አቶ በረከት ኤርትራን ተጠያቂ አድርገዋል

ሁለት ጀርመናዊያን ተጠልፈዋል

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም. January 17, 2012)፦ ባለፈው ሰኞ  ማምሻው ላይ በአፋር ክልል ይንቀሳቀሱ በነበሩ የጎብኝዎች ቡድን ላይ ማንነታቸው ያልተረጋገጠ ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ ቢያንስ 5 ሰዎች መሞታቸውና ሁለት ሌሎች ቱሪስቶች ደግሞ ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በህክምና ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ።

 

ቱሪስቶቹ የየት ሀገር ዜጎች እንደሆኑ የተረጋገጠ ማስረጃ ያልተሰጠ ቢሆንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ የዜና አውታራት አብዛኞቹ አውሮፓዊያን መሆናቸውንና ከሟቾቹ መሀል ቢያንስ ሁለቱ ጀርመናዊ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል። ከሁለቱ ቁስለኞች አንዱ ደግሞ ጣሊያናዊ ሲሆን ሌላው ሀንጋሪያን ከመሆኑም ሌላ ሁለት ጀርመናዊያንም እንደተጠለፉ ለማቀው ተችሏል።

 

የመከላከያ ሚኒስትርን ያጣቀሰ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገባ ጥቃቱ የተፈጸመው 27 ሆነው በቡድን ጉብኝት ላይ በነበሩ ጎብኝዎች ላይ ሲሆን አንድ ሰው ጉዳት ሳይደርስበት ተርፏል ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በክልሉ ቱሪስቶች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም ባውቅም የአሁኑን እርምጃ በተመለከተ ግን ስለቱሪስቶቹ ዜግነትም ሆነ ሌላ ዝርዝር መረጃ የለኝም ነው ያለው።

 

ይሁንና አሶሼትድ ፕሬስና ሮይተርን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ አለም አቀፍ የዜና አውታሮች ግን ጎብኝዎቹ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡና ብዙዎቹ አውሮፓዊያን ስለመሆናቸው የደረሳቸውን አንዳንድ ጥቆማ አካተው ዘግበዋል።

 

ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ባለስልጣን “ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው አንድ የጀርመን ጎብኝ ቡድን ላይ ጥቃት እንደደረሰበት ሪፖርት ደርሶናል። ስለሁኔታው አዲሰ አበባ ባለን ኤምባሲ በኩል እያጣራን ነው።” ማለቱ ተዘግቧል።

 

በቪየና ደግሞ የኦስትሪያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ፒተር ኮንስኪ ታይሬንታል “ሁለት ኦስትሪያዊያንን ጨምሮ 22 የሚሆኑ ቱሪስቶች ላይ ጥቃት ሳይፈጸምባቸው አልቀረም።” ብለዋል።

 

አንድ ማንነቴን ደብቁልኝ ያለ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሹምም “ሰለባዎቹ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ባመዛኙ አውሮፓዊያን መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ያምናል።” ሲል ለጋዜጠኞች ሹክ ብሏል።

 

አይሪሽ ታይምስ የተሰኘው ድረ ገጽም ጎብኝዎቹ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በኤርትራ በኩል መሆኑን ያመለከተ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን ደግሞ ሁኔታውን በተለመደ መልኩ በኤርትራ ሰልጥነው የመጡ ታጣቂዎች በቱሪስቶቹ ላይ ጥቃት እንዳደረሱ ለሮይተር ተናግረው በኤርትራ ላይ ጣታቸውን ጠቁመዋል።

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ