Ethiopia Zare (ሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2003 ዓ.ም. June 13, 2011)፦ የአንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር መሪ የነበሩት የፖለቲካ ሳይንቲስት ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት ባለቤት ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውንና የቀብር ስነ ስርአታቸውም በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ከአዲስ አበባ ገለጹ።

 

ዶ/ር ታዬ የኢህአዴግ አገዛዝ የደህንነት ሰዎች ታፍነው ለስድስት አመታት በታሰሩ ሰአት አጋር እንደነበሩ የሚነገርላቸው ወ/ሮ አስቴር ከመኖሪያ ቤታቸው በድንገት ታመው ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም ህይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም።

 

ዶ/ር ታየ ወልደሰማያት በ1983 ዓ.ም አገዛዙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካባረራቸው 42 አንጋፋ መምህራን መካከል አንዱ ሲሆኑ ከ97 የኢትዮጵያ ምርጫ በፊት አገዛዙን በመጋፈጥና የሰላ ሂሶችን በመሰንዘር የሚታወቁ እና ከምርጫው ውጤት አፈና በኋላ በስደት አሜሪካን ሀገር የማስተማር ስራቸውን እንደቀጠሉ ይታወቃል። በሀገር ውስጥ ከተቀበሉት ስቃይ በላይ ከሀገር ርቀው መኖራቸው ተጨማሪ አበሳ እንደሚሆንባቸው የሚናገሩት የዶ/ር ታዬ የቅርብ ወዳጆች የአንዲት ሴት ልጃቸውን እናት ወይዘሮ አስቴር ህይወት በድንገት ማለፍ ሀዘናቸውን የበረታ ያደርገዋል ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጠዋል።

 

ወይዘሮ አስቴር አዲስ አበባ በሚገኘው አሜሪካን ኢምባሲ ቪዛ ለምግኘት ሶስት ጊዜ ቢሞክሩም መከልከላቸውን ለማወቅ ችለናል።

 

የወ/ሮ አስቴር የቀብር ስነስርአት የባለቤታቸው የዶ/ር ታዬ እና የእሳቸው ቤተሰቦች በተገኙበት አርብ ግንቦት 19 ቀን 2003 ዓ.ም. እስቲፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል። ለዶክተር ታዬ ወልደሰማያትና ለመላ ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ይሰጣቸው ዘንድ የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል እንመኛለን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ