የመኖሪያቸውና ጽህፈት ቤታቸው ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው!

የበአሉ እለት፡ በቤተመቅደስ ውስጥ መለስተኛ ረብሻ ተነስቶ ነበር!

Ethiopia Zare (ሰኞ ታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ.ም. January 2, 2011)፦ በውጭ ሀገር በስደት ላይ የሚገኘውና ህጋዊው ሲኖዶስ ብጹዕ ወቅዱስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ አቡነ መርቆሪዮስ መቀመጫቸውን በአሜሪካዋ መናገሻ ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ እንደሚያደርጉ እና ጽህፈት ቤታቸውና የመኖሪያ ቤታቸው ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።

 

ፓትርያርክ መርቀርዮስ መኖሪያ ቤታቸውንና ዋና ጽህፈት ቤታቸውን በዲሲ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ማድረጋቸው በየቦታው የሚከሰቱ የአቢያተ ክርስቲያናትን እና የምእመናንን ችግር ለመፍታት አመች ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል። ተክለሚካኤል አበበ በዋሽንግተን ዲሲ ቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በአል አከባበር ላይ ተገኝቶ የሚከተለውን ዘግቧል።

 

የፓትሪያርኩ መኖሪያና ጽህፈት ቤታቸው እየተገነባ መሆኑን ሰምቼ፡ በግንባታው ላይ ዜናና ጽሁፍ ለማሰናዳት፤ ወደ ዲሲ ካቀናሁ ጀምሮ በተደጋጋሚ ወደቤተክርስቲያኑ ልሄድ ብሞክርም፤ በተለያዩ የሚረቡም የማይረቡም ምክንያቶች ሳይሞላልኝ ቆየና፤ በመጨረሻ የቅዱስ ገብርኤል በአል ዋዜማ እለት ካሜራዬን ይዤ ወደ ደብረ ሀይል ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ አቀናሁ። የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ በኢትዮጵያ የሚከበረው ታህሳስ 19 ቀን ቢሆንም፡ እዚህ ሰሜን አሜሪካ ግን ሀሙስ የስራ ቀን ነበርና፡ በአሉ የተከበረው ከሶስት ቀን በሁዋላ እሁድ ታህሳስ 22፡ የፈረንጆች አዲስ አመት እለት ነው። በዋዜማው ቅዳሜ ወደቤተክርስቲያኑ ሳመራ፡ ጳጳሳትና ቀሳውስት ስርአተ ዋዜማ ሲያደርሱ ደረስኩኝ። የምስል መቅረጫዬን አቀባብዬ አንድ ሁለት ፎቶዎች እንደወሰድኩ፡ ከወደ አስተዳደር በኩል “ፎቶግራፍ ለማንሳት ፈቃድ ያስፈልጋል” የሚል ትእዛዝ ደረሰኝ። ትእዛዙን ተቀብዬ፡ ካሜራዬን ወደማህደሩ መለስኩና፡ ፎቶ ማንሳት የሚከለክል ምንም አይነት ማስታወቂያ እንዳልተለጠፈ፤ መከልከል ከፈለጉ ያንን ክልከላ በግልጽ ቦታ ቢያደርጉት መልካም እንደሆነ፡ የሚከለክሉበትንም ምክንያት ቢያሳውቁኝ ለሁላችንም በጎ እንደሆነ ገለጽኩኝ።

 

በነጋታው ጠዋት ወደቤ/ክ ስሄድ በርግጥም በር ላይ ያለቦርዱ ፈቃድ ፎቶግራፍ ማንሳት የሚከለክሉ ማስታወቂያዎች ተቀምጠዋል። አስፈላጊውን የጀርባ ጥናት አድርገው የኔንም ፈቃድ አዘጋጅተውልኛል። አርፍጄ ስለነበር የደረስኩት፡ ቤተክርስቲያኑ ጢም ብሎ ሞልቶ፡ በሁለተኛው ክፍል ውስጥም ትልቅ ጥፍጥፍ ቴሌቪዥን ተሰቅሎ የቅዳሴ ስነስርአቱ ይተላለፋል። ቅዳሴው ሊጠናቀቅ አካባቢ ጽላቱ ከመውጣቱ በፊት ጳጳሳቱና፡ ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከአውደ ምህረት ላይ ተደርድረው ተቀመጡ። መዘምራን መዝሙር ሊዘምሩ ሲወጡ፡ የተወሰኑ ሴቶች እየተንጫጩ፡ ግማሾቹ ወደፊት ቀርበው፡ ገሚሶቹ ደግሞ ካሉበት ቦታ ሆነው፡ ብሶታቸውን ማሰማት ጀመሩ። መጀመሪያ ከሁዋላ ስለነበርኩ የሆነውን ሁሉ በቪዲዮ እንጂ በቅርበት በአካል አልተመለከትኩም፡ አልሰማሁምም። በሁዋላ እንደተረዳሁት ግን፡ ቦርዱ ያባረረው ወይም ያገደው አንድ ጎበዝ ሰባኪና፤ የሱን መባረር ተከትሎም ሌሎች ዲያቆናት ወጥተዋልና ይምጡ የሚለሱ የሚል ስሞታ ነው።

 

ቀጥሎ፡ የደብሩና ያካባቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳሙኤል ቅሬታቸውን ለጳጳሳቱ፡ ለፓትሪያርኩና ለምእመናኑ ተናገሩ። እሳቸው የሰበካው ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሳለ ዲያቆኑን ሊያቀስሱ ሲል፡ ከቦርዱ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ሰባኪውም እንደታገደ እሳቸወም ማቀሰስ እንደማይችሉ መነገሩ እንዳሳዘናቸው ተናገሩ። በመርሀ ግብሩ መሰረት የአቡነ መልከ ጼዴቅ ስብከተ ወንጌል ቢሆንም፡ በጳጳሱ ንግግር  ስላልተደሰቱ ይመስላል፡ ሊሰብኩ አልፈቀዱም። የቦርዱ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋ ቀርበው ስለተፈጠረው ችግር ትንሽ ማብራሪያ ለመስጠት ሞከሩና አንዳንድ ሴቶች ጣልቃ እየገቡ መናገራቸውን ስለቀጠሉ፡ ቀኑ የበዓል እንጂ የውይይት እንዳልሆነ ጠቅሰው፡ ችግሩን ወደፊት እንደሚመክሩበት በማሳሰብ ወደሚቀጥለው መርሀግብር አለፉ። አቡነ መቃርዮስም ያንኑ ሀሳብ አንጸባርቀው፡ ኢትዮጵያዊያን በፖለቲካም በሀይማኖት ጉዳዮችም አንድ አለመሆናቸው እነሱንም አገርንም እየጎዳ እንደሆነ አሳስበው ወደገንዘብ ማሰባሰቡ በመግባት፡ ለቤተክርስቲያኑ ማሳደሻ ገንዘብ ተሰባስቦ፡ ይሄ ዘገባ እስኪጠናቀር የገንዘቡን ትክክለኛ መጠና ልናውቅ ባንችልም፡ ከ10 ሺህ በላይ ብር እንደተሰበሰበ ለማወቅ ችለናል።

 

በእለቱ በቦታው ፖሊሶች ነበሩ። ስለቤተክርስቲያኑ ችግር እየመረመርን ሲሆን፡ አስፈላጊውን ማጣሪያ ከጨረስን በሁዋላ እናቀርብላችሁዋለን። እንዲሁ ጫፍ ጫፉን ለማስያዝ ያህል ግን፡ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ሳሙኤል፡ በውጪው ሲኖዶስና በፓትሪያርኩ ጵጵስና ቢቀበሉም፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከአባ መላኩ፡ ወይንም አቡነ ፋኑኤል ጋር መገናኘት እንደጀመሩና፡ ወደአገር ቤት የመግባት ዝንባሌ አላቸው የሚል ክስ ባንድ በኩል ሲሰነዘር፡ በሌላው አንጻር ግን በስብከቱ ወደር የሌለውን መምህር ለመፈንቀል ጥረት እየተደረገ ነው የሚል ክስ አለ። ዶ/ር ነጋ ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራሩ፡ ከምእመናኑ ብዙ ክስ ቀርቦበት፡ ሁለተኛም ማንም ዲያቆን ክህነት ከመቀበሉ በፊት የቤተክርስቲያኑ አስተዳደር ቦረድ መፍቀድና መወሰን አለበት፡ ጳጳሱም ያንን ስርአት ሳይከተሉ ነው ሊያቀሱት የጣሩት የሚል መልስ ሰጥተዋል።

 

በተያያዘ ዜና፡ የፓትሪያርክ መርቆሬዎስ መኖሪያና ጽህፈት ቤት ግንባታ በዚሁ በቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ ውስጥ እየተጠናቀቀ ሲሆን፡ ፓትሪያርኩና ሲኖዱሱ መቀመጫቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ካደረጉ፡ በየከተሞቹ እየተፈጠረ ያለውን የቤተክርስቲያን አስተዳደር ችግር በጊዜ ለመፍታት እንደሚቀል ይጠበቃል። በውጪ የሚገኘው ሲኖዶስና ህጋዊው ፓትሪያርክ በስራቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ቢገኙም፡ ማእከላዊና ተከታታይ እንዲሁም ጥበቅ መመሪያ የሚሰጥ የበላይ አስተዳዳሪ ባለመኖሩ ምክንያት፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በብዙዎቹ ቤ/ክርስቲያናት ውስጥ ችግር እየተፈጠረና አባላትም ለመከፋፈልና ለክስ እየተዳረጉ ይገኛሉ። ለምሳሌ በቅርቡ፡ በዴንቨር፡ በሲያትል፡ በቫንኩቨር፡ በዲሲና በዩጋንዳ የአስተዳደር ችግሮች እንደተፈጠሩና፡ የፓትሪያርኩ ጽህፈት ቤትም ይሁን የውጪው ሲኖዶስ መፍትሄ ሊያበጅ እንዳልቻለ ይነገራል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ