በኦሞ ሸለቆ የ200ሺህ ዜጎች ህይወት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል!
“አንፈናቀልም” ያሉ እየታሰሩ ነው
Ethiopia Zare ( ሐሙስ የካቲት 8 ቀን 2004 ዓ.ም. February 15, 2012)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ በመባል የሚታወቀው አካባቢ መንግስት በህንድ ኩባንያዎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለሚታገዘው ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮግራም እንዲውል 300ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመመደቡ የአካባቢው ነዋሪዎች ህልውና አደጋ ውስጥ ወደወቋል ሲል አልጀዚራ ዘገበ።
መንግስት ለስኳር ልማት የመረጠው ይህ አካባቢ 200 ሺህ የሚጠጉ የአካባቢውን ከብት አርቢ መኖሪያ ሲሆን በመከላከያ ሰራዊቱ አማካኝነት ወደ አካባቢው የሚያስገቡ በርካታ መንገዶች ተዘግተው ዜጎች በግዳጅ እየተፈናቀሉ ስለመሆኑ ተዘግቧል።
ተቀማጭነቱን በዩ.ኤስ አሜሪካ ያደረገው የኦክላንድ ኢኒስቲቲዩት ባወጣው ሪፖርት ላይ የመከላከያ ሰራዊቱ በኦሞ ሸለቆ በተለይም ቦዲ፣ ሙርሲ እና ሱሪ በተባሉ መንደሮች ተገኝቶ ነዋሪዎቹ ስለ ስኳር እርሻው ያላቸውን አመለካከት የጠየቀ ሲሆን በሚቃወሙት ላይም ግፍና እንግልት አድርሶባቸዋል።
ከዚያም አልፎ የመፈናቀሉን ሀሳብ የተቃወሙ በርካታ ነዋሪዎች በየእስር ቤቶቹ የተወረወሩ ሲሆን ወታደሮቹ አስገድዶ መድፈር ሳይቀር ይፈጽሙ እንደነበርም በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ለእርሻ ልማት እንዲውል የታሰበው የኦሞን ማጎ ብሔራዊ ፓርክ አብዛኛውን የኦሞ ሸለቆ የሚያካልል ሲሆን ህይወታቸውን በሙሉ የአካባቢው ነዋሪዎች የነበሩ በርካታ ዜጎች ከመንግስት ወታደሮች ጋር ከመዋጋት ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው እየተናገሩ ነው።
በሰበአዊ መብቶች አከባበር ዙሪያ የሚሰራ አንድ የአካባቢው ሰው ለጋዜጠኞች እንደገለጸው ከሆነ “ብዙ ነዋሪዎች የሚኖሩት በፍርሀት ነው ይሁንና አሁን የቀራቸው ነገር ስለሌለ ተገደን ከምንፈናቀል ይልቅ እንዋጋለን እያሉ ነው። ሁኔታው ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ ስጋት አለን።” ብሏል።
አንድ የጎሳ አለቃ እንባ እየተናነቀው “ሁሉንም ነገር ልናጣ ነው። የአደን ስፍራችን፣ የግጦሽ መሬታችንም ሆነ መኖሪያ ቤታችን መቅለጡ ነው። ያለአንዳች ነገር ባዶ እጃችንን ይዘን መቅረታችን ስለሆነ የውጭው አለም እንዲድርስልን እንሻለን።” ሲል ለጋዜጠኛው ብሶቱን አሰምቷል።
ባለፈው አመት መጀመሪያ ላይ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳቸው ጋር በተያያዘ በስልጣኔ ወደሗላ የቀረ ነው ያሉትን ይህንን ዞን በመጭው አምስት አመት ውስጥ የመስኖ ፕሮጄክቶችና የእርሻ ልማቶች አስፋፍተን የፈጣን ልማት ምሳሌ እናደርገዋለን ማለታቸው ይታወሳል። ይሁንና ይህ ፕሮጄክት የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስገኝ ሊረዳው ቢችልም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ግን ህልውና የሚያሳጣ በመሆኑ ተኮንኗል።
ባኳያውም ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የአለማችን ቅርሶች በሚል በዩኔስኮ በተመዘገበው በዚህ ታሪካዊ ስፍራ ላይ የተዘረጋው ፕሮጄክት ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል ነው በሚል የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን ስጋት ውስጥ ጥሏል።
ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል የተባለው የጎሳዎች መብት ተሟጋች ድርጅት ማፈናቀሉ እንዲቆምና የእርሻው እቅድ እንዲሰረዝ የጠየቀ ሲሆን በዚህ አመት ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው የጊቤ 3 ግድብ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች አንዱ የኦሞን ወንዝ በመገደብ በዙሪያው የሚኖሩ ጎሳዎችን ራሳቸውን መመገብ የማይችሉበት ደረጃ ሊያደርሳቸው ይችላል በሚል ተወግዞ እንደነበርም ይታወሳል።
“አሁን ግን ጎሳዎቹ ለከብቶቻቸው የሚያውሉት የግጦሽ መሬታቸው ሳይቀር ለመንግስትና ለውጭ ካምፓኒዎች ሊሰጥባቸው መሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል።” ትላለች ሊዝ ሀርተር የተባለችው የሰርቫይቫል አክቲቪስት።
በቅርቡ ለሳውዲት አረቢያና ለቻይና ሩዝ አምራቾች ሲባል 70ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ከጋምቤላ አካባቢ በግዳጅ መፈናቀላቸው ይታወሳል። ይህ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች የአገሪቷን ሰፋፊ መሬቶች እንዲቆጣጠሩ መደረጉ በመዲናወ በአዲስ አባባ ሳይቀር ህዝቡን እያሸበረው መሆኑን የአልጃዚራ ሪፖርት አጣቅሷል።
“ይህ አዲስ አይነት ቅኝ አገዛዝ ነው።” የሚለው አንድ በአዲስ አበባ የሚኖር መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰራተኛ “ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የሀገሪቷ ሰፋፊ ግዛቶች በውጭ አገራት ኢንቨስተሮች እየተወሰዱ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ የት እንደምንገኝ ማሰቡ ያስፈራል።” ሲል ስጋቱን አሰምቷል።
ብዙዎቹ የቻይናና የህንድ ካምፓኒዎች ሰራተኞቻቸውን ሳይቀር ከአገራቸው የሚያስመጡ በመሆኑ ለኢትዮጵያዊያኑ ስራ እድል ከመፍጠር ይልቅ ይብሱኑ እድሉን እየነሷቸው መሆኑ ተተችቷል።



