ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን በዚምባብዌ እስር ቤቶች ይደበደባሉ

Ethiopia Zare (ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2004 ዓ.ም. October 27, 2011)፦ የኮ/ል ጋዳፊን ሞት ተከትሎ በዚምባብዌም የቀድሞው መሪ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም የደህንነነት ጥበቃ ጉዳይ ህዝቡን እንደ አዲስ ማነጋገር ጀምሯል።

 

 

‘ዘ ዚምባቢያን’ የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በረሀብ እየማቀቁ ባለበት ሰአት መንግስት ከፍተኛ ወጭ እያወጣ ለቀድሞው የኢትዮጵያ አምባገነን ወደር የለሽ ጥበቃ ማድረጉ ተገቢ አይደለም ሲሉ የኮ/ሉ ጎረቤቶችና ሌሎች የህብረተሰቡ አባላት ድምጻቸውምን እያሰሙ ነው። ይሁንና ጋዜጣው የኮ/ሉን ቪላ ጎብኝቶ የጥበቃ ደረጃው ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን አረጋግጧል።

 

ኮ/ሉ ካሁን ቀደም ጋንሂል ከሚገኘው ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት ቪላቸው በአጠያያቂ ሁኔታ መረጃዎች (ደኩመንቶች) መሰረቃቸውን የሚያስታውሰው ይህ ዘገባ መረጃወቹ በአዲስ አበባ በሌሉበት ከተመሰረተባቸው ክስ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ነበሩ ብሏል።

 

በታህሳስ 1987 ዓ.ም በሌሉበት በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ኮ/ል መንግስቱ በወቅቱ የሮበርት ሙጋቤ የወታደራዊ ጉዳዮች አማካሪ እንደነበሩ ሲዘገብ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ አሳልፌ አልሰጥም በማለታቸው የአገሪቱ ማእከላዊ የመረጃ ቢሮ (IOC) ከጦሩና ከፖሊስ ጋር በመተባበር ኮ/ሉን ‘ከአንዳንድ ድንበር ዘለል ተበቃዮች ለመከላከል’ በሚል ጥበቃቸውን ለማጠናከር ተገደው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከሻቢያና ወያኔ እንደተላኩ የሚጠረጠሩ ሁለት ሰዎች ድንበር ዘለው በመሻገር ኮሎኔሉን ለመግደል ያደረጉት ሙከራ ከሽፎ በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር በወቅቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ነጻ መገናናዎች መዘገቡ ይታወሳል።

 

ከዚሁ ጋር በተያያያዘም ዛሬም ድረስ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማለፍ ዚምባቡዌን የሚያቋርጡ ኢትዮጵያዊያንን የሙጋቤ መንግስት በክፉ አይን ነው የሚያያቸው ሲል ምስክርነቱን የሰጠው ይሄው ‘ዘ ዚምባቢያን’ የተሰኘው ጋዜጣ በርካቶቹ ኢትዮጵያዊያኖች እየታሰሩ ‘መንግስቱን ለመግደል ነው ወይ የመጣችሁት?’ በሚል ድብደባና ምርመራ እንደሚደረግባቸው አጋልጧል።

 

ጋዜጣው በዘገባው ማጠቃለያ ላይ በ1983 ዓ.ም አምባገነኑን መንግስቱን ገልብጦ ስልጣን የያዘው የኢትዮጵያ መንግስት በተመሳሳይ ጭካኔ ህዝቡን ረግጦ እየገዛ መሆኑን ሳይጠቅስ አላለፈም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ