የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ድርጅት አዲስ አመራር ኮሚቴ መረጠ

Ethiopia Zare (አርብ መስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም. September 12, 2011)፦ ላለፉት ሶስት አመታት በየአመቱ በተከታታይ ሲካሄድ የቆየው፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመከላከልና በማስጠበቅ ሲተጉ የኖሩ የጦር መኮንኖችንና ታጋዮች የሚሸልሙበት የጀግኖች ምሽት ዝግጅት እንደማይኖር አንዳንድ ውስጣዊ ምንጮች ገለጹ።

 

ድርጅቱ ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ በወደቀበትና የሽልማቱን አድማስ በማስፋት ሌሎች ከወታደራዊ ጦር ሜዳ ውጪም፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትና ያስጠበቁ እንደነ አክሊሉ ሀብተወልድ ያሉ ታላላቅ የሲቪል አርበኞችን፡ በሞቱበት ይሸልማል ብለው በተስፋ ሲጠበቅ፡ በዚህ አመት የሚያደርገውን ዝግጅት መሰረዙ እጅግ እንዳሳዘናቸው፡ አንዳንድ ዝግጅቱን በጉጉት ይጠብቁ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ተናግረዋል።

 

የዝግጅቱ አስተባባሪ ታዋቂው የአየር ሀይል ባለሟል አቶ ብርሀኑ ሞላን በስልክ አግኝተን ጠይቀናቸው፡ ዝግጅቱ እንዳልተሰረዘ፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ 2012 ሀምሌ ወር እንደተዛወረ የተናገሩ ሲሆን፡ ብዙ አስተያየት ሰጪዎች ግን፡ ጀግኖቻችን ከመቃብር ተኝተው ጀግኖችን የምናስብበትን ምሽት ሲሆን ሲሆን በየወሩ ማድረግ ሲገባን፡ ያመቱንም በሰበብ አስባቡ ወደመጪው አመት መግፋቱ አግባብ አይደለም ብለዋል። የሚመለከታቸው ሰዎች የጀግኖች ምሽት አዘጋጅ ኮሚቴን እንደሚያነጋግሩ እንጠብቃለን።

 

በሌላ ዜና፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ላይ በሰላሳ አምስት አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመውና፡ በተቋቋመ ጥቂት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት እንዲያንሰራራ ታላቅ ስራን እየሰራ ያለው የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብእ በሰሜን አሜሪካ፡ ለቀጣዮቹ አስራ ሁለት ወራት የሚያገለግሉትን የስራ አመራር አባላት መምረጡ ተገጸ። በዚህም መሰረት፡ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የህግ ባለሙያ፡ አቶ ሼክስፒር ፈይሳ ሊቀ-መንበርነቱን እንደያዘ ሲቀጥል፡ በሌሎች የአባልነት ስፍራዎች ላይ የሚያገለግሉትም አመራር አባላት ታውቀዋል። የረጅም ግዜ ተመሳሳይ የስራ ልምድ ያላቸው አቶ የሺጥላ ከባልቲሞር በዋና-ጸሀፊነት፡ ወ/ሮ ፊፊ ደርሶ ከአትላንታ በምክትል ለ/ምነበርነት፡ አቶ አበበ ሀይሉ ከካሊፎርኒያ በሕዝብ ግንኙነት ሀላፊነት፡ አቶ ሀይሌ ተፈራ በቢዝነስ አስተዳዳሪነት፡ እንዲሁም አቶ ያሬድ እሸቴ በዝግጅቶች አስተባባሪነት፡ እንዲሁም አቶ እስክንድር እዮብ በግምዣ ቤት ሀላፊነት ተመርጠዋል።

 

አመራሩ በዚህ አመትም የተነሳባቸውን አጀንዳዎች በትጋት እንደሚፈጽም፡ የማህበረሰቡን የማእከል ግንበታም እንደሚጀምር፡ በተመራጮቹ ስም አቶ ሼክስፒር ፈይሳ ተናግሯል። ማህበረሰቡ በሁለተኛው አመት የስራ ዘመኑ፡ ደርጅቱን የማስተዋወቅ ስራውን ተያይዞት፡ ባሳለፍነው ሳምንት በሎስ አንጀለስ፡ በኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን በዓል ላይ ራሱንና ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ እንደሰራ፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻም፡ በቶሮንቶ፡ በሂውስተንና፡ በባልቲሞር የህዝብ ግንኙነት ስራውን እንደሚቀጥልበት ታውቋል። በመጪው ቅዳሜም፡ በቨርጂኒያ፡ አርሊንግተን፡ Barcroft Park 4100 S. Four Mile Run Dr. (a community near D.C.). በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የአዲስ አመት የአገልግልና የሽርሽር መርሀ-ግብር እንዳዘጋጀ መግለጫው ይናገራል።

 

ከዚሁ ዜና ሳንወጣም፡ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ፌስቲቫል በየዓመቱ በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ የሚታወቅ ሲሆን፡ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ነጻነት ለማስጠበቅ የከፈሉት መስዋእትነት፡ አንዱና ዋንኛው አንገታችንን እንዳንደፋ ያደረገን ውርስ በመሆኑ፡ አያሌ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፡ የጀግኖች ምሽት በኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ድርጅት የዝግጅት መዝገብ ውስጥ እንደሚገባ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። የጀግኖች ምሽት አዘጋጅ ኮሚቴ በታዋቂ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመ አገር-ወዳድ ስብስብ ሲሆን፡ ከተቋቋመ ግዜ ጀምሮ፡ እነ ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም፡ ጃጋማ ኬሎ፡ ለገሰ ተፈራ፡ አሊ በርኬንና ሌሎች መሰል ኢትዮጵያዊ ጀግኖችን ሸልሟል።

ተከሌ፡ ጳጉሜን፡ 2004

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ