በአዶልፍ ፍሬድሪክ ቤተክርስቲያን ተጠልለዋል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሰኔ 4 ቀን 2003 ዓ.ም. June 11, 2011)፦ ለረጅም ዓመታት በኖርዌይ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የደረሰባቸውን በደል ለሌሎች መንግሥታት ለማሳወቅና ተቀባይ ሀገር ለመፈለግ ወደ ስዊድን ገብተው በአዶልፍ ፍሬድሪክ ቤተክርስቲያን መጠለላችውን የስደተኖቹ ተወካይ አቶ ልዑል ታደሰ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጹ። 

በኖርዌይ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሌሎች ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩና በአሁኑ ጊዜ በችግር ላይ መሆናቸውን ያስታውቁት አቶ ልዑል አያይዘው ሲናገሩ፤ ቀደም ሲል የግብር መክፈያ ካርድ እየተሰጠን በልዩ ልዩ ሥራ ላይ በመሰማራት የመንግሥት ግብር እየከፈልን እንኖር ነበር፤ ሆኖም ከዚህ ዓመት መግቢያ ጀምሮ የግብር መክፈያ ስለተከለከልን ከምንሠራበት ቦታ በመባረራችን ባልታሰበ ችግር ላይ ልንወድቅ ችለናል ብለዋል።

አቶ ልዑል ስለኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ችግር ሲያብራሩ፤ “… አብዛኞቻችን በኖርዌይ ከሁለት ዓመት እስከ አስራ ስምንት ዓመት እንደቆየን፣ በዚሁም ጊዜ ውስጥ ቤተሰብ የመሰረትንና ልጆችም ያፈራን በመሆናችን፤ የመኖርያ ፈቃድ ተሰጥቶን እንደቀድሞአችን እየሠራን ለመኖር እንድንችል ለሚመለከታቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ኃላፊዎች ሳንሰለች ካላማቋረጥ ብንጠይቅ መልስ ልናገኝ ባለመቻላችን፤ ተደጋጋሚ ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ ጥያቄአችን ቀጠልን። …

“ሆኖም በዚህ ለጥያቄዎቻችን ያገኘነው መልስ ባለመኖሩ ችግራችንም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በመሄዱ ብዙም ህጻናት ልጆች ያሏቸው በማህላችን ስለሚገኙ ጉዳያችን ትኩረት እንዲያገኝ ጥቃቱ የደረስብን ስልሳ ሦስት የምንሆን ስደተኖች በኦስሎ ከተማ በሚገኝ ዶም ቤተክርስቲያን ውስጥ በመግባት ለስምንት ቀናት ያህል የረሃብ አድማ አደረግን። …

“ይህ ችግር ያሳሰባቸው የኖርዌጅያን ጳጳስ እና የኛኑ ጉዳይ ለመከታተል የመጡት አቶ ኦባንግ ሜቶ እንዲሁም የኖርዌጅያን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንድንነጋገር አድርገው ጊዜያዊ መጠለያና ምግብ እየተሰጠን ጉዳያችን ታይቶ መፍትሄ እንደሚፈለግለት ተነግሮን በመጠለያ ጣቢያው ቆየን።

“ሁኔታው መልኩን ሳይለውጥ ቢቆይም፤ ከዛሬ ነገ መልስ ተሰጥቶን ወደቀድሞ ኑሮአችን እንመለሳለን፣ የተሻለ ሁኔታም ይገጥመናል ብለን ስንጠብቅ ወደ ካምፕ ገብተን እንድንኖር ተነገረን። እኛ የጠየቅነው ጥያቄ ይሄ ባለመሆኑ የኖርንበትና እየሠራን የቆየነውም በዛው ከተማ በመሆኑ በተባለው ሃሳብ ለመስማማት አልቻልንም።

“ይህ በዚህ እንዳለ ፖሊሶች መጠለያው ጣቢያ ድረስ በድንገት በመምጣት በኃይል ለማስወጣት በመሞከራቸው፤ ብዙ ሁካታና ትርምስ በመነሳቱ ጥለውን ሄዱ። ማታውኑ ኃይል በመጨመርና ተጠናክረው በመምጣት ሁላችንንም አውጥተው በመኪና በመጫን ከከተማው ውጪ በተለያየ ቦታ ወረወሩን። የደረሰብን ሁኔታ ለጊዜው ቢያስደነግጠንም በሞባይል ስልክ ልንገናኝ በመቻላችን ሁላችንም እንደገና ተሰባስበን በፊት ከነበርንበት ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ድንኳን ዘርግተን ተቀመጥን።

“በዚሁ ሁኔታ ለአንድ ወር ያህል ከቆየን በኋላ የኖርዌይ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እንደተስማማ እና ሊመልሱን እንደተዘጋጁ ገለጹልን። ይህ ሁኔታ በእጅጉ ስለአሳሰበን ወደሌላ ሀገር በመሄድ ችግራችን በአውሮፓ ደረጃ ታውቆ ተቀባይ መንግሥት እንድናገኝ ለመጠየቅ አንድ የዘጠኝ ወር ልጅ፣ አስራ አንድ ሴቶች እና አስራ ስድስት ወንዶች ሆነን ወደ ስዊድን በመግባት ስቶክሆልም በሚገኘው በአዶልፍ ፍሬድሪክ ቤተክርስቲያን ለመጠለል ችለናል።” ሲሉ አቶ ልዑል ታደሰ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ በስዊድን በምን አይነት ሁኔታ እንደሚኖሩ፣ ከስዊድን የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ከእነማን ጋር እንደተነጋገሩ፣ ከእነሱስ መልስ አግኝተው እንደሆን፣ በቀጣይነትስ ምን ማድረግ እንዳሰቡ ለጠየቅናቸው ጥያቄ አቶ ልዑል ሲመልሱ፤ … ያለነው በዛው ቤተክርስቲያኑ ሲሆን ኃላፊዎቹ በዚህ ቦታ ለረጅም ጊዜ እንደማንቆይ ገልጸውልናል። ከስዊድን የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ቬንስተር ፓርቲን ጨምሮ የልዩ ልዩ ፓርቲ ተወካዮች አነጋግረውን ጉዳያችንን አስረድተናል። እነሱም ለስዊድን ፓርላማ አቅርበው እንደሚነጋገሩበትና ጉዳያችን መፍትሄ ማግኘት ካልተቻለም የአውሮፓ ፓርላማ ድረስ ለማቅረብ እንደሚችሉም አሳውቀውናል ብለዋል።

“በተጨማሪም ከወ/ሮ ካሪና ሄግ ጋር በስልክ የተነጋገርን ሲሆን፣ ከሆርን ኦፍ አፍሪካ ተወካዮች፣ ከቀይ መስቀል ኃላፊዎች፣ ከUNHCR፣ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለሥልጣናት ጋር እንዲሁም ከጋዜጠኞች ጋር ተነጋግረን ጉዳያችን በዕለታዊው የሜትሮ ጋዜጣ ላይ ሊሰፍር ችሏል።” ሲሉ አቶ ልዑል ገልጸውልናል።

አቶ ልዑል፤ “… የስዊድን መንግሥት ከሌሎች ሊረዱን ከሚፈልጉ መንግሥታት ጋር በመነጋገር ሦስተኛ ሀገር እንዲቀበለን እንዲያግዘን፤ ለዚህም ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ የኃይማኖት ድርጅቶች፣ የቀይ መስቀል ማኅበር፣ የአውሮፓ ፓርላማ እና ሌሎቹም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲተባበሩን እንጠይቃለን።” ብለዋል።

በመጨረሻም አቶ ልዑል የሚያክሉት እንዳለ ጠይቀናቸው፤ የሚከተለውን ጥሪ አስተላልፈዋል። “ይህንን የሰሙ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወገኖቻችንም ሁሉ ከጎናችን እንዲቆሙ እያሳሰብን፤ በስዊድን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በቅርቡ ድምፃችንን ለማሰማትና ችግራችንን ለማስረዳት በስዊድን ሠላማዊ ሰልፍ ስለምናደግ፤ ጥሪ በምናቀርብ ጊዜ በሰልፉ ላይ እንድትገኙልን እንጠይቃለን” በማለት ለኢትዮጵያውያን የድጋፍ ጥሪ አስተላልፈዋል።

 

ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹን ለማግኘት፣ ለማበረታታትና ለመርዳት የስደተኞቹ ተወካይ የሆኑትን አቶ ልዑል ታደሰን በስልክ ቁጥር (0046)(0)73-784-39-73 ማግኘት ይቻላል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!