በኦነግ አዲስ አቋም ዙሪያ ውዝግቡ ቀጥሏል
“በኦነግ ውስጥ የተፈጠረው ችግር ምክንያት የጠራ ራእይ ማጣት ነበር” የኦነግ ከፍተኛ አመራር
Ethiopia Zare (ሐሙስ ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. January 5, 2011)፦ በፈረንጆችቹ አዲስ አመት መግቢያ የኦሮሞ ተወላጆች በብዛት ይኖሩባታል በምትባለው ሜኔሶታ ክፍለ ከተማ በተጠራ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ይፋ የሆነውና ኦነግ (የኦሮሞ ነጻነት ግንባር) ከተመሰረተበት ከ1960 እኤአ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን አንድነት የተቀበለበትን መግለጫ ካወጣ ጀምሮ የተለያዩ አስተያየቶች በመሰማት ላይ ናቸው።
የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር በዚህቹ ከተማ ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጎ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ በጋራ ለመታገል ከማናቸውም የአንድነት ኃይል ጋር ለመስራት ቆርጦ መነሳቱን ያስታወቀ ሲሆን የግንባሩ መሪ የሆኑት ጄኔራል ከማል ገልቹ ከአስመራ በቀጥታ በቪድዮ ባስተላለፉት መልእክት የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ ግንድ ነው ከምኑ ላይ ነው ሚገነጠለው ማለታቸው ተሰምቷል።
በኦነግ ውስጥ በአመራር አባላት መካከል ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ አለመግባባት የተከሰተ ሲሆን በተለይ ለውጥን እናራምዳለን በሚሉትና በጄኔራል ከማል ገመቹ ስር በሚገኙ ወገኖች እና የኦሮሞ ህዝብ በአቢሲንያ ቅኝ ግዛት ስር ነው በሚል አቋማቸው የሚታወቁት አቶ ዳውድ ይብሳ ደጋፊዎች መሀከል ልዩነቱ ጎልቶ መታየቱ ይታወቃል።
ያለንን ጦር ወደ መሀል ኢትዮጵያ ይዘን መግባት አለብን። ጊዜ ማጥፋት የለብንም በማለት የሚታወቁት ጄኔራል ከማል ከምርጫ 97 በኋላ ከሁለት መቶ ወታደሮች በላይ አስከትለው ወደኤርትራ የገቡ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን በኦነግ አመራር ሆነው በመስራት ላይ ባሉበት ሰአት አለመግባባቱ መካረሩሩን ምስክሮች ይናገራሉ።
የትውልድ አካባቢ ፖለቲካ በኦነግ ውስጥ ለተፈጠረው መከፋፈል እንደዋና ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል ምን ያህል እውነት ነው ለሚለው ጥያቄ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ምላሽ የሰጡት በጄነራል ከማል የሚመራው ኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑትና በትግል ስማቸው በሪ ቦሩ በመባል ሚታወቁ አመራር ይህ በምንም አይነት ሁኔታ ዋጋ የሌለው አባባል መሆኑን ጠቅሰው “በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ የነበረው አለመግባባት ዋና ችግር የሙሉ ራእይ ማጣት ነበር።” ከማለታቸውም በላይ ድርጅቱ የጠራ ራእይ አልነበረውም አንዳንዶች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ችግር ነበረባቸው ሌሎች ደግሞ የኦሮሞ ችግር የጠቅላላዋ ኢትዮጵያ ችግር ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው። አሁን ግን በድርጅቱ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የነበረው የራእይ ማጣት ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በያዝነው አዲስ አመት ባወጣነው መግለጫ ተረጋግጧል። ብለዋል።
አሁን በኦነግ የተያዘው አቋም አዲስ አመለካከት ሳይሆን ቀደም ሲል የነበሩና በድርጅቱ የታቀፉ ታዋቂ የኦሮሞ ኢሌቶች (ምሁራን) ዘንድ ሲብላላ የቆዬ ጉዳይ መሆኑንም የኦነግ ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑት አቶ በሪ ቦሩ አስምረውበታል።
በተያያዘም በአቶ ዳውድ ይብሳ የሚመራው ኦነግም ለውጥ አራማጅ የተሰኘውን ክፍል የያዘው አቋም በአቢሲኒያዊያን የተቀናበረ ሴራ ነው። በሚል መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል። (በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን ያወጣውን መግለጫ ሙሉ ቃል ይህንን በመጫን ያንብቡ)



