የኢሕአዴግ መንግስት 52 ቢሊየን ባለ100 እና 50 ብር ኖቶች ሊያሳትም ነው
ግሽበቱን ያባብሰዋለረ ተብሎ ተሰግቷል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም 6 ቀን 2004 ዓ.ም. September 17, 2011)፦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ 52 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አዳዲስ የመቶ እና የሃምሣ ብር ኖቶችን ሊያሳትም መዘጋጀቱ ተሰማ። በሀገሪቱ ታሪክ ይህንን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ ታትሞ የማያውቅ ሲሆን ለማሳተም ብቻ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ እንደሚፈጅ ተገምቷል።
አንዳንድ የመንግስት ምንጮች ገንዘቡን ማሳተም ያስፈለገው ስርጭት ላይ የነበሩ አሮጌ ብሮችን ለመተካት ነው ቢሉም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ምናልባትም 20% ብቻ ነው ለዚህ አገልግሎት ሊውል የሚችለው የቀረው ግን በቀጥታ ኢኮኖሚው ውስጥ ነው የሚገባው ሲሉ ለፎርቹን ጋዜጣ ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ እስከ ሰኔ 2002 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቃሽ ገንዘብ ውስጥ 21.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የመቶ ብር ኖቶችና 3.4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ባለ 50 ብር ኖቶች ብቻ ነበሩ።
ይሁንና በአዲሱ እቅድ መሰረት 46 ቢሊዮን ዋጋ ያላቸው የመቶ ብር ኖቶች እና 6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የ50 ብር ኖቶች እንዲታተሙ መፈለጉ እና ይህ የታቀደው አዳዲስ ብሮች ከታተሙ ከአጭር ጊዜ በኋላ መሆኑ፣ አላማው አሮጌ ብሮችን በአዲስ መተካት ብቻ ያለመሆኑን የሚያሳይ ሆኗል። ይልቁንም መንግስት ያወጣው በጀት በአንጻራዊነቱ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ አዳዲስ ኖቶችን እንዲያትም ካስገደዱት ምክንያቶች አንዱ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።
ይህንን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው አዲስ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ማስገባቱ በሀገሪቱ የነገሰውን የዋጋ ግሽበት ይብሱኑ ሊያባብሰው ይችላል ሲሉ የዘርፉ ምሁራኖች ስጋታቸውን አሰምተዋል።
በተለይም ገንዘቡ ወደ ኢኮኖሚው በአንድ ጊዜ እንዲገባ ከተደረገ በግሽበቱ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ያንኑ ያህል ከባድ ይሆናል ባይ ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ በቂ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ እስከሌለ ድረስ ከዋና ዋና ከረንሲዎች አንጻር የብር የምንዛሬ ዋጋ ይብሱኑ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ማክሮ ኢኮኖሚስቶች ፎርቹን ለተባለው ጋዜጣ ገልጸዋል። የብሔራዊ ባንክ ሪዘርቭ ባሳለፍነው የበጀት አመት 3ቢሊዮን ብር ብቻ እንደነበር ይታወቃል።
አዳዲሶቹን የብር ኖቶች ለማተም ሶስት ታዋቂ የገንዘብ አታሚ ኩባንያዎች የጨረታ ዋጋቸውን በሁለት ሳምንት ውስጥ ያስገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ አራተኛው የሆላንድ ካምፓኒ ግን በቴክኒካዊ ማጣሪያ ወቅት እንዲገለል ተደርጓል። ኖቶቹን ለማተም የብሔራዊ ባንክ የሚከፍለው ትክክለኛ ወጭ መታወቅ የሚችለው ከጨረታው በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ቢሆንም በአማካይ 30 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስወጣ ይገመታል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘም የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የሆኑት አቶ ጌታሁን ናና ከጥቂት ወራት በፊት ተጫራቾቹ ኩባንያዎች ወዳሉባቸው ፈረንሳይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ ተጉዘው ማተሚያ ፋብሪካዎቹን መጎብኘታቸው ይታወቃል። ገንዘቡ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።



