አዲሱ ፌዴሬሽን (ESFNA-ONE) ተብሏል

አቶ አብነት የስፖርት ክለቦችን ለመደለል ገንዘብ መበተን ጀምሯል

Ethiopia Zare (ሐሙስ ጥር 3 ቀን 2004 ዓ.ም. January 12, 2011)፦ የኢትዮጵያዊያን በሰሜን አሜሪካ ስፖረት ፌደሬሽን የሚያካሂደው አመታዊ የስፖርት ውድድር አመታዊ ዝግጅቱን በዳላስ ቴክሳስ እንደሚያካሂድ ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በሼህ መሀመድ አላሙዲ ወዳጅ አቶ አብነት የሚመራ አዲስ ፌደሬሽን ተቋቁሞ ሌላ የስፖርት ውድድር በዋሽንግተን ዲሲ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ።

 

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በኖርዝ አሜሪካ ያለምንም ተጽእኖ ለሁለት አስርት አመታት የዘለቀ ቢሆንም ባለሀብቱ ሼህ መሀመድ ፌደሬሽኑን ለመርዳት በሚል በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ዶላር በመስጠት በእጃዙር እጃቸውን ካስገቡ እና ሁኔታውን በጥንቃቄ ሲከታተሉ በቆዩ ኢትዮጵያዊያን ተጋልጠው ፌደሬሽኑ ነጻ ከወጣ በኋላ በያዝነው አመት በዳላስ ቴክሳስ 29ኛውን የስፖርትና የባህል በዓል ለማክበር ዝግጅት በሚያደርግበት በአሁኑ ሰዓት በተጓዳኝ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ሌላ የስፖርት ውድድር ለማዘጋጀት በአቶ አብነት ገ/መስቀል የሚመራ ኃይል በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስ ላይ መሆኑን ምንጮች ገለጹ።

 

ይሄው ራሱን ESFNA-ONE በማለት የሰየመው ፌደሬሽን አር.ኤፍ.ኬ. (RFK Stadium) በመባል ሚታወቀውን ዝነኛ ስቴድየም በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ ከጁላይ 1 እስከ ጁላይ 7  ለአንድ ሳምንት ያህል ጊዜ መከራየቱ የተጠቆመ ሲሆን ወጭው ሙሉ ለሙሉ በሼህ መሀመድ አላሙዲና በአቶ አብነት ገ/መመስቀል እንደሚሸፈን ውስጥ አዋቂ ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል። ስታዲየሙ ቀድሞ ፌደሬሽኑ 25ኛ የብር ኢዮቤልዮ በአሉን ሲያከብር 1.5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለአንድ ሳምንት በመክፈል ያከበረበት መሆኑ ይታወቃል።

 

በአቶ አብነት የሚመራው ይሄው ቡድን በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የማስታወቂያ ስራ በመስራት እና በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ላይ የሚገኝ ሲሆን ለማስታወቂያ ዘመቻ ብቻ በርካታ ገንዘብ መድቦ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

 

አዲሱ ፌደሬሽን የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በሎስ አንጀለስ ከተማ ጠቅላላ ሰብሰባ ለማካሄድ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ቡድኖችን በመጋበዝ እያንዳንዳቸው ሁለት ሰዎችን ወክለው እንዲልኩ ግብዣ ከማድረጉም በላይ ወጫቸው ሙሉ ለሙሉ እንደሚሸፈንና የኪስ ገንዘብ በመስጠት ላይ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በተጨማሪም ለእያንዳንዱ ቡድን 10ሺህ ዶላር እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

 

ይሁን እንጂ በዳላሱ የስፖርት ውድድር ለመሳተፍ በየሀገራቱ የሚገኙ ቡድኖች ያሳወቁና የተመዘገቡ ሲሆን አንዳንድ አካባቢ ያሉ የእግር ኳስ ክለቦች ግን ከአዲሱ የእነ አቶ አብነት ፌደሬሽን ጋር ለመሆን መደራደር መጀመራቸው ታውቋል። በዚህም የሲያትሉ ዳሽን እና ዲሲ ስታር በገንዘቡ ድለላ የተታለሉ መሆኑን ምንጮቹ ገልጸው በሁኔታው ያልተስማሙ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ‘የምንወደውን ስፓርት ፌደሬሽንና ህሊናችንን ለገንዘብ ስንል አንሸጥም’ በማለታቸው አለመግባባት መፈጠሩም ተገልጿል።

 

በተያያዘም በመጭው የበጋ ወራት በዋሽንግን ዲሲ በየአመቱ የሚከናወነው እና ባለፈው አመት የመጀመሪያ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ ከጁን 29 እስከ ጁላይ 1 ሁለተኛ አመታዊ በአሉን ለማድረግ ዝግጅቱን እያካሄደ ሲሆን በማርች ወር የአደዋ በአልን በማስመልከት ታላቅ በአል ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ