በጋምቤላ ክልል በምስጢር የደኅንነት አባል ሆነው ይሠራሉ የተባሉት አቶ ጌታቸው አንኮሬ ባልታወቁ ሰዎች በድንገት መገደላቸውን ተከትሎ ቀደም ሲል በክልሉ የነበረው ውጥረት በከፍተኛ ደረጃ መባባሱ ተገለጸ። የክልሉ ባለሥልጣናትና ካድሬዎችም ስጋት ላይ ወድቀዋል።

የደቡብ ክልል ተወላጅና የህወሃት አባል በመሆን በክልሉ ለረዥም ዓመታት በምስጢር የደኅንነት ሠራተኛነታቸው የሚታወቁት አቶ ጌታቸው ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ህይወታቸው ያለፈው በፕሬዚዳንቱ አቶ ኦሞት ኦባንግ መኖሪያ ቤት ውስጥ ስብሰባ ላይ ቆይተው የመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ እንደገቡ ነው።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ የመረጃ ምንጮች ከስፍራው እንዳስታወቁት የአቶ ጌታቸው ህይወት ሊያልፍ የቻለው በመኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ ባልታወቁ ሰዎች በተደጋጋሚ በጥይት ከተደበደቡ በኋላ ነው። በከተማዋ እምብርት ግድያውን ያከናወኑት ክፍሎች ለምን ጥቃቱን እንደፈጸሙ ከየትኛውም ወገን በግልጽ የተነገረ ነገር የለም።

ከሰባት ዓመታት በፊት ማንነታቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች የክልሉን እስር ቤት ሰብረው በመግባት የፖሊስ ኮሚሽነሩን ዲድዑሞ ኦሞኒ በመግደል የሚፈልጉዋቸውን እስረኞች ካስፈቱ በኋላ በጋምቤላ ከፍተኛ የደኅንነት ኃላፊ ሲገደሉ አቶ ጌታቸው የመጀመሪያ ናቸው። በወቅቱ እስረኞቹን ለማስፈታት የፖሊስን ጥበቃ አልፈው የገቡት ኃይሎች “ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደል አልመጣንም” በማለት ጥበቃ ላይ የነበሩትን ማረጋጋታቸውን ምስክሮች በወቅቱ መናገራቸውን ምንጮቻችን አስታውሰዋል።

አሁን የተከሰተው ግድያ በጋምቤላ እየተካሄደ ካለው የመሬት ነጠቃና አስገድዶ ማፈናቀል ጋር ስለመያያዙ ኃላፊነት ወስዶ የተናገረ አካል አስካሁን አልተሰማም። የጋራ ንቅናቄያችን የመረጃ ምንጮች ያሰባሰቡት አስተያየት በክልሉ በህወሃት/ኢህአዴግ አማካኝነት እየተከናወነ ያለው ኢሰብዓዊነት የተሞላው የመሬት ነጠቃና የግዳጅ ሰፈራ የፈጠረው የእምቢተኛነት ውጤት ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

ከግድያው በኋላ የአገዛዙ ታጣቂዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ ኃይሎችና ወታደሮች ገዳዮቹን በአሰሳ ለማግኘት ሲዋከቡ ታይተዋል። የዓይን ምስክሮችን ዋቢ ያደረጉት የመረጃ ምንጮች እንዳሉት ይህ ዜና እስከተቀናበረበት ሰዓት ድረስ ግድያውን ስለሰነዘሩት ክፍሎች የተገኘ ፍንጭ ስለመኖሩ የክልሉ ፖሊስ የሰጠው መግለጫ የለም። የፌዴራሉ ኃይሎች ሶስት ያካባቢው ተወላጆችና ሁለት የሌላ አካባቢ ሰዎች በጥርጣሬ ይዘዋል።

በክልሉ ያለው ውስብስብ ችግርና የአቶ ጌታቸው ግድያ የፈጠረው ስጋት ከፍተኛ በመሆኑ የጋምቤላ ከተማ በወታደሮች ጥበቃ ስር እንድትውል ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር። ሆኖም ግን የጸጥታ ሠራተኞች ፕሬዚዳንቱ በቃል ያስተላለፉትን ትእዛዝ በደብዳቤ ያረጋግጡ በመባሉ ለጊዜው ተጨማሪ ወታደሮች ሳይመደቡ ቀርቷል። ተጨማሪ ሃይል እስኪታዘዝ በሚል ጊዜያዊ የሰዓት እላፊ ተጥሎ እንደነበር ባልደረቦቻችን ከስፍራው አስታውቀዋል።

ይኸው ካድሬዎችንና የአገዛዙን አገልጋዮች ጭንቀት ውስጥ የከተተው አደጋ በኦሞ ጨለቆ አቦቦ አካባቢና በሌሎች ወረዳዎችም አለመረጋጋት በመፍጠሩ ለካድሬዎች “ማንንም አትመኑ” የሚል መመሪያ ከበላይ አካላት መሰጠቱ ታውቋል።

በክልሉ እየጠፋ ያለው የሰው ህይወትና ንብረት እንዲሁም አለመረጋጋት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን እጅግ እንደሚያሳስበው ገልጾ “ህዝብን አለማዳመጥ፣ ለህዝብ ፍላጎትና ውሳኔ አለመገዛት፣ ዜጎችን እትብታቸው ከተቀበረበት መሬት በግዳጅ በማፈናቀል መሬታቸውን የመሸጥ ዘመቻ ማካሄድ የክልሉን ነዋሪዎችና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዘነ በመሆኑ ለሚደርሰው ችግር ሁሉ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ተጠያቂ ነው” በማለት ለሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ክፍላችን አስታውቋል። በሌላም በኩል የክልሉን ተወላጆች “ሽፍታ” በማለት የተጀመረው ወከባ ተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንደሚያስከትል አኢጋን ስጋቱን ገልጾዋል።

በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ያለፈው አቶ ጌታቸው አስከሬናቸው ወደ ትውልድ አገራቸው ሆሳዕና በነጋታው መላኩን የአይን ምስክሮች አስታውቀዋል። አቶ ጌታቸው የሆሳዕና አካባቢ ተወላጅ ሲሆኑ፣ ወደ ጋምቤላ የመጡት በቀድሞው ስርዓት የሰፈራ ፕሮግራም በህጻንነታቸው ነበር። የሚያውቋቸው እንደሚናገሩት አቶ ጌታቸው በክልሉ የምስጢር የደኅንነት ሠራተኛ ሆነው ለረዥም ዓመታት ከመስራታቸው በተጨማሪ ከፌዴራሉ የስለላ መዋቅር ጋር በቀጥታ ግንኙነት ነበራቸው። በተለይም አቦቦ አካባቢ ሰፋፊ መሬት ከወሰዱ የውጪ ባለሃቶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ ጌታቸው ቤተሰቦቻቸውም ጭምር የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ አገልጋዮች እንደሆኑ ከሥፍራው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። በክልሉ አንድ ነባር የፖሊስ አባል እንደተናገሩት “ሟች በታችኛው የቀበሌ አስተዳደር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሰላይ ፖለቲከኛና ትልቅ የተባለ የገንዘብ አቅም አላቸው” በማለት አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት ፉኚዶ ከተማ በሚገኘው የወታደር ካምፕ ውስጥ “ጸጉረ ልውጦች ታይተዋል” በሚል በድንገት በተከፈተ የተኩስ እሩምታ ሶስት ሰዎች በተኙበት ህይወታቸው ሲያልፍ፣ እናቷን ያጣች አንዲት ታዳጊና በሊስትሮ ስራ የተሰማራ አንድ ወጣት መቁሰላቸውን የክልሉን ምንጮቻችንን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም። በዘገባው በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ባደረሱት ላይ ፖሊስና የክልሉ ባለስልጣናት ምንም ዓይነት ርምጃም ለመውሰድ አለመሞከራቸው ነዋሪዎቹን ክፉኛ እንዳሳዘነ ተዘግቦ ነበር። ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ሰዓት ድረስ በክልሉ መስተዳድር በኩል ኃላፊነትን መውሰድ አስመልክቶ የተሰጠ ነጻ መግለጫ የለም፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት በጋምቤላ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩ የአኙዋክ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን በአቶ መለስ ትዕዛዝና በአቶ ኦሞት ኦባንግ አስፈጻሚነት ከተጨፈጨፉና በሺዎች የሚገመቱ ከተሰደዱ በኋላ በቅርቡ አቶ ኦሞትን ከሥልጣን ለማስወገድና ለማሰር በተካሄደ ግምገማ ላይ አቶ ኦሞት “እኔ ከታሰርኩ ወታደርና መሣሪያ የሰጠኝ አቶ መለስም ይታሰራል” በማለት አቶ መለስን የዕልቂቱ ቀጥተኛ ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላም ሁኔታውን በማስተባበል ከህወሃት/ኢህአዴግ በኩል ምላሽ አለመሰጠቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዓለምአቀፉ ፍርድቤት አቶ መለስን በዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስከሰስ እየታገሉ ለሚገኙት የአኙዋክ የፍትሕ ምክርቤት፣ አኢጋን እና ሌሎች ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ሁኔታውን በቅርብ እየተከታተሉት እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)

_____________________________________

ለተጨማሪ መረጃ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነትን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ