የኢሕአዴግ መንግስት ለአምባሳደሩ መታሰር በቂ መልስ አላቀረበም
“የዓለም አቀፍ ህግጋትን ጥሰዋል” የስሎቫክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር
Ethiopia Zare ( ቅዳሜ ኅዳር 9 ቀን 2004 ዓ.ም. November 19, 2011)፦ አጠያቂ በሆነ መልኩ በኢህአዴግ ታጣቂ የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ለ3 ቀናት በእስር የቆዩትን አምባሳደር በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እጅግ ዘግይቶ የሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም ሲሉ የስሎቫክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አወገዙ።
በአዲስ አበባ የስሎቫክ አምባሳደር የሆኑት ሚላን ዱቼክ ከመኖሪያ ቤታቸው በቅርብ ርቀት ላይ የታሰሩት ባለፈው ኖቬንበር 5 ቀን ሲሆን ለአገራቸው መንግስት ሳይገለጽ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በእስር እንዲያሳልፉ መደረጉ በስፋት ሲያነጋግር መሰንበቱ ይታወሳል።
የአምባሳደሩ መታሰር ሊታወቅ የቻለው ሰኞ ኖቬንበር 7 ቀን 2004 ዓ.ም በስራ ገበታቸው ላይ ሳይገኙ በመቅረታቸው ኢምባሲያቸው “የደረሱበት አልታወቀም” የሚል ሪፖርት ካሰማ በኋላ ነበር።
የስሎቫክ መንግስት ሁነቱን በማውገዝ አምባሳደሩን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከመጥራቱም በላይ ድርጊቱ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ግንኙነትን በተመለከተ በ1961 የተፈጸመውን የቪየና ስምምነት የተላለፈ ነው። በሚል አጠንክሮ ሲያወግዝ ሰንብቷል።
አምባሳደር ዱብቼክም ያለመታሰር ዲፕሎማቲካዊ መብታቸው ተገፎ ለ3 ቀናት የታፈኑበት ምክንያት እንዳልገባቸውና አንዳችም የሀገሪቱን ህግ የሚጥስ ተግባር መፈጸማቸውን እንደማያውቁ ገልጸዋል።
የስሎቫክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኩስ ዙሪንዳ የኢትዮጵያ መንግስት የዲፕሎማቲክ ህግን ተላልፎ ለምን አምባሳደራቸውን እንዳሰረ እንዲያብራራላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ዘግይቶም ቢሆን የደረሳቸው ቢሆንም ምላሹን “የሚያረካ አይደለም” ሲሉ አጣጥለውታል።
ይህ በጀርመን ስሎቫክ አምባሳደር በኩል የተላከላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ “ስህተት ስለመስራታቸው የሚጠቁሙ ቃላት ቢኖሩትም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው እንደሚጠበቀው ይፋዊ ይቅርታ ባለመጠየቋ በድጋሚ ለማውገዝ ተገደናል” ብለዋል።
“አምባሳደሩን በማናቸውም አይነት መልኩ ቢሆን ሊያስሩት አይገባም ነበር። እርምጃው የአለም አቀፍ ህግጋትን የጣሰ ነው።” የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አባል አገራት ሁኔታው እንዳሳሰባቸውና ከእኛ ጋር ያላቸውን የአቋም አንድነት ግልጽ አድርገዋል።” ብለዋል።



