300 የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስደተኞች በሀርጌሳ ታስረዋል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም 27 ቀን 2004 ዓ.ም. October 8, 2011)፦ የኢህአዴግ መንግስት በሱማሌ ላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ስደተኞች ታፍነው እንዲመለሱለት ትእዛዝ አስተላልፏል። በዚህም መሰረት እስካሁን 300 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአሰሳ ተይዘው በሀርጌሳ እስር ቤቶች ውስጥ የታጎሩ ሲሆን በቅርቡም ወደ አዲስ አበባ ይላካሉ ተብሏል።

 

ሀርጌሳ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን አሳልፋ እንድትሰጥ ኢህአዴግ ግፊት ሲያደርግባት የቆየ ቢሆንም የቀድሞው የሶማሌ ላንድ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሙሐመድ አብዲ ጋቦሳ ግን ተጽእኖውን ተቋቁመው መቆየታቸው ነው የሚነገረው።

 

ይሁንና በቅርቡ “አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁማለሁ” በሚል ከስልጣናቸው በፈቃዳቸው የለቀቁ ሲሆን በምትካቸውም ሙሐመድ ኑር ሀራሌ አዲሱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስተር ተብለው መስከረም 1 ቀን ተሹመዋል።

 

ሶማሌ ላንድ ከ1991ዓ.ም ጀምሮ ነጻነቴን አውጃለሁ ብትልም ከኢትዮጵያ በቀር አንድም እውቅና የሰጣት ሀገር እንደሌለ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ግን የቆንሲላ ቢሮ ከፍታ ከመስራቷም በላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሀርጌሳ ውስጥ ቅርንጫፍ ከከፈተ አመታት አስቆጥራል።

 

የኢህአዴግ መንግስት በሀርጌሳ ላይ ተጽእኖ ሲያሳድር የቆየ መሆኑ ሲታመን ግፊቱን መቋቋማቸው የሚነገርላቸው ዶ/ር ሙሐመድ ስልጣናቸውን በለቀቁበት ወቅትም በምትካቸው ፍላጎቱን የሚያሟሉለት ሰው እንዲሾሙ በፕሬዝዳንቱ ላይ ተጽእኖ አድርጓል የሚያሰኙ ምልክቶች ታይተዋል ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች ጥርጣሬያቸውን አሰምተዋል።

 

በተለይም 500 የኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ እስረኞችን ስም ዝርዝር የያዘው የ”አስራችሁ ላኩልኝ” ጥያቄ ለሱማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ለአህመድ መሀመድ ሰላንዮ የደረሳቸው ሴፕቴምበር 1ቀን ሲሆን አዲሱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርም የተሾሙት በዚሁ እለት መሆኑ የአጋጣሚ ጉዳይ አይመስልም ባይ ናቸው ተችዎቹ።

 

ፕሬዚዳንት ሴላንዮ አዲሱን ሹመት የሰጡት ከቻይና ጉብኝታቸው መልስ ሲሆን በወቅቱ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ተገናኝተው የበርበራ ወደብን ግንባታና አጠቃቀም በተመለከተ በቻይና፣ በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ መሀከል የሶስትዮሽ ውል ተፈራርመው ነበር። ምናልባትም በሀገራቸው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ስደተኞችን አሳልፈው እንዲሰጡ ግፊት የተደረገባቸው በዚሁ የቻይና ጉብኝታቸው ወቅት ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።

 

አዲሱ ሚኒስተር እንደተሾሙና የኢህአዴግ ደብዳቤ በደረሰ በ3ኛው ቀን የሀገሪቱ ምክትል የአገር ውስጥ ሚኒስተር የሆኑት ኦስማን ጋራድ ሶፌ “በሀገራችን የሚገኙ ስደተኞች በሙሉ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደየመጡበት ይመለሳሉ” የሚል ይፋ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

 

ወዲያውም አዲሱ ሚኒስትር ሙሐመድ ኑር አራሌ ለፖሊስና ለደህንነት መስሪያ ቤታቸው በሰጡት ትእዛዝ መሰረት የኢህአዴግ መንግስት ይያዙልኝ ያላቸው 500 የፖለቲካ ስደተኞች እየተለቀሙ ታስረዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ብቻ 300 ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ስደተኞች በሶማሌ ላንድ መታሰራቸው ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ