የመምህር የኔሰው መስዋእትነት ተዘከረ፡ ሁለት ወጣት ምሁራን የጥናት ስራዎች አቀረቡ

Ethiopia Zare (አርብ ኅዳር 8 ቀን 2004 ዓ.ም. November 18, 2011)፦ አድባር በመባል የሚታወቀው የውይይትና ክርክር ክበብ በቶሮንቶ የተሳካ ውይይት ከማድረጋቸውም በላይ ‘ፍትህና ነጻት በሌለበት ሀገር መኖር ሰለቸኝ” በማለት ራሱን በእሳት ያቃጠለው መምህር የኔሰው ገብሬ መስዋእትነት በታላቅ ሁኔታ ተዘከረ።

 

ብዙዎቻችን ልጆቼን፡ ትምህርቴንና፡ ስራዬን እያልን የሚጠበቅብንን ብሄራዊ ግዴታ ላለመወጣት እግራችንን ወደኋላ መጎተታችን የተለመደ ነው። ፋሲካ ወልደሰንበት ግን ሁሉንም ባንድ ላይ ከማስኬድ ምንም ነገር ያላገዳት ታላቅ አገር-ወዳድ ወይዘሮ ነች። በላይዋ ላይ ብዙ የቤት ስራዎች ቢከመሩባትም፡ የአገሯ ጉዳይ ዘወትር ስለሚያንገበግባት፡ ከጓደኞቿ ጋር ሆና የዛሬ አራት ወር አካባቢ አድባር የክርክር ክበብን አቀቋመች። እነሆ ባለፈው ማክሰኞ፡ ኖቬምበር 15፡ አመሻሹ ላይ፡ መቀመጫው ቶሮንቶ የሆነው አድባር የክርክር ማህበር፡ ከቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የኤኩቲ ጥናት (Equity Studies) ተማሪዎች ጋር በመሆን በዊሊያም ዶ አዳራሽ ያዘጋጁት፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት ረገጣና የዘር ማጥፋት ወንጀል፡ እንዲሁም የምእራባዊያን ዝምታና የቻይና ግብረአበርነት የተወያየ የመጀመሪያው የሶስት ሰኣት ውይይት በድል ተካሄደ።

 

የመጀሪያው ተናጋሪ፡ የኦጋዴኑ ተወላጅ፡ አንደበተ ርትኡ መሀመድ ሀሰን መድረኩን ከመያዙ በፊት፡ የዩኒቨርስቲው የኢኩቲ ጥናት ሀላፊ ፕሮፌሰር ጁን ለርኪን የመግቢያ ንግግር አደረጉ። የማናልፈው፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስከፊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጣሪያ እንደነካ መገለጫ የሆነው ክስተት ከሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ተከስቶ ነበርና፡ ከፕሮፌሰር ለርኪን ቀጥሎ ያንን ማንሳት የግድ ነበር። የመምህር የኔሰው ገብሬ ሞት። የቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችውና የቤናጋሊዋ ተወላጅ ወጣት ዶያሊ ስለየኔሰው ገብሬ ሞት የሚያትተውን የእንግሊዘኛ ዜና አነበበች። የኔሰው ገብሬ፡ በተለይ በዋካ አካባቢ፡ በጠቅላላው ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ በደልና ኢፍትሀዊነት በመቃወም በከተማው አስተዳዳሪዎች ፊት ራሱን በእሳት አቃጥሎ እንዳጠፋ የሚያትተውን ዜና ዶያሊ በምታነብበት ግዜ፡ በአዳራሹ ውስጥ የነበረው ተሳታፊ በሙሉ በሀዘን ተደፋ። የስብሰባው ኡደት በዚ ዜና ተቃኝ። መሀመድ ቀጠለ።

 

መሀመድ ሀሰን መድረኩን ይዞ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ፡ በተለይም በኦጋዴን አካባቢ በሕወሀት/ኢህአዴግ አስተዳዳር እየተፈጸመ ስላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል  በሰፊው ተናገረ። መሀመድም እንዲህ አለ፡ “በኦጋዴን አካባቢ፡ ከዚህ በፊት በነበሩ መንግስታተም ብዙ ግፎች ተፈጽመዋል። የአሁንን ስርአት ግፍ ልዩ የሚያደርገው ግን፡ ሰዎችን ከማሰርና ከማሰቃየት አልፎ፡ በሽቦ አንቆ በመግደል፡ ዛፍ ላይ ለቀናት ሰቅሎ እንዲሞቱና እንዲበሰብሱ ማድረጉ፡ እንዲሁም ወጣቶችንና ባለቴቶችን ሰይመርጥ አስገድዶ መድፈሩ” ነው ብሏል። ይሄ በንጉሱም በደርግም አገዛዝ ግዜ አልተፈጸመብንም ሲል በምሬት ተናግሯል። በተለይም እ.አ.አ. በ2007 ዓ.ም፡ የህወሀት አገዛዝ ኦቦሌ (Cobole) በሚባለው ለም አካባቢ ያለውን የኦጋዴን ህዝብ አፈናቅሎ ቦታውን ለቻይና ነዳጅ ፈላጊዎች ሲሰጥ፡ ያንን የተቃወሙ የአካባቢው ታጣቂዎች ሰባ የቻይናና የዌአኔ ሰዎችን ከደገሉ በኋላ፡ በአካባቢው ህዝብ ላይ የሚያደርሰው  ሰቆቃ ለከት እንደሌለው ከሰቆቃው ተርፈው በወጡ ሰዎች ምስልና በበማስረጃ አስደግፎ ተናግሯል።

 

ከመሀመድ ቀጥሎ፡ አንዱ የአድባር መስራች የሆነው ወጣት ድሜጥሮስ ብርቁ የአድባርን አቋም የሚያንጸባርቀውንና በኢትዮጵያ ውስት እየተፈጸመ ላለው ግፍ ምእራባዊያን እያሳዩ ያለውን ፍትሀዊ ያልሆነ ቸልተኝነት አጥብቆ የሚተች ጽሁፍ አቅርቧል። ድሜጥሮስ፡ ምእራባዊያን ቸል ማለት ብቻ ሳይሆን፡ እንዲያውም የሕወሀትን መንግስት በገንዘብና መቁሳቁስ በማገዝ በተዘዋዋሪ የወንጀሉ ተባባሪ እንደሆኑ ለማሳየት ሞክሯል። በተጨማሪም መሀመድና ድሜጥሮስ፡ በዚህ ሁሉ የሰብአዊ መብት እመቃ ውስጥ የቻይናን አብይ ሚና አልዘነጉም። ሁለቱም ተናጋሪዎች ከቤቱ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተውላቸው ለበር። ስለኦጋዴንና የተቀረው ኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትም  ከቤቱ አስተያየት ተሰጥቷል። መሀመድ በኦጋዴን ላይ ያተኮረው ስለአካባቢው በደንብ ስለሚያውቅ እንደሆነ እንጂ፡ በኦጋዴን የሚደረገው በደቡብም፡ በጋምቤላም እንደሚደረግ አስረድቶ፤ በተጨማሪም በምርጫ 97 የተደረገውን ጭፍጨፋና የሊቢያን ምሳሌ አጣቅሶ የጭቆናውን ብሄራዊነት አስረድቷል። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በቤንጋዚ 193 ሰዎች ሲሞቱ ጣልቃ ለመግባት የወሰኑት ምእራባዊያን ግን፡ በኢትዮጵያም በምርጫ 97፡ በአዲስ አበባ ብቻ 193 ሰዎች ሲሞቱ ምንም አለማለታቸው የምእራባዊያንን ወላዋይነት ያሳያል ብሏል።

 

ሌላው የአድባር መስራች ዳንኤል ጥላሁን ምእራባዊያን መንግስታት በተባበሩት መንግስታት ቻርተር መሰረት የዘር ማፋጥትን የማስቆም፡ ውል እንደገቡና ሀላፊነት እንዳለባቸው እንዳለባቸው፡ ያንን አለማድረጋቸወም ሀላፊነታቸውን እንዳለመወጣት እንደሚቆጠር ተናግሯል። በመጨረሻም፡ ተሰብሳቢው የካናዳን መንግስት የሚነዘንዝና በካናዳዊያን ዘንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት ገፈፋና ጭቆና የሚያነቃ የፈቃደኞች ስብስብ አቋቁሞ በድል ተጠናቋል።

 

የስብሰባውን ቅንጫቢ እዚህ http://www.youtube.com/watch?v=MLE5CXUo3Bc እና http://www.youtube.com/watch?v=8tv8IVsT9CI ተመልከቱ።

 

ከቶሮንቶ ለተጠናቀረው ዘገባ፡ ተክለሚከኤል አበበ። ኖቬምበር። 2011

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ