በአዲስ አበባ የሚካሄደው የግብረሰዶማዊያን ስብሰባ ቁጣ ቀስቅሷል
የኃይማኖት አባቶች ድፍረት ይጎላቸዋል ተባለ
"ይህንን በህይወት በማየቴ እጅግ ስሜቴ ተነክቷል" ጋዜጠኛ ሰይፉ መኮነን
“ተቃውሟቸው የታይታና ግብዝነት የሞላበት ነው” ተክለሚካኤል አበበ
Ethiopia Zare (አርብ ህዳር 22 ቀን 2004 ዓ.ም. December 2, 2011)፦ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ነገ ቅዳሜ፡ ዲሴምበር 3 በአፍሪካ የግብረ ሰዶማዊያን ቡድን አሰባሳቢነት በጤና ጉዳዮች ላይ በጁፒተር ሆቴል የሚካሄደው ስብሰባ በዚህ ሳምንት በህብረተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ከመሆኑም በላይ በተለይ የሀይማኖት አባቶች የወሰዱት አቋም ቀድሞም ቁርጠኝነት ያልነበረውና ወላዋይነት የሞላበት መሆኑ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የ16ኛ አለማቀፍ የኤድስ ቀን አስታኮ በተጠራው ታላቅ ጉባኤ ላይ ከአስር ሺህ በላይ እንግዶችና የመንግስታት ተወካዮች እንደሚሳተፉበት የተጠበቀ ሲሆን፡ ከጉባኤው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የፊታችን ቅዳሜ እለት የአፍሪካ ወንዶች ለጤናማ ግንኙነት መብት ተሟጋች በመባል የሚጠራው (AMSHR) African Men for Sexual Health and Rights (AMSHeR), ቡድን አማካኝነት የተጠራው የግብረ ሰዶማዊያን ስብሰባ በሀገሪቱ ዋነኛ መነጋገሪያ እንደሆነና በህዝብ ዘንድ ቁጣ የቀሰቀሰ መሆኑ ታውቋል።
ይህንኑ ጉባኤ ለመቃወም የሀገሪቱ ዋና ዋና የሀይማኖት መሪዎች ማለትም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፤ የእስልምና፤ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ አባቶች የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጋዜጠኞችን የጋበዙ ቢሆንም ከመግለጫው ቀድመው የደረሱት የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሓኖም በዝግ የሀይማኖት መሪዎች ጋር ውይይት አካሂደው ከወጡ በኋላ የሀይማኖት አባቶቹም የግብረ ሰዶማዊያኑን ስብሰባ አስመልክቶ የሚሰጡት መግለጫ ቀኑ ላልተገለጸ ጊዜ መራዘሙን ገልጸው ምንም አይነት ንግግር ሳያሰሙ የጋዜጣዊ መግለጫውን ዘግተው መውጣታቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ተገልጿል።
በአሁኑ ሰአት ስብሰባውን የሚቃወሙ ሰዎች እየጠየቁ ያሉት የተቃውሞ ሰልፍ ጥያቄ ከመንግስት በኩል አጥጋቢ ምላሽ ያላገኘ ቢሆንም በእጅ ስልኮች የቴክስት መልእክቶች ጉባኤውን ለመቃወም እንዲወጡ ቅስቀሳዎች እየተደረገ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
የግብረሰዶማውያን በሚመለከት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ ህግ ማውጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን ግሎባል ቮይስ የተባለ የመገናኛ ብዙሀን ግብረ ሰዶማዊያን በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት አስመልክቶ ባወጣው የሀዝብ አስተያየት በህዝቡ ዘንድ ምንም አይነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጾ ባወጣው መስፈርት ከማሊ ቀጥላ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጧታል። መስፈርቱ ግብረሰዶማዊነት በማሊ 98% ተቀባይነት እንደሌለው ሲያሳይ በኢትዮጵያ 97% ተቀባይነት ማጣቱን ይፋ አድርጓል።
የሀይማኖት አባቶች መንግስት የሚለውን ከመደገፍና ግፍና በደል ሲፈጸም ዝም ብለው ከመመልከት ውጭ የሀገሪቱን ቀጥተኛ ችግሮች ለመጋፈጥ አንዳችም ርምጃ ሳይወስዱ፡ ባህልንና ስርአትን ለማስጠበቅ የቆሙ ዘቦች መምሰላቸው አስመሳይነት ብቻ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጭዎች ተሰምተዋል።
“ግብረሰዶማዊነት የኢትዮጵያ ራስ ምታት አይደለም፡ ከሆነም በሀገሪቱ በሚከሰቱ ከግብረሰዶማዊነት የከፉ አሳሳቢና አዋራጅ የሰብአዊ ድርጊቶች ላይ ምንም አይነት ቃል ያልተነፈሱ የሀይማኖት አባቶች አሁን ብድግ ብለው፤ ‘የግብረ ሰዶማዊያንን ስብሰባ እናወግዛለን’ ለማለት መነሳታቸው” የሀይማኖት አባቶቹን የአስመሳይነት ልክ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ሲል በዪኒቨርስቲ ኦፍ ኦታዋ የአለም አቀፍ ሕግ ድህረ ምረቃ ተማሪ የሆነው አቶ ተክለሚካኤል (ተክሌ) አበበ ተናግሯል። አቶ ተክሌ ቀጥሎም፡ “በሀገሪቱ የ15 እና የ16 አመት ታዳጊዎች ገላቸውን እየቸበቸቡ በሴተኛ አዳሪነት እንዲተዳደሩ እየተገፉ ባሉበትና፡ ሁለት መቶ ሺህ በሴተኛ አዳሪነት፡ ሌላ አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ በጎዳና ተዳዳሪነትና በልመና በሚተዳደሩባት አገር፤ እህቶቻችን አልፎም ተርፎም በአረብ አገራት አሳራቸውን ሲበሉ እነሱ የሚከራዩ ቪላቸውን በየከተማው የሚገነቡና አብያተ ክርስቲያናቸውንና የእምነት ተቋማቸውን በቅጥ ያላስተዳደሩ የሀይማኖት መሪዎች፡ ደርሰው የባህል ጠበቆች መሆናቸው ቅጥፈት ነው” ሲል ተናግሯል።
“ይሄ የህዝብን ድጋፍ ለመሸመት የሚደረግ ሽሚያና ሩጫ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አንገብጋቢ ችግር አይደለም” ሲልም አስተያየቱን አክሏል። በተለይም በአሜሪካን ዩኒቨርስቲ ከግብረሰዶማዊያን ጋር እየተጋፉ፡ እየተሻሹ እንደተማሩ የሚነገርላቸው አባ ጳውሎስ በንዲህ ያለው ድራማ ላይ መገኘታቸውን ሰውየውን ከምእራቡ አለም ለመነጠልና እኚህ ሰዎች በግለሰቦች ጓዳም ጭምር ዘልቆ ለሚገባ ስርአት አጃቢዎች መሆናቸውን ለማሳየት ልንጠቀምበት እንደሚገባ ጠቁሟል።
በስደት ከሀገሩ ከወጣ በኋላ በካልጋሪ ነዋሪ የሆነው የቀድሞ የመብሩክ እና የሰይፈነበልባል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሰይፉ መኮነን ይህንኑ ሁኔታ አስመልክቶ “አባቶች አስኬማቸውን (የምንኩስና ቆባቸውን) ጥለው እና ቀሚሳቸውን አውልቀው ወደ ገዳም መሄድ እስኪገባቸው ድረስ ፈታኝ የሆነ አጣብቂኝ ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሶ ክርስቲያናዊት ሀገር እየተባለች ለእልፍ አመታት የኖረች ሀገር ሰው እንደሌላት በዋና ከተማዋ ይሄንን አይነት ጉባኤ ለመከናወን ሲታቀድ አባቶች ሆ ብለው መነሳት ነበረባቸው። በአሁኑ ሰዓት ምእመኑ እንጂ አባቶች በሙስናና በገንዘብ ተይዘዋል። ይህንን በህይወት በማየቴ እጅግ ስሜቴ ተነክቷል። የሀይማኖት አባቶች ራሳቸውን የሚፈታተን ነገር ሲመጣባቸው እና የጠሩት የጋዜጣዊ መግለጫ በጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሓኖም ቢታገድም በድፍረት ወጥተው መጋፈጥና አቋማቸውን ማሰማት የአባትነት ሃላፊነታቸው ነበር። ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
የኢህአዴግ አገዛዝ ይህንን ስብሰባ ያለበትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲል ብቻ ፈቃድ መስጠቱን የሚተነትኑ በሀገሪቱ የገንዘብ ችግር ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ስጋታቸውን በሚገልጹበት በአሁኑ ወቅት የሀይማኖት መሪዎቹ ለታይታና ለይስሙላ መሰብሰባቸው እራሱ የሀገሪቱን ውድቀትና የማህበራዊ እሴቶችንን ውድመት የሚያሳይ ነው ተብሏል።
የፊታችን ሰንበት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የአለም አቀፉ የኤድስ ማህበር ዋና ዳይሬክተር ሚሸል ሲዲቤ፣ የአሜሪካ አለማቀፍ ኤድስ ተቋም አስተባባሪ ኤሪክ ጎስቢና ሌሎች ታላላቅ ተቋማት ሃላፊዎች ንግግር የሚያደርጉ መሆኑ ተገልጿል።



