ዛሬ በአዲስ አበባ ድንገተኛ ፍተሻ ተካሄደ
Ethiopia Zare (ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2000 ዓ.ም. May 23, 2008)፦ ዛሬ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ እንደሚያስረዳው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ብዛት ያላቸው የፌደራል ፖሊሶች መንገደኞችንና መኪኖችን በማስቆም ከፍተኛ ፍተሻ በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል።
በተለይ በቦሌ አካባቢ ሁኔታውን የተከታተሉ የዓይን ምስክሮች ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጹት በመንገድ ላይ ግራና ቀኝ ሆነው በረጅሙ ተሰልፈው የነበሩት የፌደራል ፖሊሶች ራዲዮ የያዘውንና ፊሽካ በመንፋት ትዕዛዝ ያስተላለፈውን አዛዥ በመከተል በአካባቢው የሚገኙ መንገደኞችንና መኪኖችን በማስቆም ለረዥም ሰዓታት ፍተሻ ሲያካሂዱ መቆየታቸውንና እነሱም ተፈትሸው ማለፋቸውን የመሰከሩ ሲሆን፣ ፍተሻው የችኮላና ትህትና ያልነበረው መሆኑን ገልጸዋል።
ሁኔታውን ለማጣራት ባካሄድነው ሙከራም በተለያዩ ቦታዎች ተመሳሳይ ድንገተኛ ፍተሻ እየተካሄደ መሆኑን ያረጋገጥን ሲሆን፣ አንዳንድ ምስክሮች እንደሚሉት የዚህ አይነት ከፍተኛ ፍተሻ ከምርጫ 97 በኋላ የመጀመሪያው ነው ሲሉ ተሰምተዋል።



