ሸምጋዮቹ ወደ አሜሪካ ይጓዛሉ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ.ም. May 21, 2008)፦ ምርጫ 97ን ተከትሎ በርካቶች ወደ እስር ከተወረወሩ በኋላ፣ በተለይም የቅንጅትን ከፍተኛ አመራሮችና ከምርጫው ጋር በተያያዘ የታሰሩትን ሰዎች ያስፈቱት የሀገር ሽማግሌዎች ወደ አሜሪካ በያዝነው ሣምንት እንደሚሄዱ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጡ።
እንደ ምንጮቻችን ገለፃ ከሆነ የፊታችን እሁድ አሜሪካን ሀገር ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ለሀገር ሽማግሌዎቹ የሽልማት ስነስርዓት ተዘጋጅቶላቸዋል። የሽልማቱ ምክንያት እስረኞቹን ለማስፈታት የላቀ አስተዋፅዖ በማድረጋቸው ሲሆን፣ የሽልማት አዘጋጆቹ ግለሰቦች ወይንም አካላት አልያም ቡድኖች ማንነት ለጊዜው ማረጋገጥ አልተቻለም።
በዚህ የሽልማት ስነስርዓት ላይ ይገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስኃቅ፣ ደጃዝማች ዶ/ር ዘውዴ ገ/ሥላሴ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ሊቀመንበር ሊቀ ትጉኀን አስታጥቄ አባተ እና ፓስተር ዳንኤል ገ/ሥላሴ ይገኙበታል።
እነዚህ የሀገር ሽማግሌዎች በሀገር ውስጥና በስደት ባሉት ሲኖዶሶች እና ጳጳሳት መሃከል የጀመሩትን የማስታረቅ ሥራ ይህንን የሽልማት አጋጣሚ በመጠቀም፤ ከስደተኛው ሲኖዶስ እና ከአቡነ መርቆርዮስ ጋር ስለመገናኘታቸው የታወቀ ነገር የለም።



