የንግስት ሳባ የወርቅ ምንጭ ተገኘ
Ethiopia Zare (ረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ.ም. February 14, 2012)፦ ከ3 ሺህ አመታት በፊት ሰፊ ግዛት ታስተዳድር እንደነበር በአፈ ታሪክ የምትታወቀው የንግስት ሳባ (ኩዊን ሼባ) የወርቅ ማውጫ ጉድጓዷ መሆኑ የታመነበት ስፍራ በትግራይ ውስጥ ገራልታ በተባለው አምባ ተገኘ።
የአርኪዮሎጂ ግኝቱን የመራችው እንግሊዛዊቷ ሊዮዝ ስኮፊልድ በቁፋሮ ያገኘችው የወርቅ ጉድጓድ ንግስት ሳባ በስፋት ሲተረክ የኖረው የወርቅ ሀብቷ ምንጭ ሊሆን ስለመቻሉ የተለያዩ ምልክቶችን ማግኘቷን ይፋ አድርጋለች።
ቀዳሚውን ፍንጭ የሰጣት የንግስቲቷ ግዛት ልዩ ምልክት ተደርጎ የሚገመተው የፀሐይና የግማሽ ጨረቃ ምስል የተቀረጸበት 6 ሜትር ያህል ርዝመት ያለው ሐውልት ሲሆን ከድንጋዩ ስር ዘልቃ ባደረገችው ፍለጋ ንግስት ሳባ ትጠቀምበት የነበረው የሳባዊያን ቋንቋ የተቀረጸበት ጽሁፍ ለማግኘት መቻሏ ተመልክቷል።
በቁፋሮው አንድ የወደመ ቤተ መቅደስና በአካባቢው ጦርነት ተደርጎ እንደነበር የሚያሳዩ በርካታ አጥንቶች መገኘታቸውን የተለያዩ አለማቀፍ የዜና አውታራት ዘግበዋል።
“አርኪዮሎጂን ከምወድለት ነገሮች አንዱ ከአፈታሪኮችና ከጥንታዊ አማልክት ታሪኮች ጋር የሚገናኝበትን መንገድ ነው። አሁን የተገኘው የንግስት ሳባ የማእድን ማውጫ ሊሆን የመቻሉ ጉዳይ በእርግጥ የሚያስደንቅ ነው።” ስትል የቀድሞዋ የብሪቲሽ ሙዚየም ኃላፊ እንግሊዛዊቷ አርኪዮሎጂስት ሊዮዝ ስኮፊልድ ለዴይሊ ሜይል ገልጻለች።
ንግስት ሳባ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ኃያል ንግስት እነደነበረች በአፈ ታሪክ የሚነገር ሲሆን ግዛቷም የአሁኗን ኢትዮጵያንና የመንን እንደሚያጠቃልል ይታመንበታል።
ንግስት ሳባ 4ተኩል ቶን የሚመዝን ወርቅ ስጦታ በግመሎች አስጭና ጥበበኛው ሰለሞንን ለማግኘት እየሩሳሌም ድረስ መጓዟና በዚሁ በተጀመረ ፍቅርም ቀዳማዊ ምኒሊክን መጸነሷ በአፈታሪክ ሲተረክ የቆየ ነው።
የክረስትና ሀይማኖት መሰረት በሆነው መጽሐፍ ቅዱስም በመጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ ምዕራፍ 10 ቁጥር 2 - 3 ላይ ...በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ፤ የከበረም እንቁ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ እየሩሳሌም ገባች ወደ ሰለሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው።... የሚል ይነበባል።
አርኪየሎጅስቷ ስኮፊልድ አስፈላጊውን ወጭ መሸፈኛ እንዳገኘች ሙሉ ቁፋሮ የምታካሂድ መሆኗን አረጋግጣለች። አያይዛም፦ “በዚህ ቁልቋልና ግራር በሞሉበት ድንጋያማ ጥንታዊ ቦታ ላይ ቆሜ ንግስቲቱ ባሪያዎቿንና ከወርቅ ማውጫው ድንጋይ እየጎተቱ የሚሄዱ ዝሆኖቿን ስትቆጣጠር በአይነ ሕሊናዮ ማየት አይገደኝም።” ማለቷን ዘ ጋርዲያን አጣቅሶታል



