ሱዳን ኢትዮጵያዊውን የፖለቲካ ስደተኛ ለኢህአዴግ አሳልፋ ሰጠች
Ethiopia Zare ( እሁድ ኅዳር 17 ቀን 2004 ዓ.ም. November 27, 2011)፦ የሱዳን መንግስት በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ እስርና እንግልት እያደረሰ ነው በሚል እየተወነጀለ ባለበት በአሁኑ ወቅት አንዷለም አለማየሁ የተባለውን የኢህአዴግ ተቃዋሚ አሳልፎ ለኢትዮጵያ መንግስት እንደሰጠ ከደረሰን ዜና መረዳት ተችሏል።
አንዷለም አለማየሁ ቀድሞ የፖለቲካ ድርጅት አባል የነበረ ሲሆን ወደ ኤርትራ ኮብልሎ ከአስመራ በሚያስተላልፈው የራዲዮ ፕሮግራሙ አማካኝነት የኢህአዴግን መንግስት የሰብአዊ መብት ረገጣና በባለስልጣናቱ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ሲያጋልጥ የቆዬ መሆኑ ተመስክሯል።
በቅርቡ ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት የኤርትራ ባለስልጣናት ወደ ሱዳን እንዲሻገር ያደረጉት ሲሆን የሱዳን የጸጥታ ሀይሎችም አስረው ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ እንዳቆዩት ጉዳዩን ሲከታተል የቆው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ተሟጋች ኮሚቴ (SOCEPP) ይፋ እድርጓል።
ይሄው ዋና መቀመጫውን በርሊን ያደረገው ኮሚቴ በመግለጫው እንዳስታወቀው ከሆነ አንዷለም አለማየሁ የኢህአዴግ አስተዳደርን በግልጽ ሲተች የቆየ ሰው እንደመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ከተላከ፤ ግርፋትና እንግልት እንደሚደርስበት፣ በህይወቱም ላይ ሳይቀር እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችል ለሱዳን መንግስት በጥብቅ ያስታወቀ ቢሆንም የሱዳን መንግስት ግን ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ አንዷለምን ለኢህአዴግ አገዛዝ አሳልፎ እንደሰጠው አጋልጧል። አንዷለም ወደ ኢትዮጵያ የተላለፈው በትክክል መቼ እንደሆነ ግን ሪፖርቱ አላመለከተም።
የሱዳን መንግስት ከኢህአዴግ አስተዳደር ጋር በሚያደርጋቸው አንዳንድ የፖለቲካ ጥቅም ልውውጦች ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን እንደመደራደሪያ ይጠቀምባቸዋል፤ በሚል በተለያዩ ወገኖች ሲወነጀል የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እስርና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
አንዷለም አለማየሁ ቀድሞ የየትኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንደነበርና መቸ ወደ ኤርትራ እንደኮበለለ ኮሚቴው በሪፖርቱ ግልጽ አላደረገም። እንዲሁም በሱዳን የጸጥታ ኃይሎች የተያዘው መችና እንዴት እንደነበር ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ጉዳዩን ሲከታተል የቆየውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ተሟጋች ኮሚቴን በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።



