አንድ ሄክታር መሬት ከሃያ ብር ባነሰ
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የመሬት ነጠቃ የተዘጋጀ ልዩ ጥናታዊ ዘገባ

Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 3 ቀን 2003 ዓ.ም. June 10, 2011)፦ አንድ ሄክታር መሬት በአንድ ዶላር ከ19 ሣንቲም (በኢትዮጵያ ከሃያ ብር ባነሰ ገንዘብ) በ”ኢንቨስትመንት” ስም ለ99 ዓመታት በሚቆይ ሊዝ የኢህአዴግ መንግሥት የኢትዮጵያን መሬት እየቸበቸበ፤ ህዝቡን ለዘመናት ከኖረበት ቀዬ እያፈናቀለ መሆኑን የኦክላንድ ተቋም እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በቅንጅት ባካሄዱት የጥናት ዘገባ ገለፁ።
ሁለቱ ተቋማት በእንግሊዝኛ ያቀረቡት ባለ 64 ገጽ ልዩ ጥናታዊ ዘገባ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ስላለው የመሬት ሽንሸና፣ ሽያጭና ነጠቃ ሰፋ ያለ መረጃን አካትቷል። (ባለ64 ገጹን የእንግሊዝኛ ጥናት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)። ጥናቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሥልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ ፓርቲ ምን እየሠራ እንደሆነ ያመላክታል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ጥናቱን አስመልክቶ “አንድ ሄክታር መሬት በሃያ ብር!” በሚል በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የላከውን ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች አስፍረነዋል።

በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች እየተካሄደ ስላለው የመሬት ነጠቃ ሰኔ 1፣ 2003 መቀመጫው በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ጠቅላይ ግዛት የሆነው የኦክላንድ ተቋም አንድ ጥናታዊ ዘገባ አውጥቷል። በኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩረው ክፍል ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ጋር በቅንጅት የተጠና ሲሆን፤ ዘገባው በ“ኢንቨስትመንት” ሽፋን ነዋሪውን ለዘመናት ከኖረበት ቀዬ በማፈናቀል አንድ ሄክታር መሬት በዶላር $1.19 (ከ20 ብር በማይበልጥ) ለ99 ዓመታት በሚቆይ ሊዝ እየተሰጠ ያለበትን ሁኔታ ቦታው ድረስ በመገኘትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ነዋሪዎችና ሌሎች ግለሰቦች ጋር በመነጋገር የተዘጋጀ ዘገባ ነው።
ባለ 64 ገጹ ጥናታዊ ዘገባ በቅርቡ በአማርኛ ተተርጉሞ የሚወጣ ሲሆን፤ አሁን የታተመውን የእንግሊዝኛ ጽሑፍ የተመለከቱት የጋራ ንቅናቄው ዋና ኃላፊ አቶ ኦባንግ ሜቶ ጉዳዩን በ1877 ዓ.ም. በበርሊን ኮንፈራንስ አፍሪካን ለመቀራመት ከተደረገው ሕገወጥ ስምምነት ጋር ያመሳስሉታል። “ይህ ሕገወጥ የመሬት ስምምነት የነዋሪውን ጥቅም የሚያስከብር ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ያለውን የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝን ጥቅም የሚወክል ብቻ ነው። ሆኖም ግን በእነዚህ ሕገወጥ ስምምነቶች የአካባቢው ነዋሪ ለዘላለም መከራ ውስጥ ይወድቃል። ልክ ከዚህ በፊት ቅኝ ገዢዎች አፍሪካውያንን ሳያሳትፉ አፍሪካን ለመቀራመት የወሰዱት እርምጃ እስካሁኑ ጊዜ ድረስ የግጭቶችና የሰላም ማጣት ምክንያቶች ሆነው እንደቀሩ ሁሉ አሁን በኢትዮጵያ የሚደረገውም ከዚህ የተለየ ውጤት አይኖረውም” በማለት አቶ ኦባንግ ያሳስባሉ። የኦክላንድ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አኑራድሃ ሚታል ደግሞ በበኩላቸው ሲናገሩ “በአፍሪካ በአሁኑ ጊዜ የተሰጠ ያለው የመሬት መጠን በጣም የሚያስደነግጥ ነው። በአፍሪካ ያሉትን ትናንሽ የእርሻ መሬቶችንና የተፈጥሮ ደኖችን እየመነጠሩ ለከፍተኛ የኢንቨስትመንት ተግባር ማዋል የምግብ ዋጋ እንዲንር የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል” በማለት ያስጠነቅቃሉ።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ነጠቃ እየመራ ያለው ያለምንም የሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነው። አገዛዙ ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይደረሰው የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ አፈና፣ ግድያ ወዘተ እንዲሁም በተደጋጋሚ በተካሄዱ ምርጫዎች የፈጸመው የማጭበርበር ተግባርና ከዚያ ጋር በተያያዘ የገደላቸው ኢትዮጵያውያኖች እንዲሁም በጋምቤላና በኦጋዴን የፈጸመው የዘር ማጥፋት አሰቃቂ ወንጀል የሕዝብ ድጋፍ የሌለው ለመሆኑ ከሚጠቀሱት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ስለዚህም ነው አሁን እያካሄደው ያለው ‹‹ስምምነት›› ሕገወጥ የሚያሰኘውና አገዛዙ በሚገረሰስበት ጊዜ አብሮ የሚሻር የሚሆነው። የኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን መቀራመት ሕገወጥ እንደነበር ሁሉ ሕዝብን ያላሳተፈ ስምምነት ሁሉ በምንም ዓይነት መልኩ ይፈረም ሕገወጥ ከመሆን የሚያድነው የለም። ይህንን አያይዘው አቶ ኦባንግ ሲቀጥሉ “ይህ በአዲስ መልኩ እየተካሄደ ያለ የእጅአዙር ቅኝ ግዛት ነው” ይላሉ። አክለውም ሲያብራሩ “በአሁኑ ጊዜ በጋምቤላ እየተሰጠ ያለው መሬት በሕንድ ወይም በእንግሊዝ ወይም በአሜሪካ ወይም በካናዳ ቢካሄድ ኖሮ ከፍተኛ የሆነ ነውጥ ያስነሳ ነበር። አንድ የኢትዮጵያ የንግድ ድርጅት ከእነዚህ በአንዱ አገሮች በመሄድ ሕዝቡ እሺ ሳይል መሬት መውሰድ ቢጀምር የዚያ ቦታ ነዋሪዎችና የአገሪቷ ሕዝቦች ዝም ይላሉ ወይ? ታዲያ እንዲህ ያለው ተግባር በሌሎች አገሮች የማይፈቀድ ከሆነ በኢትዮጵያ ሲፈጸም ትክክል የሚያደርገው ምንድር ነው?” በማለት ሊጠየቅ የሚገባውን ጥያቄ ይጠይቃሉ። ይህንን ተግባር በዝምታ የማይመለከተው ተፈናቃይ ኅብረተሰብ ሊያደርስ የሚችለውን ጥቃት በመፍራት ይመስላል አገዛዙ የቅድሚያ “ጥንቃቄ” እየወሰደ ይገኛል። ሁኔታውን በቅርብ የሚከተታተሉት አቶ ኦባንግ ሲናገሩ “መሬቱ እየተሸጠ ባለበት ቦታዎች የህወሃት/ኢህአዴግ ሠራዊት በብዛት እየታየ ይገኛል። ይህም በእነዚህ አካባቢዎች አመጽ ሊነሳ ይችላል ከሚል ፍራቻ የተነሳ ሲሆን የኃይል እርምጃ መውሰድ ከተጀመረ እጅግ በርካታ ሰዎች እንደሚያልቁ” አስቀድመው ይናገራሉ።
በመሠረቱ ኢትዮጵያውያን ልማትንም ሆነ የውጪ ኢንቨስትመንትን ይደግፋሉ። ይህንንም ተከትሎ የሚመጣውን የኢኮኖሚ ብልጽግና እና የአካባቢ የመሠረተልማት ተቋሞች መስፋፋት የሚቃወም የለም። ሆኖም ግን ነዋሪዎችን ለዘመናት ከኖሩበት በማፈናቀል እና የእርሻ መሬታቸውን በሕገወጥ መንገድ አስገድዶ በመውሰድ እና እነርሱን ለችግር እንዲጋለጡ በማድረግ የሚፈጸም ሁሉ ልማት ሳይሆን ጥፋት ነው። በዚህ የመሬት ነጠቃ ተጠቂ የሚሆኑት ነዋሪዎች በሚደርስባቸው የኑሮ ችግር ምክንያት በተነጠቁት በራሳቸው መሬት ላይ እጅግ ርካሽ በሆነ ክፍያ ለመሥራት እንደሚገደዱም በዚህ ጥናታዊ ዘገባ ከተካተቱት እውነታዎች አንዱ ነው። ሆኖም ህወሃት/ኢህአዴግ ለዚህ ጆሮ ያለው አይመስልም። እንዲያውም የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አበራ ዴሬሳ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን የኢትዮጵያን የምግብ እጥረት በቀላሉ የሚቀርፍ ዘዴ ነው ይሉታል “እኛ የአሜሪካን፣ የካናዳን፣ የቻይናን እና የሕንድ ባለሃብቶችን በሙሉ በእነዚህ መሬቶች ላይ ጥራጥሬ ሳይሆን እንደ አኩሪ አተር ያሉ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ እህሎችን እንዲያመርቱ ነው የምንመክራቸው። ምክንያቱም ከእንደነዚህ ዓይነት ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ ከሆኑ ሰብሎች በሚገኘው ገንዘብ በምግብ እጥረት ላይ የሚገኘውን 13ሚሊዮን ሕዝብ ለመመገብ እንችላለን። ገንዘብ ካገኘን ምግቡን ከየትም እንገዛዋለን፤ ያለብንንም የምግብ ችግር ማስወገድ እንችላለን” ይላሉ። በእንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ነው በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር የኢትዮጵያ ድንግል መሬት ለባለሃብቶች እየተሰጠ ያለው። የጥናቱ ዘገባ የሚያጋልጠውም እንደዚህ ዓይነቱን ከተጠያቂነት ውጪ ያለውን አስተሳሰብ ነው። በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያስከትለውንም ከፍተኛ ተጽዕኖ በተለይም አካባቢው በተፈጥሮ ደን የተከለለ ከመሆኑ አኳያ ሥነምህዳሩን ከመጉዳትም ሆነ ብዛሃ ህይወት ላይ የሚያደርሰው ጠንቅ በየትኛውም መልኩ ቦታ እንዳልተሰጠው ጥናታዊው ዘገባ በስፋት ያትታል። እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ለአካባቢ ጥበቃ ውድመት የሚያስከትል ተግባር እየፈጸሙ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አፍሪካን ወክዬ ስለአካባቢ ጥበቃ የምከራከር ነኝ በማለት የአቶ መለስ አገዛዝ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም እያምታታ ይገኛል።
ያለፉትን 20 ዓመታት በጥሞና ለተከታተለ ግለሰብ የአቶ መለስ አገዛዝ የማምታታት ባህርይ አሁን የተጀመረ እንዳልሆነ ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። ህወሃት/ኢህአዴግ የሥልጣን ኮርቻ ላይ እንደተቆናጠጠ አቶ መለስ ከአስር ዓመታት በኋላ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸው ራዕይ በቀን ሦስት ጊዜ እንዲበላ ማድረግ እንደሆነ ‹‹ተንብየው›› ነበር። በነዚህ አስር ዓመታት ላይ ሌሎች አስር ዓመታት ተጨምረው ምንም የገቢ ምንጭ የሌለው ኢትዮጵያዊ በቀን ሦስት ጊዜ ሊመገብ ይቅርና ገንዘብ ያለው እንኳን በገንዘቡ ገዝቶ ለመመገብ የማይችልበት ‹‹የትንቢት›› ፍጻሜ ላይ ደርሷል። ጠኔ በገጠር ብቻ መሆኑ ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ በታላላቅ ከተማዎችም ሕዝቡን ክፉኛ እያራወጠው ይገኛል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ነዋሪ ለም መሬቱ ለውጪ ባለሃብት እየተሸጠና ምርቱ ወደ ውጪ እየተጋዘ ሲሄድ የሚመለከትበት ዓይን ይኖራል ብሎ መገመት ያዳግታል። ጥናታዊው ዘገባም ይህንኑ ሃቅ የሚያስተጋባ ሲሆን በተለይ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ቁጣ በበርካታዎች ዘንድ እንዳለ ሆኖም ግን አገዛዙ ሊያደርስ የሚችለውን ኢሰብዓዊ የአጸፋ እርምጃ በመፍራት ሕዝቡ በታመቀ ዝምታ ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራል። ነገር ግን ይህ ዝምታ እንደማይቀጥል እንዲያውም የጠኔው ሁኔታ እያየለ ሲሄድ በአገሪቷ ውስጥ ከሚታየው አፈናና የመብት ረገጣ ጋር ተቀላቅሎ ባልታሰበ ጊዜ ሊፈነዳ እንደሚችል ብዙዎች የሚስማሙበት እውነታ እየሆነ መጥቷል።
ሆኖም ከመሠረቱ ማርክሲስታዊ የሆነው የአቶ መለስ አገዛዝ ይህንን እውነታ ከመቀበል ይልቅ የምዕራባውያን ዕርዳታ እንዳይቀርበት የዴሞክራሲን ካባ ከላዩ በመደረብ ችግሩን ለማዳፈን ጥረት እያደረገ ይገኛል። እንደዚህ ዓይነት ጥናታዊ ዘገባዎች ሲወጡም ልክ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የሂውማን ራይትስ ዎችና የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያቤት እንዲሁም የአውሮጳ ኅብረትን ዘገባ በማናናቅ እንዳጣጣለው ሁሉ ይህንንም ጥናታዊ ዘገባ እንደሚያጣጥል አስቀድሞ የሚገመት ነው። ሆኖም ግን በቦታው ላይ እየተከሰተ ያለውንና ከነዋሪዎቹ የሚሰማውን የሰቆቃ ድምጽ እስከመቼ ሊያፍን እንደሚችል ለራሱም የተረዳው አይመስልም። እንዲያውም በቅርቡ አቶ መለስ እስካሁን ለምን አገሪቷ ተሸጣ እንዳላለቀች በቁጭት የሚከተለውን ተናግረው ነበር፡- “ማልቀስ ካለብን ለህንዶች ለሰጠነው 100 ሺህ ሄክታር መሬት ሳይሆን ገና ላልሰጠነው 3 ሚሊዮን ሄክታር ነው”።
የጋራ ንቅናቄው መሪ አቶ ኦባንግ ድርጅታቸው ጉዳዩን በቀላሉ እንደማይመለከተው ነው የሚናገሩት፡- “በአሁኑ ጊዜ እኛ ኢትዮጵያውያን በተቻለን መጠን በእንደዚህ ዓይነት ወንጀል የተሰማሩትንም ሆነ በሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ በሕገወጥ መንገድ ኃብት ማካበትን፣ ወዘተ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ሁሉ ለፍርድ የሚቀርቡበትን መንገድ በማመቻቸት በኩል በትጋት እየሠራን ነው። ጊዜ ቢወስድም ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረባቸው አይቀሬ ነው፤ ምዕራባውያንም የወንጀለኞች መታጎሪያ የሚሆኑበት ምንም ምክንያት የለም” በማለት ያስገነዝባሉ። አቶ ኦባንግ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁም የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ፡- “እናንተ ባለሃብቶች በግፍ እየተነጠቀ በተሰጣችሁ መሬት ላይ ምርት አምርታችሁ ትርፉን እያጋበሳችሁ በነጻ እንኖራለን ብላችሁ አስባችሁ ከሆነ በጣም ተሳስታችኋል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝምታ እንደ እሺታ ተቀብላችሁት ከሆነ የዝምታው ቋንቋ ስላልገባችሁ በድጋሚ በአንክሮ ለማዳመጥ ብትሞክሩ ይሻላል። የሕዝብ ድጋፍ ከሌለውና እየሞተ ካለ አገዛዝ ጋር የምታደርጉትን ውል በድጋሚ ብታጤኑት ይበጃል። ይህ አገዛዝ በተባበረ የኢትዮጵያውያን ክንድ ወደ ከርሰመቃብሩ ይወርዳል፤ የዚያን ጊዜ የእናንተም የመሬት ሽያጭ ውል አብሮ ያከትማል።”
የኦክላንድ ተቋም እና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ዋና ዳይሬክተሩን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) በመጻፍ ወይም በስልክ (202) 725 - 1616 በመደወል ወይም ድረገጻችንን (http://www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ።



