ሕዝብ እና ፌደራል ፖሊስ ተፋጠዋል

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ታህሳስ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. December 27, 2011)በደሴ ከተማ ልዩ ስሙ አራዳ ገበያ በመባል የሚታወቀው ቦታ 11 ቤቶች ተቃጥለው ነዋሪዎች በድጋሚ በእሳት የጋዩ ቤቶቻቸውን ለመስራት  ሲሞክሩ በስፍራው የደረሱ የፌደራል ፖሊሶች ቤቶቹ እንዳይሰሩ በመከልከላቸው ምክንያት  ህዝብና የፌደራል ፖሊስ መፋጠጣቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ጠቆመ።


በአራዳ ገበያ ጨው ተራ በመባል የመታወቀው አካባቢ አርብ ለቅዳሜ ማለትም ታህሳስ 13 ቀን ለ14/ 2004 ዓ.ም ሌሊት ባልታወቀ ምክንያት የተነሳ እሳት መጠነኛ ጉዳት ቢያደርስም በሚቀጥለው ቀን ታህሳስ 14 ለታህሳስ 15 ቅዳሜ ለእሁድ ሌሊት በድጋሚ የተቀጣጠለው እሳት ለ11 ቤቶች እና በርካታ ግምት ያላቸው ንብረቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን ለመረዳት ችለናል።


በስፍራው ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሁለት ወንድማማቾች በሚቀጥለው ቀን ቤታቸውን ለመስራት ሙከራ ባደረጉበት ወቅት የፌደራል ፖሊሶች ደርሰው አካባባው ለልማት ስለሚፈለግ ምንም አይነት መልሶ ግንባታ ማካሄድ እንደማይደረግ በሰጡት ማስጠንቀቂያ መክንያት በአካባቢው ነዋሪዎችና የፌደራል ፖሊሶች መሀከል ፍጥጫ መነሳቱ ታውቋል።

 

በአካባቢው የሚገኙ ተቃዋሚ ድረጅት አባላት በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማሰገባት ከተጎጅዎቹ ጎን በመቆም ነዋሪዎቹ ሚያደርጉትን ርብርብ በመርዳት ያሳዩት እገዛ በኢህአዴግ ፌደራል ፖለሶች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው መሆኑንና ነዋሪዎቹ በብርድና ዝናብ መሰቃየታቸውንና የጤና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ስጋት መኖሩን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

 

ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው ግለሰቦች ሌላ ቦታ ሄደው ቤት እንዲከራዩ ከፌደራል ፖሊሶች ጥብቅ ትእዛዝ ቢሰጣቸውም በአሁኑ ሰዓት ባለው የአከራይና ተከራይ አለመተማመን ምክንያት ቤት ተከራይቶ ለመኖር ከፍተኛ ፈተና ውስጥ እንደወደቁ ተገልጿል።

 

በአሁኑ ሰዓት በተቃጠሉ ቤቶቻቸውና ንብረታቸው ሳቢያ ችግር ላይ የሚገኙ ተጎጅዎች ቤት ተከራይተው እንዳይኖሩ እንኳን በሀገሪቱ በተፈጠረው የአከራይና የተከራይ አለመተማመን የተነሳ የከፋ ችግር ላይ ለመውደቅ መቻላቸውን የገለጹ የአይን ምስክሮች የቀበሌ ቤቶችን ማከራየት እንደማይቻልና የተከራዩ ግለሰቦች ካሉና ለቀበሌ ካሳወቁ ግንኙነታቸው በቀጥታ ከቀበሌው ጋር እንደሚሆንና አከራዩ እንደሚቀጣ የሚያስገድደው አዋጅ በመውጣቱ ምክንያት ብዙ አከራዮች ቤታቸውን ማከራየት እንደማይደፍሩና በግል ይዞታ ያላቸው ባለቤቶችም ጭምር ቤታቸውን ‘ነገ ምን አይነት አዋጅ እንደሚመጣ አናውቅም’ በሚል ስጋት ቤቶቻቸውን ከማከራት እንደተቆጠቡ ለመረዳት ተችሏል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ