ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ልትናገር ነው
Ethiopia Zare (አርብ ሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. July 1 , 2011):- በዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮጵያዊያን ውርስና ቅርስ አዘጋጅነት በሚካሄደው ታላቅ ፌስቲቫል ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ህዝብ ፊት ቀርባ ንግግር ልታደርግ መሆኑን ባልደረባችን ተክለሚካኤል አበበ ከስፍራው አስታወቀ። ዝርዝሩን እንደሚከተለው አቅርቦታል።
የክብር ቀን፡ የክብር ሳምንት
እነሆ በኢትዮጵያዊነታችሁ ደስ ይበላችሁ
- ከ ሐምሌ ፩ እስከ ሐምሌ ፫፡ ፳፻፲፩ ዓ.ም. (ጁላይ 1 እስከ ጁላይ 3፡ 2011 ዓ.ም.)
ልጅ ተክሌ - ከዋሽንግተን ዲሲ
የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ፌስቲቫል በደመቀ ሁኔታ ሊከፈት ነው፡ ዝግጅቱ ተጧጡፏል፡ ኢትዮጵያዊያን ከየስቴቶቹ እየገቡ ነው።
- ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ከእስር ከተፈታች ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ ባደባባይ ትናገራለች።
- ቅዳሜና እሁድ ፓርኪንግ ነጻ ነው።
- የልጆች መንደር፡ የሩጫ ውድድር፡ የስእል ትእይንት፡ የምግብ፡ የአልባሳትና ሌሎች ደረቅ ሸቀጦች ገበያ
የአሜሪካንን ድንበር ማቋረጥ ገና ሳስበው ይከብደኛል።
አንዳንድ ግዜ አንድ ሰዓት አንዳንድ ግዜ እስከ ሶስት ሰዓት መቆም የተለመደ ነው። በተለይ ከቫንኩቨር ሲያትል ስንጓዝ ይብሳል። የአሜሪካን ድንበር ጠባቂዎች፡ ሁሉም መንገደኛ እነሱን፡ አሜሪካንን ሊያጠቃ የመጣ ይመስላቸዋል። ስለዚህ ሲያዩ ያጉረጠርጣሉ። ሲናገሩ ይቆጣሉ። ዛር እና ውቃቢ ያስነሳሉ። ይሄ ጸባያቸው ከድንበር ድንበርና ከሰው ሰው ይለያያል። እነሆ ዛሬ ግን ድንበሩ ቀለል ብሏል። ከፊታችንም ወረፋ የለም። ከሞንትሪያል ተነስተን፡ ኒው ዮርክ በጊዜ ልንገባ ነው። እንደፈራሁት 20 ሳይሆን 17 ሰዓት ብቻ ሊፈጅብኝ ነው። ከኦታዋ-ዋሺንግተን ዲሲ። መብረር እችል ነበር። ግን ሼክስፒር ፈይሳ ክንፌን ሰበረው። ለመጀመሪያ ደረጃ በረራ የተመደልኝ የትኬት ገንዘብ የተቸገሩና ወላጅ አልባ ህጻናትን ወደሚረዳው የበጎ-አድራጎት ድርጅት፡ ወደ ሜሪ ጆይ መስራች (ሲስተር ዘቢደር) ድንኳን ኪራይ ዞረ። እንዲህ ነው ደግነት። ቢሆንም ደስ ደስ ይለኛል። እንደኔ ደግ ያርጋችሁ።
ደስ ደስ ይለኛል። እነሆ በኢትዮጵያዊነታችሁ ደስ ይበላችሁ ተብሎ ባንዱ ነቢይ የተነገረው በኔ ይፈጸም ዘንድ፡ በዋሽንግተን ዲሲ ወደሚከበረው የመጀመሪያው የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ፌስቲቫል ስጓዝ ደስ ደስ እያለኝ ነው። ድንበሩን መልአኩ ሚካኤል ከፍቶታል። ተክለሚካኤል አይደለሁ። መንገዱንም መልአኩ ጅብሪል ያቀናዋል። መንገዱ እስካሁን አልጋ ባልጋ ነው። በርግጥ ግን ጉዞው ያደክማል። የዛሬውም፡ ላለፉት አስር ወራት የተጓዝነውም መንገድ ያድክማል። ግን ደግሞ በተለይ ያንዳንዶቹ ትጋት ያበረታል። ጌቱ ስእሎቹን ሊሰቅል ከወዲያ ወዲህ ይራወጣል። ቢኒያም ኮች፡ እግር ኳስ ተጨዋቾቹን ሊያሰለጥን ይማልዳል። ስልኬ አቃጨለ። እመቤት፡ ነች። ግምዣ ቤታችን። ነፍሷን አታውቀውም። እነሆ አሁንም ከካሊፎርኒያ ዲሲ ሁለት ቀን ቀድማኝ ገብታም ስልኳ አያባራም። የጥሪዎቹ ብዛትና አይነት በዚህ ወር እያደገና እየበዛ መጥቶባታል። የጥሪው ብዛት ከጓደኞቿ፡ ከቤተሰቦቿ እንዲሁም ከራሷም ጋር ያላትን ግንኙነት እያወጣጠረው መጥቷል። እንዱ ስለጋዜጠኞች ማለፊያ ወረቀት ይጠይቃታል። አንዱ ስለድንኳንና ምግብ ዝግጅት። ሌላኛው ስለ ዝግጅት መጀመሪያ ሰዓት። ስለ አዲስ አባል አመዘጋገብ የሚጠይቅም አለ። ሌላኛው ለፌስቲቫሉ ስለሚታተሙት ቲሸርቶችና በራሪ ወረቀቶች ይደውላል። ሌላኛው ደግሞ ስለእርብ የመክፈቻ ዝግጅት ይደውላል። አንዱ ስለሆቴል ነው። አንዱ የፌስቲቫሉ ዋና ሆቴል፡ ሜሪዬት ኪ ብሪጅ ሞልቶበት፡ http://www.marriott.com/hotels/travel/waskb-key-bridge-marriott/ ሌላ አማራጭ ሆቴል ፍለጋ ነው የደወለው። አንዳንዱ ደግሞ ስለህጻናት ዝማሬ ነው።
እነሆ፡ እመቤት፡ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስን የመጀመሪያ አመት የዋሽንግተን ፌስቲቫል የመጨረሻ መሰናዶ ተያይዛው፡ የሚመጣባት አንዳንዱ ስልክ የሚያበረታታ ነው። አንዳንዱ ስልክ ደግሞ የሚያስጨስ ነው። ይሄ ጉዳይ እንዳትተውው ልጇ ነው። እንዳትስመው ደግሞ እሳት ሆነባት። እነሆ ከነገ፡ አርብ እስከ እሁድ እስክትገላገል፡ እመቤት፡ ከጓደኞቸ ጋር የተሳካ ፌስቲቫል ለማድረግ ደፋ ቀና ትላለች። አብዛኛው ነገር መስመር ይዟል። መድረክና ድንኳን፡ አዳራሽን የሙዚቃ መሳሪያ ተይዟል። ማስታወቂያና ግብዣው ለየተቋማቱ ተልኳል። በየቀኑ ስብሰባ ነው። ቴሌኮንፈረንስ። የኢሜል ልውውጡ ይገድላል። ድንኳን ተከራዩ ተሰልፏል። ዝግጅት አቅራቢው ተሰናድቷል። እንቅፋት ግን በሽ ነበር። ሁሉንም አለፍነው እንጂ።
አንዱን ምጥ አርብ እንገላገለዋለን። አርብ ከሰዓት በኋላ፡ ከአምስት ሰዓት ጀምሮ፡ የስእል ትእይንት፡ በሁለት ኢትዮጵያዊያን ሰኣሊያን በመሰረትና በመክብብ ይቀርባል። ይሄ የመክፍቻው እለት ነው። የግጥምና የጥበብ ስራዎች፡ እንዲሁም የታላላቅ ኢትዮጵያዊያን ንግግር ይቀርባል፡ ከኢትዮጵያ የተላኩ የጥበብ ስራዎችም አሉን። አርብ ጁላይ 1፡ 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ከ11፡00 ጀምሮ (5pm)። ሁሉም የፌስቲቫል ዝግጅት በዚያው በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ ቅጽር-ግቢ ቢሆንም፡ የአርብ መክፈቻ ዝግጅቱ ቦታ ከቅዳሜና እሁዱ ዝግጅቶች ቦታ ለየት ይላል። የአርብ እለቱ ዝግጅት፡ በLucille and Richard Spagnulo Gallery; 1221 36 St., NW ነው። Washington, D.C. 20057, Georgetown University። አርብ ጁላይ 1 የክብር ቀን መጀመሪያ ነው።
ቅዳሜና እሁድ ፓርኪንግ ነጻ ነው
የቅዳሜና እሁዱ ዝግጅቶችም እዚያው ጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሆኖ፡ በሁለገብ ስቴዲየሙ ውስጥ ነው። ቅዳሜ እና እሁድ አድራሻው፡ 3700 ) ኦ መንገድ ላይ ነው። (3700 O Street NW, Washington, D.C., Georgetown University, Multi-Sport Facility):: በመኪና ለምትመጡ፡ በጣም ቀላል ነው። 3607 M Street NW (Gas Station) ድረስ ይምጡ፤ ከ M Street ወደ Canal Road ይግቡ። ግማሽ ብሎክ እንደሄዱ፡ የትራፊክ መብራት ላይ ቀኝዎትን ይያዙና የSouthWest Garage ምልክት ተከትለው መኪናዎትን ያቁሙ። ቅዳሜ እግር ኳስ፡ ሩጫና የባህል ሙዚቃ ጨዋታ አለ። የነ አቶ ዳምጠው ቅኝት ባንድ፡ ከነማሪቱ ለገሰ፡ ሻምበል በላይነህ ጋር ሊያዝናናዎት ተዘጋጇቷል። እሁድ ደግሞ እነ ያምቡሌ (ብርሀኑ ተዘራ)፡ መስፍን ዘበርጋ፡ እና አበባ ደሳለኝ፡ አሉልዎ። መኪና የማትነዱና የኔ ቢጤ እግረኞች፡ አቶ ለማና ጓደኞቻቸውን እድሜ ይስጣቸውና፡ ቀኑን ሙሉ በነጻ ከፎጊ ቦተም ባቡር ጣቢያ ሊያመላልሱን ቃል ገብተዋል። እመቤትና ጓደኞቿ፡ ለህጻናት ምን የመሰለ የልጆች የድንኳን አምባ አዘጋጅተዋል። የልጆች መንደር፡ የልጆች ድንኳን፡ የልጆች ዳስ፡ እያልን ስንከራከር ነው፡ እዚህ አገር 40 አመት የኖረችው እመቤት፡ “የልጆች አምባ” ብላ የሰየመችው።
ሰዉ ከየስቴቱ እየገባ ነው፡ ብርቱካን ንግግሯን ጽፋ ጨርሳለች፡
እነሆ እኔም ዲሲ በሰላም ገብቻለሁ። አቶ ሀይሌና አምስት ጓደኞቻቸው ከሂውስተን እየነዱ መጥተዋል። ኤደንና በላይ ከካሊፎርኒያ ገበተዋል። ሰላማዊት ከካንሳስ ስትገሰግስ መጥታ የስራዋ ቦታዋን እንድንሰጣት እየሞገተችን ነው። ሼክስፒርና ጓደኞቹ ከሲያትል ተሰልፈዋል። ዲሲ ሞቅ ሞቅ ብሏል። በዚህ አጋጣሚ ከጀርመንም የመጡ አጋጥመውኛል። ብርቱካን ሚደቅሳም እነሆ ከእስር ከተፈታች በኋላ፡ ለመጀመሪያ ግዜ ግልጽ ያደባባይ ንግግር ልታደርግ ተዘጋጅታለች። የክብር እንግዳችን ብርቱካን ትከበራለች። ለብርቱካን መፈታት ታላቅ አስተዋጽኦ አደረገውና “የውቦች ስደት” የተሰኘውን ፊልም የሰራው ክሪስ ፍላህርቲና ሌሎች ታላላቅ ኢትዮጵያዊያንም ይከበራሉ። የእግር ኳስ ቡድኖቻችን እየተሰናዱ ነው። አቢሲኒያ ከሂውስተንና ካትላንታ፡ ጥቁር አንበሳ ከባልቲሞር፡ ራስ ተፈሪ ከዲሲ፡ ኮከበ-ዳለስ ከቨርጂኒያና፡ ኢትዮ አንበሳ ከቶሮንቶ ሊጋጠሙ አሰፍስፈዋል። ከዚያ የአጭርና መካከለኛ ርቀት ሩጫም አለ። የዲሲ ቅድስት ማሪያም ሯጮች ሊሮጡ ተሰናድተዋል። ግን ይሄ ሁሉ ድካም ለምንድር ነው? ያስፈልግ ነበርን? እነሆ ቅስቀሳና ውስወሳ።
ትንሽ ሀተታ፡ ትንሽ ፕሮፓጋንዳ
እኔና እኛ የኢትዮጵያዊነትን ፌስቲቫል ይዘን ሙጭጭ የምለው ለምንድር ነው? የኢትዮጵያን ጥበብ ቀሚስ ማየት ወይንም ቀይ ወጥ ማሽተት ወይንም ኢትዮጵያዊያንን ማስጨፈር አምሮን አይደለም። በማህበራዊ፡ በባህላዊና በስፖርታዊ፡ በመዝናኛ ጉዳዮች ላይ ህዝቡን ማሳተፍና መቆጣጠር ካልቻልን በስተቀር፡ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተጋረጠውን ጦርነት አናሸንፍም ብለን ስለምናምንና፡ የኢትዮጵያዊነት ባህል፡ አንዱ የመዋጊያ መሳሪያችን፡ የህልውና መሰረታችን ነው ብለን ስለምናስብ ነው። ከዛሬ ስድስት ወር በፊት፡ የዚህን የባህል ዝግጅት አስፈላጊነት ለታማኝ በየን ስጽፍለት እንዲህ ብዬ ነበር
“…. ላገርህ የምትታመን ነህና የምትችለውን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አትልም። በትግሉ እየተሸነፍን ነው ባልልም፡ ጠላታችን በራሳችን መሬት ላይ እያጠቃን ነው። ባገር ቤትም በዚህ በውጪም። ጥቃቱ ደግሞ ከተራው ህዝብ ይልቅ ያንተን ቢጤውን ታዋቂ ሰው ያቃጥላል። ኢህአዴግ ያደረሰብንን ጉዳቱን ብትመዝነውም፡ ከተራው ሰው ይልቅ የሚጎዳው ከፍ ያለው ሰው ነው።፡ተራው ሰውማ ሁሌም በችግር መኖር ለምዷል። በባህላዊና በማህበራዊ፡ እንዲሁም በኢኮኖሚያዊና በስፖርታዊ ነገሮች ላይ የበላይነቱን ካልያዝን ጠላት በደንብ አድርጎ ያሸንፈናል። ስለዚህ በዚህ በመጪው ክረምት ከሰኔ አንድ እስከ ሀምሌ ሶስት በዋሽንግተን በሚደረገው “የኢትዮጵያዊያን ፌስቲቫል በሰሜን አሜሪካ” ያለህን ሁሉ ወርውር ብዬ ነበር። እነሆ ከታማኝ እስከ ሰጠኝ፡ ከፈረጃ እስከ ከድጃ፡ ከዳበሳ እስከ ዲሳሳ የኢትዮጵያዊነቱን ፌስቲቫል ለማሳካት ደፋ ቀና እያሉ ነው።
የዚህ ዝግጅት ትርፍ ብዙ ነው። የስነልቡናውና የባህል ትርፉ ይልቃል። ከበርበሬ እስከ ቀበቶ፡ ከመጽሀፍ እስከ ፊልም፡ ከጥቅስ እስከ ጥብስ … የሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች ሁሉ ይገኛሉ። በዚህ መልኩ በማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የበላይነቱን ይዘን ካልሄድን ያለንን ሁሉ ለጠላት እያስነጠቅን መጓዝ ይሆናል። አገር መጠበቅ ህዝብን መያዝ ይፈልጋል። ህዝብ ከምንይዝበት መድረክ አንዱና ዋንኛው ደግሞ የመዝናኛ መድረክ ነው። እኛ መዝናኛና መገናኛ መፍጠር ካልቻልን፡ ጠላት ያንን መድረክ እየፈጠረ ስራችን ከማጥቃት ወደመከላከል ይወርዷል። ለነገሩ ወርዷል እንጂ። በገንዘብ ረገድ ይሄ ዝግጅት ያንዳንዶቻችንን ኪስ ቢጎዳም፡ ከፍተኛ የሞራል ትርፍ አለው። ከቫንኩቨር እስከ ኤድመንተን እስከ ቶሮንቶ እስከ ካልጋሪ፡ እስከ ዊኒፔግ እስከ አምስተርዳም ስጓዝ ያስተዋልኩት ነገር፡ ኢትዮጵያ ለአሜሪካና በካናዳ ዜጎች በደንብ ሊቸበቸብ የሚችል ከግሪክ፡ ከአይሪሽ ወይንም ከቻይናና ህንድ ያላነሰ ባህልና ምግብ አላት። ያንን ብልጫ መጠቀም እንችላለን። ያንን የባህል የበላይነት መቆጣጠራችን በጠላቶቻችን ላይ የሞራልና የፖለቲካም የበላይነት እንዲኖረን ያደርጋል።
ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው። ታሪክ ሰሪ ግለሰቦችም ናቸው። አብዲሳ አጋ። በላይ ዘለቀ። ዘርአይ ደረስ። ያ አንድ ሰው እስኪሞት ድረስ ትከሻው ቢጎብጥም ኪሱ ቢቀደድም ቆዳው ቢሸበሸብም ጸጉሩ ቢሸብትም የምንፈልገው ቦታ እስክንደርስ የተጣለበትን አደራ ከመወጣት ውጪ ምንም ምርጫ የለውም። ጠላት እየበለጠን፡ እያሸነፈን ነው። ከላይ እንዳልኳችሁ በሁሉም መድረክ ቦታ እየቆያየርን ካልተከላከልንና ካላጠቃን፡ አናሸንፍም። አናሸንፍም ብቻ አይደለም፡ ሽንፈታችን ራሱ በሚያሳቅቅ መልኩ ይሆናል። ሌሎች አድርገውታል። እኛም ልናደርገው እንችላለን። አሁን ትግል የያዝንበት መንገድ የሚያዛልቅ፡ ወይንም ፈረንጆቹ እንደሚሉት sustainable አይደለም። ከዚህና ከዚያ በሚለቃቀም ብር እንኩዋንስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ልናቆም፡ እንኩዋንስ፡ ዘረኝነትንና ጎሰንነትን የሚጥል ድርጅት ልንገነባ፡ ከራሳችን ጉሮሮ ለማለፍም ፍዳ ነው። ስለዚህ ጠንካራ የንግድና የባህል እንዲሁም የማህበራዊ ጉዳዮች መሰረትና ድርጅት ያስፈልገናል። በያመቱ የጀግኖች ምሽት፡ የሰማእታት ቀን፡ የአንድነት መድረክ እያልን ያለፈውን ብቻ ደግመን ደጋግመን ብንዘምረው ምን ይጠቅማል? ዛሬም ብናደርገው እንጂ። እነሆ የክብር ቀን ዛሬ ነው።
ዛሬ፡ በዋሽንግተን ዲሲ፡ ከጁላይ 1 እስከ 3 ቀን። በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ እንገናኝ። የፕሮግራማችንን ዝርዝርና ለበለጠ መረጃ እዚህ ላይ ይመልከቱ። http://ethiopianheritagesociety.org/ ለመረጃ 202-466-1677 ወይንም 713-545-6731 ወይንም Business Relations Officer 703-395-6067- Event Coordinator ይደውሉ። የዝግጅቱን ሙሉ መግለጫ፡ እዚህ ላይ ያንብቡት http://ethiopianheritagesociety.org/index.php/news/ ።
ሰኔ 30፡ 2011 ዓ.ም. ዋሽንግተን ዲሲ



