የአምባሣደር ዘውዴ ኃይለማርያም ሥርዓተ ቀብር በስቶክሆልም ተፈጸመ
Ethiopia Zare (ሰኞ መስከረም 15 ቀን 2004 ዓ.ም. September 26, 2011)፦ አምባሣደር ዘውዴ ኃይለማርያም በደረሰባቸው ሕመም ስቶክሆልም በሚገኘው ካሮሊንስካ ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላቸው ቆይተው ነኀሴ ፴ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. በ፹ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም ረቡዕ መስከረም ፲ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ሶልና በሚገኘው በኖራ ግራቭኒንግስ ፕላትስ ተፈጽሟል።
አምባሣደር ዘውዴ ኃ/ማርያም ሰኔ ፲ ቀን ፲፱፻፳፫ ዓ.ም. ከእናታቸው ከክብርት ወ/ሮ ለማወርቅ ተክለማርያምና ከአባታቸው ከስመ ጥሩ ጀግና ከልጅ ኃይለማርያም ማሞ በአዲስ አበባ ነበር የተወለዱት። ዕድሜአቸውም ለትምህርት እንደደረሰ የሀገራችንን ትምህርት ሲማሩ ከቆዩ በኋላ፤ ለዘመናዊ ትምህርት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው የተሰጣቸውን የቀለም ትምህርት አጠናቀዋል። ከዚያም ወደ እንግሊዝ ሀገር ለከፍተኛ ትምህርት ተልከው የሕግ ትምህርት ተምረው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ከእንግሊዝ ሀገር መልስ በመንግሥት ሥራ በመቀጠር በጡረታ ሚኒስቴር በፀሐፊነት፣ በመገናኛና ሥራ ሚኒስቴር የአውራ ጎዳና ኮሚሽነርነት፤ በመቀጠልም በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልክተኛ፣ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በምክትል ሚንስትርነት፣ በዮርዳኖስ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሣደር፣ በባህር ኃይል ክፍል መስሪያ ቤት በምክትል ሚንስትርነት፣ በመከላከያ ሚኒስቴር በምክትል ሚንስትርነት፣ በዴንማርክ፣ በፊላንድ፣ በኖርዌይ እና በስዊድን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሣደር ሆነው ሰርተዋል። በተለያዩ ሀገራት ለሀገራቸው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ወደሀገራቸው በመመለስ ባላቸው ማዕረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጡረታ እስተገለሉበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል።

በመጨረሻም ላለፉት ሰላሣ አራት ዓመታት በስዊድን ሀገር በስደት ኖረዋል። በዚህም ጊዜ ውስጥ ለአስራ ሦስት ዓመታት የስዊድን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጉዳዮች ኤክስፐርት በመሆን የሠሩ ሲሆን፣ በኢንተርናሽናል ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ስለሰብዓዊ መብቶች ጥናትም ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሰባዓዊ መብቶች በአፍሪካ በሚባለው ድርጅት ውስጥም ሊቀመንበር ሆነው እንዳገለገሉ ለመረዳት ተችሏል።
በማኅበራያዊ አገልግሎት በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን በስዊድን ሲቋቋም የምዕመናንን ስብሰባ ይመሩ የነበሩና፤ አሁን ያለው የመድኅኒዓለም ቤተክርስቲያን በዓለም ቤተክርስቲያን ታውቆ በማኅበር እንዲደራጅ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ያበረከቱ ናቸው።
እየዋዠቀ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታም የጠራና የተስተካከለ ጎዳና እንዲይዝ በግላቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር በመሰለፍ ጥረት ከማድረጋቸውም በላይ፤ የኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ተቆጣጣሪ ድርጅት (Ethiopian Good Gevernance Monitoring Authority) ማቋቋም አዲስ የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚሆንም መጠቆማቸውን ፕሮፌሠር ቴዎድሮስ ቬስታል በአድናቆት ጽፈውላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ ጥናት ያደረጉበትና በእውነተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክና አበይት ክንውኖችን የያዘ “በኢትዮጵያ ላይ ሲተኮር” (ኢንትሮስፕክት) የሚል የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ለሕትመት እንዲበቃ አድርገው ለተተኪው ትውልድ ትተዋል።
አምባሣደር ዘውዴ በሀገራቸውና በውጪ ሀገር ይሄን ሁሉ አገልግሎት ያበረከቱ ሲሆን፤ በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ ሀገራቸው ወደ እድገት ጎዳና እንድታመራ፣ የበለጸገች፣ ሠላምና ፀጥታዋ የተጠበቀ፣ የህዝብ መብት የተከበረባት እንድሆን ጥልቅ ምኞትና ፍላጎት ነበራቸው። ሆኖም ይህ ምኞትና ፍላጎታቸው ተሳክቶ የሚወዷት ሀገራቸውን ለማየት ሳይችሉ በስደት በቆዩበት ሀገር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አምባሣደር ዘውዴ እውነተኛን ነገር ለመፈለግ የሚጥሩ፣ ያመኑበትን ፊት ለፊት የሚናገሩ፣ ያልመሰላቸውን በግልጽ የሚቃወሙ ሰው አክባሪና ቀና ምግባር የነበራቸው ሰው እንደነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክራሉ።
አምባሣደር ዘውዴ ኃ/ይለማርያም የሁለት ወንዶችና የአንድ ሴት አባት ሲሆኑ፣ የልጆቻቸውንም ልጆች ለማየት የበቁ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ምንጊዜም ስማቸው ሲጠራ የሚኖረው የጀግናው የልጅ ኃይለማርያም ማሞ የበኩር ልጅ ነበሩ።
እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር! ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመድዶቻቸው መጽናናትን ይሰጥ ዘንድ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል ከልብ ይመኛል።



