ጋዜጠኛ አበበ ቶላ (አቤ ቶክቻው) ወደ ኬንያ ተሰደደ
አቤ ቶክቻው በየሳምንቱ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለዛ ባለው መጣጥፎቹ የብዙ አንባቢያንን ልብ የሳበ ብርቱ ጋዜጠኛ ሲሆን ጽሁፎቹ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ በርካታ አንባቢያን ጋር ይደርሱ እንደነበር ይታወቃል።
አበበ ቶላ ሰሞኑን የደህንነት ሰዎች ይከታተሉት እንደነበርና በአዲሱ የሽብርተኛነት ህግ የሚከሰሱ እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በፓርላማቸው ዛቻ ከተፈጸመባቸው የወደፊት ታሳሪዎች አንዱ እንደሆነ ጥቆማ እንደደረሰውና ክትትሉ ስለበረታበት ሀገሩን ጥሎ ለመውጣት እንደተገደደ ለመረዳት ተችሏል።
አቤ ቶክቻው አንድ የደህንነት ሰራተኛ በተደጋጋሚ ቢሮው ድረስ በመዝለቅ 'ከከሰሩ የውጭ ሀገር ፖለቲከኞች ጋር ትገናኛለህ - በዚህም የሀገር ስጋት ሆነሀል በማለት እንዳስፈራራውና በተከታታይ በጽሁፎቹን እንዲያቆምና ከመንግስት ጋር አብሮ እንዲሰራ እንደጠየቀው ለአውራምባ ታይም ጋዜጣ ገልጾ እንደነበር አይዘነጋም።
መጣጥፎቹን በፍትህ ጋዜጣ የጀመረው አቤ ቶክቻው ‘ከእንግዲህ በኋላ አለቆቼ ሊከሱህ ተዘጋጅተዋል አብረህ ከመንግስት ጋር የማትሰራ ከሆነ የራስህ ውሳኔ ነው’ የሚል ማስጠንቀቂያ ከዚሁ የደህንነት ባልደረባ እንደደረሰው ለመረዳት ተችሏል።
አቤ ቶክቻው (አበበ ቶላ) በአሁኑ ሰአት በኬንያ ለደህንነቱ አስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይ በኬንያ የኢህአዴግ የመረጃ ሰዎች በህይወቱ ላይ አደጋ ሊያደርሱበት ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩን ምንጮቻችን ስጋታቸውን አክለው ገልጸዋል



