Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥር 5 ቀን 2004 ዓ.ም. January 14, 2011)፦ ባለፈው አመት ጁን ወር ላይ በሶማሌ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የኦብነግ ወታደሮች ጋር በጥይት ተመተው የተማረኩትና በፍትህ አጉዳይነቱ በሚታወቀው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ለ11 ዓመታት እስር ላይ እንዲቆዩ የተፈረደባቸውን ሁለቱን ስዊድናዊ ጋዜጠኞች በተመለከተ የዲፕሎማሲው ፍጥጫ ቀጥሏል። በምህረት የመፈታታቸው እድልም የመነመነ መሆኑ ተገለጸ።

 

በኢትዮጵያ ውስጥ በአዲሱ የሽብርተኛነት ህግ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት ጋዜጠኛ ማርቲን ሺልቤ እና ፍቶግራፈሩ ጆን ፔርሰን በምህረት ይለቀቃሉ የሚለው ተስፋ የመነመነ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፕሮፌሰር የሆኑት ወንደሰን ደምሴ መግለጻቸውን ስቶኮልም ኒውስ የተባለ ድረገጽ ይፋ አውጥቷል።

 

ፕሮፌሰር ወንዶሰን ሮይተር ለተባለው አለማቀፍ የዜና አውታር እንደገለጹት “ከአሁን ቀደም ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረደበት ሰው ምህረት ያገኘበት አንዳችም አይነት ሁኔታ አላስታውስም። ከማለታቸውም ሌላ “አወዛጋቢው ጥያቄ ሽብርተኝነት ‘በሰብአዊነት ላይ የተወሰደ ወንጀል’ ተብሎ ይፈረጃል ወይንስ አይፈረጅም የሚለው ነው። እንደዚያ የሚወሰድ ከሆነ የይቅርታ እድል አይኖራቸውም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ህግ በሰበአዊነት ላይ የተወሰዱ ርምጃዎች ምህረት አይደረግላቸውምና።” ብለዋል።

 

የተለያዩ ታዛቢዎች ሲዊድናዊያኑ ምህረት ከጠየቁ ተቀባይነት ያገኛሉ ሲሉ አስተያየታቸውን ሲገልጹ እንደነበር አይዘነጋም። ይሁንና በአዲስ አበባ ያሉ ዲፕሎማቶች ግን የተለዩ አስተያየቶችን ለዜና አውታሩ የገለጹ ሲሆን በርካታ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በተመሳሳይ ሁኔታ በመከሰሳቸው ለሲዊድናዊያኑ ምህረት ማድረጉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን አጣብቂኝ ውስጥ ይከታቸዋል ማለታቸው ተሰምቷል።

 

ስዊድናዊያኑ ጋዜጠኞች ባለፈው ወር የ11 ዓመት እስራት የተወሰነባቸው የኢትዮጵያ መንግስት ሽብርተኛ ብሎ የሰየመውን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባርን (ኦብነግ) በመርዳትና በማስተዋወቅ እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ የሀገሪቱን ድንበር ጥሶ በመግባት ወንጀል ተከሰው መሆኑ ይታወቃል።

 

ስዊድናዊያኑ ውሳኔውን በይግባኝ ለመቀልበስ እንደማይሞክሩና ምህረት ለመጠየቅ መወሰናቸውን ያስታወቁት ባለፈው ማክሰኞ ሲሆን ይግባኝ የማቅረቢያው ጊዜ እንዳለፈም ምክንያታቸውን ይፋ አድርገዋል።

 

“ቃል በቃል ያሉኝ እንዲህ ነው፦ በኢትዮጵያ የምህረት እና የይቅርታ አድራጊነት ባህል አለ። ተስፋችንን እሱ ላይ ለማድረግ መርጠናል” ያሉት የጆን ፔርሰን አባት የሆኑት ጄል ፔርሰን ይቅርታውን ተስፋ አድርገው እየተጠባበቁ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ጆንስ ኦድላንደር ደግሞ የጋዜጠኞቹን መጭ እድል በተመለከተ “በሁለቱ መንግስታት መሀከል የቀጥታ ንግግር እያደረግን ነው” ብለዋል።

 

በአሁኑ ሰአት ሶስት የተለያዩ በጋዜጠኞችና በፖለቲከኞች ላይ የተመሰረቱ ክሶች በመታየት ላይ ሲሆኑ በስዊድናዊያኑ ላይ የተመሰረተውን ክስ የፈረዱባቸው ዳኞች “በህግ ከታገዱ አማጽያን ጋር የፈጠሩት ግንኙነት ከተለመደው የጋዜጠኛነት አሰራር ውጭ ነው፤ ሽብርተኞችን መርዳት ሊያስብል የሚችል ነው።” ሲሉ ነበር ለ11 ዓመት በእስር ላይ እንዲቆዩ የፈረዱት።

 

የሰበአዊ መብት ተማጋቾችና ለፕሬስ ነጻነት የቆሙ አለም አቀፍ ማህበራት ካለፈው ጁን ወር ጀምሮ ቢያንስ 33 ሰዎች መከሰሳቸውን እየጠቀሱ ይህ መንግስት የጸረ ሽብር አዋጁን ተቃውሞን ለማፈን እየተጠቀመበት መሆኑን የሚያጋልጥ ነው በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ላይ ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ