የኦታዋው ግልጽ ህዝባዊ ስብሰባ፡ በስውር ተጠናቀቀ
“የብሄር ድርጅቶችን፡ አቅርቦ መያዝ እንጂ፡ ሙሉ በሙሉ ማግለሉ አግባብ አይደለም” እኔ
“የብሄር ድርጅቶችን እንደውም መድረክ በመስጠት ማጠናከር ሳይሆን ማጥፋት ነው” አንድ ተሳታፊ
“የኢትዮጵያን አንድነት የማይቀበሉ የብሄር ድርጅቶችን እንደውም ወደፊት እንደወያኔ የምንዋጋቸው ናቸው” ዶ/ር ኤርሚያስ ዓለሙ
ልዩ ዘገባ - ልጅ ተክሌ (ኦታዋ-ካናዳ)
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2003 ዓ.ም. July 14, 2011):- እሁድ ጁላይ 24፡ 2011 ዓ.ም.፡ መቀመጫው በኦታዋ የሆነው፡ “የኢትዮጵያ ካናዳዊያን መድረክ ለዴሞክራሲ” (በእንግሊዘኛው “Ethio-Canadians Forum for Democracy”፡ ከፖለቲካ እስረኞች አንድነት ማህበር፡ ከኢህአፓና፡ ከዓለም-አቀፋዊው የፖለቲካ ድርጅቶች ትብብር ምስረታ አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በመተባበር፡ በኦታዋ ያዘጋጀው ስብሰባ የተለያዩ፡ ሀሳቦች ተንሸራሽረውበት ተጠናቀቀ። ዝግጅቱ ግን እንዳይቀረጽ መከልከሉ ጥቂቶችን አስቆጥቷል።
ከለንደን የፓርቲዎች ህብረት ምስረታውን የሚያስተባብረውን ስብስብ ወክለው የመጡት ዶ/ር ኤርሚያስ አለሙ የተገኙበት ዝግጅት ላይ ብዙ በኦታዋ ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተገኙ ሲሆን፡ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። የዝግጅቱን የኦታዋ አስተባባሪ ቡድን ወይንም ቡድኖች ወክሎ የተናገረው አቶ ዳዊት፡ ባገር ጉዳይ ላይ ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውንና ከዚህ ደረጃ የደረሱበትን ሁኔታ ገልጾ ሲያበቃ፡ መድረኩን ለእለቱ እንግዳ ለዶ/ር ኤርሚያስ ዓለሙ አስተላልፏል። እሳቸውም እያደረጉ ስላሉት የፖለቲካ ሀይሎች ትብብር ምስረታና ስለ መስፈርቶቻቸው፡ ስላጋጠሟቸው መሰናክሎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በሰጡት ማብራሪያ መሰረትም፡ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በማያወላውል መልኩ የሚቀበሉ፡ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ያላቸው፡ በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ምንም አይነት መድልዎችን የማያደርጉና፡ ሕወሀትን ለመጣል የቆሙ የፖለቲካ ድርጅቶችንና የሲቪክ ማህበራትን በማሰባሰብ ለመስራት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ኤርሚያስ በውይይቱ ላይ ለተነሱ ብዙ ጥያቄዎችም መልስ ለመስጠት ሞክረዋል። ከብሄር ድርጅቶች ጋር በተያያዘ፡ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እስከተቀበሉ ድረስ አብሮ ለመስራት ምንም ችግር እንደሌለባቸው፡ ከዚያ በተረፈ ግን፡ እንደ ኦነግና ኦብነግ ያሉ ድርጅቶች ግን፡ ባንድ በኩል እሳቸው “አፖሎጂስት” እና “ተላላኪ” ባሏቸው ድርጅቶች በኩል በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን ብለዋል እየተባለ፡ እያሉ፡ በሌላ በኩል ግን በድረ-ገጾቻቸው ላይ ኢትዮጵያ ቅኝ-ገዢ ነች እያሉ ሀሳባቸውን እንደሚያራግቡ፡ ስለዚህም ኢትዮጵያዊነታቸውን እስካልተቀበሉ ድረስ፡ አይደለም አብረን ልንሰራ፡ እንደውም እንዋጋቸዋለን ሲሉ ሌላ የትግል ግንባር ፈጥረዋል። በተለይ የኢህአፓ-ዲ አባላትም ይሄንኑ የሳቸውን ሀሳብ ሲያጠናክሩና አስረግጠው ሲያስረዱም ተስተውለዋል። በሌላው አንጻር፡ በእድሜያቸው ገፋ ያሉ አንድ ኢትዮጵያዊ አዛውንት፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቁጥር ከመብዛት ይልቅ፡ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን አስተያይተው፡ ቢዋሀዱና ወደአንድነት ቢመጡ መልካም ነው ሲሉ ምክር ሰጥተዋል። የኢህአፓ አባልና መሪ አቶ ጌታቸውና አቶ ሰሎሞን ድርጅቶች አንድ እንዲሆን የሚለው ሀሳብ የድርጅቶችን አሰራር ያላገናዘበና ለጊዜው የማያስፈልግ እንደሆነ አሳስበው፡ ከዚያ በተረፈ ግን ከብሄር ድርጅቶች ጋር በተያያዘ፡ ኢትዮጵያዊነትን ከማራመድ ውጪ የሚንቀሳቀሱትን ቦታ በመንፈግ ማጥፋት ነው እንጂ፡ ልክ ድሮ ለሻእቢያ ቦታ እንደሰጠነው፡ ለነዚህም ቦታ መስጠት፡ ነገ ሌላ ሬፈረንድም ላይ ይጥለናል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በእለቱ ዘወትርም እንደሚያደርገው ካሜራውን ይዞ ተሰብሳቢውን ሰይሆን ተናጋሪዎቹን ለመቅረጽ የገባው የዚህ ዜና ጸሃፊ፡ “ከዚህ ፊት የቀረጸውን ስላላስተላፈና፡ አሁንም ለምን እንደሚቀርጸው ስላልታወቀ፡ እንዲሁም የተሰብሳቢዎቹን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል፡ ዝግጅቱን መቅረጽ እንደማይችል ተገልጾለት ተከልክሏል።” በዚህም እጅግ በጣም አዝኖ፡ ሀዘኑንም “በዚህ ረገድ ከሕወሀት ብዙም አንለይም” ሲል፡ ገልጾላቸወዋል። በተጨማሪም ሀዘኑን በኩርፊአም ገልጿል። በተለይም ለዴሞክራሲያዊ ትግሉ ከአርባ አመት በላይ የታገለው ኢህአፓ ድርጅት አባላትና ከፍተኛ አመራር ያሉበት ስብስባ፡ ኢህአፓ ስሙ ላይ ዴሞክራሲን ካከለ በኋላ፡ አንዲህ ያለ ጸረ-ዴሞክራሲያዊ እግዳ ላይ መሳተፉ ትንሸ ግራ እንዳጋባው ገልጿል። የሆነ ሆኖ፡ ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ ተጠቃሎ፡ ህዝቡም ኢትዮጵያ ጥልቅና የከፋ ችግር ውስጥ እንዳለች አምኖ፡ አንድ ላይ ተባብሮ ለመስራት ተስማምቶ ተለያይቷል። ዝግጅቱ በቀጥታ በፓልቶክ የተላለፈ ሲሆን፡ የዚህ ዜና አቅራቢ ግን ስብሰባውን በድምጽ ብቻም ለመቅረጽ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ቀርቷል።
ነዋሪነቱ በኦታዋ የሆነና በስብሰባው ላይ የተገኘ አንድ የጅማ ተወላጅ፡ ስለስብሰባው በሰጠው አስተያየት፡ “ኢትዮጵያን ከሕወሀት አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ከሕወሀት የተሻልን ሆነን መገኘት እንዳለብንና፡ የብሄር ድርጅች ይሄንን ካላደረጉ አንቀበላቸውም የሚለው ቅድመ-ሁኔታ ያለበት አካሄድ ጎጂና ለነጻነት የሚታገሉ የብሄር ድርጅቶችንም በርቱ የሚያሰኝ ስለሆነ፡ በተለይ ትብብር ለመፍጠር ደፋ ቀና የሚሉ ሀይሎች የሚናገሩትን በጥንቃቄና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ቢያደርጉት መልካም ነው” ሲል አስተያየቱን ገልጿል። የዚህ ዜና አጠናቃሪ፡ ተክለሚካኤል አበበም ይሄንን ሀሳብ ይጋራል። በዚህና በመሰል የትብብር ሂደቶች ላይ ዝርዝር ዘገባ እናቀርባለን።



