የኢትዮጵያ ጦር በድጋሚ ወደ ሶማሊያ ሊዘምት ነው
“ፕሬዝዳንቱ አልፈለጉም” የሶማሊያ ባለስልጣን
“ተጠቃሚው አል-ሻባብ ነው” የፖለቲካ ተንታኞች
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 9 ቀን 2004 ዓ.ም. November 19, 2011)፦ የሶማሊያ አብዛኛውን ክልል የተቆጣጠረውና ከአልቃይዳ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው የሚባለውን አል-ሻባብን ለመመንጠር፤ የአፍሪካ ህብረት በድምሩ 10 ሺህ የሚገመት ጦር ለመላክ እየሞከረ ሲሆን የኢትዮጵያን ጦር ተሳትፎ በተመለከተ ግን ካሁኑ አወዛጋቢ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
በአሁኑ ወቅት በህብረቱ መለዮ ስር ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት 9700 የብሩንዲና የኡጋንዳ ወታደሮች ሲሆኑ በተናጠል ደግሞ የኬንያ ወታደሮች በቅርቡ መዝመታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ጦር በአሜሪካን ሁነኛ የጀርባ ድጋፍ ሶማሊያን በ2006 ዓ.ም ወርሮ እንደነበር ሲታወስ በከተሞች ላይ ይወስድ በነበረው የጅምላ ጭፍጨፋ ሳቢያ በሺህ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች በመገደላቸው፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ጸረ ኢትዮጵያ ስሜት እንዲያብብ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም አል-ሸባብ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ እድል በማግኘቱ በርካታ አዳዲስ አባላትን ለመመልመል አብቅቶታል።
በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር በገባበት እግሩ እንዲወጣ ዋንኛው ምክንያት ይህ እንደነበር ያስታወሱት ሰሞኑን ለንባብ የበቁ የተለያዩ አለም አቀፋዊ የዜና ዘገባዎች አሁን ደግሞ ‘በሺህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ዳግም ሶማሊያ ሊገቡ ነው’ የሚለው ዜና እያወዛገበ ስለመሆኑ ዘግበዋል።
ኢትዮጵያ ሶማሊያ ላይ ያደረገችውን ወረራ በተመለከተ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ፖሊሲያችን ስህተት ነበር” ሲሉ ፓርላማቸው ውስጥ በይፋ ማመናቸውና በፓርላማ ወረራውን ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩትን የኢዴፓውን አቶ ልደቱ አያሌውን ሳይቀር ማሳፈራቸው አይዘነጋም።
የሶማሊያ መንግስት አንድ ባለስልጣን ለኒው ዮርክ ታይምስ ዘጋቢ እንደገለጹት ከሆነ በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ሰራዊት ድንበር እየተሻገረ ሲሆን ይህም ለሶማሊያ ፕሬዝዳንት ለሼክ ሸሪፍ አህመድ ምቾት ያልሰጠ ጉዳይ ሆኗል።
“ባለፈው ወረራ ወቅት በፈጸማቸው ከፍተኛ የጭካኔ ተግባራት ሳቢያ ሰፊ የህዝብ ጥላቻ በማትረፉ፤ የኢትዮጵያ ጦር ዳግም ወደ ሶማሌ መግባት ለአል-ሻባብ ይህ ነው የማይባል የፕሮፓጋንዳና የምልመላ እድል የሚፈጥር ነው” ሲሉ አንዳንድ ተንታኞች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት ዲና ሙፍቲ ግን “ለጊዜው በግልጽ የተወሰነ ነገር ባይኖርም አዲስ አባባ አይነተኛ ሚና እንደሚኖራት መገመት ይቻላል” ብለዋል። “እንጋበዛለን። አስተዋጽኦም እናደርጋለን!” ሲሉም በእርግጠኝነት መናገራቸው የዳግም ዘመቻውን አይቀሬነት ማረጋገጫ ነው በሚል ብዙዎች ይስማማሉ።
በተያያዘ ዜና አንዳንድ የምእራቡ ዓለምና አፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ለጋዜጠኞች እንደጠቆሙት ከሆነ ኢትዮጵያ አል-ሻባብን በወጉ ለመሰባበርና የራሷን ወኪሎች በአገሪቱ ላይ ለማስቀመጥ ቋምጣለች። ይህ ግን ለበለጠ የስልጣን ፍጭትና ደም መፍሰስ የሚያጋልጥ ነው ሲሉ ስጋታቸውን አሰምተዋል።
ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና ኬንያ በሶማሊያ ተጽእኖ ያለው ኃይል ለመሆን በየፊናቸው እየጣሩ ሲሆን በእንቅስቃሴያቸውም ከምእራቡ ለጋሽ አገራት ሁነኛ ጥቅም ለማግኘት እየሞከሩ ነው ተብላል።



