በአዲስ አበባ የፌደራል ፖሊስ ጥበቃ ተጠናክሯል
የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በየቤታቸው ይፈተሻሉ
Ethiopia Zare (አርብ ህዳር 29 ቀን 2004 ዓ.ም. December 9, 2011)፦ በመናገሻዋ አዲስ አበባ በየትላልቅ ፎቆችና ዋና ዋና መንገዶች ዙሪያ የፌደራል ፖሊስ በመባል የሚታወቁት ተወርዋሪ የጥበቃ ኃይሎችና የደህንነት አባላት ሩጫ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ መታየታየቱ ተገለጸ።
የፌደራል ፖሊሶቹ በየመንገዱ ዜጎችን በማስቆምና “ተለጠፍ“ በማለት ልዩ ፍተሻ እያደረጉ እንደሚገኙም ከስፍራው የደረሰ ዘገባ ያስረዳል።
የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በየቤታቸው ሶስት የፌደራል ፖሊስ አባላቶች በመዝለቅ ልዩ ምርመራ እየተደረገላቸው መሆኑን ምስክርነታቸውን የሰጡ ሰዎች፤ ከየት መጣህ? ለምን መጣህ?፣ መቼ ትመለሳለህ?፣ ምን ያህል ጊዜ ትቆያለህን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች የቀረበላቸው መሆኑን ገልጸው ይህንንና መሰል ጥያቄዎችን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ተጠይቀው እንደነበርና አሁን ድጋሚ መጠየቃቸው ለምን እንዳስፈለገ ቤተሰቦቻቸው ቤት ድረስ በመምጣት ለፈተሿቸው የፌደራል ፖሊሶች ቢጠይቁም “ለደህንነት ነው” የሚል ምላሽ ብቻ እንደተሰጣቸው መስክረዋል።
ይህንን አይነት ጥያቄ ለውጭ ሀገር ዜግነት ላላቸው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚቀርብ መሆኑን ወይንም በተናጠል ለአንዳንድ ግለሰቦች ብቻ ስለመሆኑ ምስክሮቹ ተጠይቀው በእነሱ ላይ የተደረገውን የቤት ውስጥ ፍተሻና ጥያቄ እንጂ ይህ ችግር በሌሎች ላይ ስለመድረሱ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።
ይህ በውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደረገው ልዩ የቤት ለቤት ፍተሻ ሰሞኑን ከ100 በላይ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ መሪዎችንና አባላትን፤ እውቅ ግለሰቦችንና የውጭ ሀገር ዜጎችን ለእስር በዳረገው የ”ሽብርተኝነት” ህግ ጦስ ይሁን በአዲስ አበባ በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ የኤችአይቪ/ኢድስ ጉባኤ ምክንያት የታወቀ ነገር ባይኖርም በቅርቡ ስራ ላይ የዋለው የ”አሸባሪነት” ህግ ማንኛውም ዜጋ በቤቱ የሚያኖረውን እንግዳ በሚመለከት ለቀበሌ ወይንም ለወረዳ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ያስገድዳል።



