ኦባንግ ሜቶ ኦታዋ ገባ፡ በኮንጎዎች የተቃውሞ ሰልፍ ላይም ተሳተፈ
“የኦታዋና ቶሮንቶ ኢትዮጵያዊያንን እንቅስቃሴ ያሳድጋል” ተብሎ ተስፋ ተደርጓል
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ህዳር 28 ቀን 2004 ዓ.ም. December 8, 2011)፦ የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ በእንግሊዘኛው Solidarity Movement for New Ethiopia የተባለው የተባለው መቀመቻው በሰሜን አሜሪካ የሆነ የኢትዮጵያዊአን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት መስራችና ስራ አስኪአጅ አቶ ኦባንግ ሜቶ፡ ቀድሞ ይኖርበት ከነበረው ሳስካቱን ከተማ ወደ ካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ በዚህ በያዝነው ሳምንት መዛወሩ ታወቀ።
የዛሬ ስምንት አመት አካባቢ የአቶ መለስ አገዛዝ በአኝዋክ ብሄረሰብ አባላት ላይ ከፈጸመው ከአራት መቶ በላይ የአኝዋክ ብሄር ተወላጆች ከተገደሉበት ክስተት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስት በአስታራቂነትና በሰብአዊ መብት ተሟጋችነት የሚታወቀው ኦባንግ ሜቶ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርገውን ተጋድሎ ቀጥሎ ይሄንኑ ትግሉን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ በሚል ወደኦታዋ መዛሩን ባለፈው ማክሰኞ በኦታዋ የኮንጎዎች ተቃውሞ ሰልፍ ላይ ባገኘነው ግዜ ገልጾልናል።
በኮንጎ የሚካሄደውን የዘር ማጥፋትን ወንጅልና የምርጫ መጭበርበር ተቃውመው የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን አጅቦ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ሲጓዝ የነበረው ኦባንግ ሜቶ፤ በኮንጎ ኤምባሲ አጠገብ አነጋግረነው፡ “ኢትዮጵያዊያንም ከኮንጎዎች ተምረው፡ በብሄርና በዘር ሳይከፋፈሉ ባንድነት ሆነው የህወሀት/ኢህአዴግን አገዛዝ ሊያወርዱትና ባገራቸው ዴሞክራሲአዊ ስርአት ሊገነቡ መነሳት አለባቸው” ብሏል። የሰልፉንና የኦባንግን መልእክት በቪዲዮው ላይ ይመልከቱ። በመጪው ሰኞ ጠዋት ድሴምበር 12፡ ሕወሀት በነጠቀን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ስለሚደረግ፡ 506 International Drive, NW, http://www.march4freedom.org/ (የኮንጎዎቹን ተሞክሮ ልብ ብለው ያስተውሉ)።
በኦታዋ በሺዎች የሚቆጠሩ የተማሩ፡ ልምድ ያላቸውና የተደላደሉ ኢትዮጵያዊያን ቢኖሩም፡ እስከቅርብ ግዜ ድረስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ሚና አናሳና ኮሳሳ ሆኖ ቆይቷል። በቅርቡ የኢትዮጵያዊያን ካናዲያዊያን መድረክ ለዴሞክራሲ Ethiopian Canadians Forum for Democracy የተሰኘ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ቢቋቋምምና ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ኢሳትን በመርዳትና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ረገድ ቢንቀሳቀስም፡ ፎረሙ የኢህአፓ-ዲ ጥገኛና እስረኛ በመሆኑና በግንቦት ሰባት አባልነት የሚጠረጠሩ ሰዎችን አጥብቆ በመፍራቱ የተነሳ በአካባቢው የሚገኙ አያሌ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን ሊጠቀምባቸው አልቻለም። ፎረሙና በኦታዋ የሚገኙ ሲቪክ ማህበራት በቅርቡ ለየኔሰው ገብሬ ባዘጋጁት የሻማ ማብራት ስነስርአት ላይ፡ በአካባቢው የሚገኙ እንደ ግንቦት ሰባት፡ አረና፡ ታጠቅና ኢሰፓ ያሉ አገር ወዳድ ድርጅት መገኘታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/1246
ኦባንግ ሜቶና የግንቦት ሰባት አባላት በቅርቡ በሽብረተኛው የሕወሀት አገዛዝ ሽብርተኞች መባላቸው የሚታወቅ ነው። የኦባንግ ሜቶ ወደኦታዋ መምጣት የአካባቢውን ኢትዮጵያዊ በማጠናከር ረገድና በዴሞክራሲ ታጋዮች መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል። ከኦታዋና አካባቢው ኢትዮጵያዊያን ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ያዘጋጀነውን ሀተታ በቅርቡ ከድረ-ገጾች ላይ እንሰቅላለን። ይመቻችሁ።
በተክለሚካኤል አበበ



