ናትናኤል መኮንን ክፉኛ መደብደቡን ለፍርድ ቤት ገለጸ

Ethiopia Zare (ሐሙስ ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. November 10, 2011)፦ ልደታ በሚገኘው በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ የቀረቡት ስምንት ተከሳሾች መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጎ አንድ ላይ በካቴና ተጠፍረው መቅረባቸውና የአንድት ፓርቲ ምክር ቤት አባል የሆነው ናትናኤል መኮንን በፖሊሶች ክፉኛ መደብደቡን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

ዛሬ ሀሙስ በሽብርተኝነት ክስ ከቀረበባቸው 24 ሰዎች መካከል በውጭ ሀገር የሚኖሩትን የግንቦት 7 አመራር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ መስፍን አማን፣ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ አቶ ንአምን ዘለቀ እና ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለምን ጨምሮ አርቲስት አበበ በለው የተካተቱ ሲሆን በሀገር ውስጥ ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡት ተከሳሾች ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን ገ/ኪዳን፣ አቶ ዮሃንስ ተረፈ ከበደ፣ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ በረደድ፣ አቶ ምትኩ ዳምጠው ውርቁ፣  አቶ አንዱዓለም አያሌው ይገኙበታል።

 

35 የሰው ምስክሮችንም አቃቢ ህግ እንደሚያቀርብ ይፋ ያደረገ ሲሆን የምስክሮቹን ስም ዝርዝር ለደህንነታቸው ሲባል እንደማይሰጥ የገለጸ ሲሆን ለሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ህዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ማስረጃዎችን አጠናክሮ እንደሚያቀርብ ገልጿል።

 

 

ተከሳሶቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ህዳር 5 ቀን የሚያሰሙ ከመሆኑም በላይ የአንድነት ፓርቲ ምክር ቤት አባል በሆነው ናትናኤል መኮንን ላይ ከፍተኛ ስቃይ ያለበት ድብደባና እንግልት እንደደረሰበት ለፍርድ ቤቱ ያሰማው አቤቱታም በቀጣይ ቀጠሮ ይታያል ከማለት ውጭ ፍርድ ቤቱ ትኩረት እንዳልሰጠበት በስፍራው የተገኙ የአይን ምስክሮች  በሰጡት ቃል ለመረዳት ተችሏል።

 

በተያያዘም በእነ ኤልያስ ክፍሌ ክስ መዝገብ ስር የተከሰሱት አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ርዮት አለሙ፣ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር እና ሂሪት ክፍሌ ላይ አቃቢ ህግ ምስክሮቹን ማሰማት የጀመረ ሲሆን አብዛኞቹ ምስክሮች አድራሻ የሌላቸውና ቋሚ ስራ ሳይኖራቸው በየቦታው የራሳቸውን ኑሮ ለማሰነፍ የሚፍጨረጨሩ ወጣቶች መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ተከሳሾቹ ገንዘብ እከፈሉን ወረቀት በትነናል የሚል ጭብጥ ያለው ምስክርነት ማሰማታቸው ታውቋል።

 

በ1997 ዓ.ም በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር በአገዛዙ እስር ቤቶች ቁጥጥር ስር የነበሩ የቅንጅት አመራር አባላት ላይ አቃቢ ህግ ያቀረበው ምስክር ‘በል ብለውኝ ነው እንጂ የማውቀው ነገር የለም’ በማለቱ አይዘነጋም።

 

በእነ አርቲስት ደበበ እሰቱ ነገ ህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም በተያዘው ቀጠሮ አቃቢ ህግ የምስልና የጽሁፍ ስራዎችን ትርጉም በማስረጃነት እንደሚያቀርብ ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ