• አሜሪካዊው ሰላይ በለንደኑ ጉባኤ ቁልፍ ሰው ነበር
  • የደርግ ደህንነት ሹም ኮ/ል ተስፋዬ ቀብር ተፈጸመ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2003 ዓ.ም. June 13, 2011)፦ የሕወሀት ጥብቅ ወዳጅና ከደርግ መንግስት ውድቀት በፊት የለንደኑ ጉባኤ አቀናባሪ ፖል ሄንዝ ህይወት ማለፉ ተሰማ። የደርግ የደህንነት ሹም ኮ/ል ተስፋዬ ወ/ስላሴ ቀብር ስነስርአት ተፈጸመ።

 

ፖል ሄንዝ ህወሐት/ኢህአዴግ በጫካ ትግል በነበረበት ሰአት ጭምር ከፍተኛ የመረጃ እገዛ ሲያደርግ እንደነበርና ሰሜን ሸዋ መረሀቤቴ ድረስ አብሮ በመዝለቅ የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲስፋፋ ከአቶ መለስ ጋር በቅርብ ይሰራ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በ1983 ዓ.ም ከደርግ ውድቀት በፊት በለንደን በተካሄደው የፖለቲካ ድርጅቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጉባኤ የአቶ መለስ ቡድን አይሎ እንዲገኝና የበላይነቱን ይዞ ሀገሪቱን እንዲቆጣጠር ከፍተኛውን ሚና የተጫወተ ሁነኛ ሰው መሆኑ አይዘነጋም።

 

ፖል ሄንዝ ኢትዮጵያን በጎሳ በመመተር ክልላዊ መንግስታትን በህዝብ ላይ ከመጫን አልፎ የአባይን ባለቤትነት ከኢትዮጵያ እጅ እንዲወጣ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የሚያስታውሱ ምሁራን ይናገራሉ።

 

እንደምሁራኖቹ አባባል በወቅቱ አቶ መለስ ስልጣን ላይ ከወጡ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከግብጹ መሪ ሆስኒ ሙባረክ ጋር በፖል ሄንዚ ሴራ የታሸ ዶሴ ላይ የመፈራረማቸውን ያነሳሉ። ይህንኑ የስምምነት ፊርማ በሚመለከት አንጋፋው ኢትኦጵያዊ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “ከዚህ በላይ እንደተገዛ እቃ አድርገን ከመቁጠር በስተቀር እኛ ኢትዮጵያዊያን ህጋዊ እውቅና አንሰጠውም” በማለት አቋማቸውን ገልጸውበታል።

 

ማቹ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሰው ፖል የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ይከታተል እንደነበርና የኢትዮጵያን እድገት በተመለከተም “በአፍሪካ ውስጥ ሌላ ጃፓን አያስፈልገንም” የሚል ብርቱ አቋም እንደነበረው የብዙዎች ትዝታ ነው።

 

በተያያዘ ዜና የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግስት ዋና የደህንነት ሹም የነበሩት ኮ/ል ተስፋዬ ወ/ስላሴ ግንቦት 24 ቀን የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በእስረኞቹ ላይ የተወሰነው የሞት ቅጣት ወደ እድሜ ልክ እስራት የሚለውጠውን የመንግስትን የይቅርታ ደብዳቤ ለህዝብ ይፋ ካደረጉ በኋላ ባለፈው ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

 

ኮ/ሉ ሀሙስ ግንቦት 25 ቀን/2003 ዓ.ም. ልጃቸው እስር ቤት ለመጠየቅ ወደ እስር ቤት ሄዶ በነበረ ሰአት ሳያገኛቸው መመለሱን የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ያጣራ ሲሆን የተሰጠው ምክንያት ለጋዜጠኞች ቃለ ምልልስ እየሰጡ ነው የሚል እንደነበርና ቅዳሜ እለት መሞታቸውን እንደሰሙ ቤተሰቦቻቸው ገልጠዋል።

 

ኮ/ል ተስፋዬ በሀገር ውስጥ፣ በአሜሪካና እስራኤል ከፍተኛ የጸጥታና የስነ ልቦና ትምህርት የተከታተሉና የቀድሞው መንግስት ቀንደኛ ሰው መሆናቸው ይታወቃል። ኮ/ሉ በ1981 ዓ.ም. የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ካከሸፉት ግንባር ቀደሙ ሲሆኑ በፖል ሄንዝና በህወሀት፤ በሲ.አይ. ኤ እና በተለያዩ የአባይ ጉዳዮች ላይ የጥበቃና የደህንነት እውቀት ያካበቱ እንደነበሩ የቅርብ ወዳጆቻቸው ገልጸዋል። የኮ/ል ተስፋ ወ/ስላሴ ቀብር ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ግንቦት 30 ቀን 2003 ዓ.ም. በኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ