በኢሳት የተጀመረው እወካ ለአረብ ሀገራት ተርፏል

የእውቀት ማነስ ነው ተብሏል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ የካቲት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. February 18, 2012)፦ የኢትዮጵያ መንግስት የተቃዋሚዎችን ድምጽ ለመገደብ የተያያዘው የጃሚንግ (የእወካ) ስራ በርካታ የአረብ ቴሌቭዥን ጣቢያዎችንም ከስርጭት ውጭ እያደረጋቸው መሆኑ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል።


አዲሷ የእወካው ሰለባ የሆነችው ሊባኖስ ስትሆን ፍጹም ፈላጭ ቆራጭ እየሆነ የመጣው ኢህአዴግ ተቃዋሞዎቹን ለማፈን የወሰደው እርምጃ በምትኩ የተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎቿን ስርጭት ማገዱን ኮንናለች።


የሊባኖስ የቴሌ ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር የሆኑት ሚ/ር ኒኮላስ ሴኖይ የስርጭቱን መታፈን በተመለከተ የተደረገው ቅድመ ምርመራ ሲግናሉን የምታፍነው ኢትዮጵያ መሆኗ መረጋገጡን ትላንት ፌብርዋሪ 17 ቀን ለጋዜጠኞች ይፋ አድርገዋል።


“ስርጭቶቻችን የታፈኑት ከኢትዮጵያ መሆኑን የአረብ ሳት የነገረን ሲሆን ድርጊቱን በማውገዝ ለኢትዮጵያ መንግስት የላኩትን የተቃውሞ ደብዳቤ ኮፒውን ሰጥተውናል።” የሚሉት ሚኒስተር ኒኮላስ ሴኖይ “ይህ የጃሞንግ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት አለበት!” ሲሉ በአጽንኦት አሳስበዋል።


ይህ ኢትዮጵያ መንግስት የተቃዋሚዎቹን ድምጽ ለማፈን ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ እያፈሰሰ የተያያዘው የጃሚንግ ስራ በተለይ በኢትዮጵያዊያን ሳደላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) እና በኤርትራ ቲቪ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ቢታመንም ድርጊቱ ያላነጣጠረባቸውን በርካታ የአረብ ሀገራት ቴሌቭዥን ጣቢያዎችንም ከስርጭት ውጭ ማድረጉ አልቀረም።


ሌላው ቀርቶ ባለፈው ወር ውስጥ የገዛ ራሱን ብቸኛ ቴሌቭዥን ጣቢያ (ኢቲቪን) ሳይቀር ከአየር ውጭ ለማድረግ መብቃቱን አጣቀሶ አንድ የሊባኖስ የዜና አውታር የኢትዮጵያ መንግስት የማፈኛ ማሽኖቹን የአጠቃቀም ብቃቱ የአረብሳት ሀላፊዎችን በእጅጉ እያሳሰባቸው መሆኑን ዘግቧል።


ባለፈው አመት ውስጥ ዋና ቢሮውን በኳታር ያደረገውን የአልጀዚራ አረብኛ ቻናልን ጨምሮ የቪኦኤና የዶቼ ዌሌ ራዲዮ ጣቢያዎችን አፈና ሲደርስባቸው መቆየቱ ይታወሳል።


በአሁኑ ወቅት የችግሩ ሰለባ የሆኑ መንግስታትና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች የኢትዮጵያ መንግስት ሲግናል በማወክ የሚፈጽመውን ተግባር እንዲያቆም እንዲያስገድዱት ካልሆነ ግን ብቸኛውን የመንግስት ቲቪውን (ኢቲቪን) ከኔትውርካቸው እንዲዘጉት በሁለቱ የሳተላይት ኔትዎርክ ካምፓኒዎች (አረብሳት እና ናይልሳት) ላይ ግፊት እያደረጉ መሆኑ ተዘግቧል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ