የሰወነት አካላቸው በጥቁር ገበያ ይቸበቸባል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2004 ዓ.ም. November 5, 2011)፦ በግብጽ በኩል አቋርጠው ወደ እስራኤል ሀገር ለመሻገር የሚሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ሱዳናዊያን ስደተኞች የሰውነት አካላቸው እየተሰረቀ እሬሳቸው በበረሃ ውስጥ እንደሚጣል ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በመረጃ አረጋገጡ።

 

 

“ዘ ኒው ፋውንዴሽን ፎር ሂዩማን ራይት” እና “ዘ ኤቭሪ ዋን ግሩፕ” የተባሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ያቀረቡት መረጃ እንደሚያሳየው በመቶ የሚቆጠሩ የኢትዩጵያና የሱዳን ስደተኞች አስከሬን በሲናይ በረሃ ደረቅ የውሃ ጉድጓዶች ውስጥ ተጥሎ የተገኘ ሲሆን የኩላሊትና ጉበት ስርቆት እንደተፈጸመባቸውም ተረጋግጧል።

 

እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ መግለጫ ከሆነ ስደተኞቹ ወደ እስራኤል ለመሻገር የተጠየቁትን ያህል ገንዘብ ማቅረብ ካልቻሉ በባርነት እንደሚቆዩ፣ ድብደባ እንደሚፈጸምባቸውና ሴቶቹም በአስገድዶ መድፈር እንደሚጠቁ አትቷል።

 

በግብጽ በኩል ወደ እስራኤል ለመሻገር አመቺው መንገድ በሲናይ በረሃ ማቋረጥ ሲሆን በአካባቢው በብዛት የሚንቀሳቀሱትና ከወንጀሉም ጋር ተዛምደው የተጠቀሱት የሳዋርካ ቤዶይን ጎሳዎች ናቸው።

 

ይህንኑ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው የሳዋርካ ጎሳ መሪ ስደተኞቹን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ እስራኤል የሚያሻግሩ ሰዎች እንዳሉ አንዳንዴም ግርፊያና እንግልት እንደሚፈጸም እንደሚያውቁ አምነው ይሁንና ይህንን የሚፈጽሙት አንዳንድ ወንጀለኞች በግል እንጂ በተቀናጀ ሁኔታ በጎሳቸው በኩል የሚፈጸም እንዳልሆነ አስተባብለዋል።

 

የግብጽ የወደብ ከተማ ከሆነችው አል- አሪሽ የሬሳ ማቆያ ቦታ የተገኙ ፍቶግራፎች ስደተኞቹ የቀዶ ጥገና እንደተደረገላቸው በግልጽ ያሳያሉ። ይህም የተፈጸመው ህይወታቸው ከማለፉ አስቀድሞ ስለመሆኑ የ”ኒው ጀኔሬሽን ፋውንዴሽን” መሪ የሆኑት ሀምዲ አል- አዛዚ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

 

“የሰውነት ብልቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉት ሰዎቹ በህይወት እያሉ ከተወሰደባቸው ብቻ ነው” የሚሉት ሀምዲ አዛዚ “ስደተኞቹን በመጀመሪያ ያደነዝዟቸዋ፤ ከዚያም የሰውነት አካሎቻቸውን በመስረቅ እንዲሞቱ ይተዋቸውና ከመቶ ከሚቆጠሩ ሌሎች ሰለባዎች ጋር በደረቁት የውሃ ጉድጓዶች ውስጥ ይጥሏቸዋል።” ሲሉ ያብራራሉ።

 

ይህንን ለመሰለው የጭካኔ ድርጊት አይነተኛ ተጠርጣሪ የሆኑት በጥቅም የታወሩ አንዳንድ የግብጽ ዶክተሮች ሲሆኑ ወደ በረሃ ተጉዘው በዘመናዊ መልክ በተደራጁ ተንቀሳቃሽ የህክምና ክሊኒኮች በመጠቀም ቀዶ ጥገናውን ፈጽመው ካይሮ ወደሚገኙ የግል ክሊኒኮቻቸው ይመለሳሉ ነው የተባለው።

 

የቀድሞው የካይሮ ፎርሰኒክ ዲፓርትመንት ኃላፊና በህጉ ውስጥ የሰውነት አካል ንግድ ጉዳይ ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ፍክሪ ሳኪ የቀዶ ጥገናው ኩላሊትና ጉበት በሚገኙበት የሰውነት ክፍል ላይ በወጉ የተሰራ መሆኑን በመግለጽ በዶ/ሮቹ ላይ ያደረውን ጥርጣሬ ከፍ አድርገውታል።

 

ይህ ህገ ወጥ የሰውነት አካል ንግድ ከአደንዛዥ እጽ ንግድ የላቀ ገቢ የሚያስገኝና ከጦር መሳሪያ ንግድ ቀጥሎ ትልቁ የወንጀለኞች የገቢ ምንጭ ስለመሆኑም ዶ/ር ፍክሪ ሳኪ አብራርተዋል።

 

በቅርቡ የሲ.ኤን.ኤን ጋዜጠኞች ያነጋገሩት አንድ የቀድሞ የወንጀል እንቅስቃሱው አካል የነበረ ግለሰብ እንዳስረዳው ከሆነ ዶክተሮቹ በቀጥታ ከሳዋርካ ተወላጆች ጋር እንደሚደራደሩና ለአንድ የሰውነት አካልም ከ20ሺህ የአሜሪካን ዶላር ጀምሮ እንደሁኔታው ከዚያም ከፍ ያለ ገንዘብ እንደሚከፍሉ ይታመናል።

 

ይሁንና የአካባቢው ባለስልጣናት እስከአሁን ድርስ አንድም ለወንጀሉ ተጠያቂ መሆን የሚችል ሰው ይዘው ለህግ አላቀረቡም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ