ስብሃት ገ/እግዚአብሔር በመጨረሻዋ ሰዓት
“በሰላም ነው ማረፍ የምፈልገው ከዚህ በሗላ መኖር አያሻኝም።” ጋሼ ስብሃት
“አካሉ ቢደክምም አእምሮው ግን አስከመጨረሻው የሰላ ነበር” ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ የካቲት 13 ቀን 2004 ዓ.ም. February 21, 2012)፦ በስነ ጽሁፍ ስራዎቹ ከፍተኛ ዝናንና ክብርን ያተረፈው አንጋፋው የስነ ጽሁፍ ሰው ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ባደረበት የጉሮሮ ካንሰር ህመም ምክንያት ሰኞ የካቲት 12 ቀን ከሌሊቱ 9ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል (ኢዛዝክ) ያነጋገረው የስብሃት የልብ ወዳጅ የሆነው ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ “ስብሃት ሰውነቱ ቢደክምም እንኳን አእምሮው ግን እስከመጨረሻዋ ሰዓት የሰላ ነበር።” በማለት የወዳጁን የመጨረሻ ሰዓት ገልጿል።
ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ስብሃትን ከትውውቃችሁ አንጻር በአጭሩ እንዴት ትገልጸዋለህ ተብሎ በተለይ ከኢትዮጵያ ዛሬ ለቀረበለት ጥያቄ “በስነ ጽሁፍ ዓለም ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ህይወት ዙሪያም ስለሰው ልጅ እየተጎዳ የኖረ፤ አስተዋይና ዕድሜውን ሁሉ ለበጎ ተግባር የተጠቀመበት ታላቅ ሰው ነው።” ብሎታል።
በህመም እንደሚሰቃይ የታወቀው ጥር 7 ቀን ሲሆን በወቅቱ በተዋናይነት በሚሰራበት አዲስ ፊልም ቀረጻ ላይ ነበር። በመጀመሪያ ወደ ዩኒቨርሳል ክሊኒክ የተወሰደ ሲሆን በሗላም በቤተ ዛታ ክሊኒክ ለ11 ቀናት ተኝቶ ምርመራ እንደተደረገለት ተመልክቷል።
ከዩናይትድ ቪዥን ላቦራቶሪ የተገኘው የምርመራ ውጤት እንዳረጋገጠው ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ህመሙ የጉሮሮ ካንሰር መሆኑ ታውቋል። ይሁንና ከእድሜውና ከሰውነቱ መድከም አንጻር የካንሰር ትሪትመንቱን መቋቋም እንደማይችል ነበር የታመነበት።
በህክምናው ወቅት ምግብ በቲዩብ ለሰውነቱ እንዲደርስ የተደረገ ቢሆንም ህይወቱ ረጅም ሊሆን እንደማይችል የተገነዘበው ጋሼ ስብሃት ግን “በሰላም ነው ማረፍ የምፈልገው ከዚህ በሗላ መኖር አያሻኝም።” በሚል የምግብ ማስተላለፊያ ቱቦውን ነቅሎ ጥሎት እንደነበር ታውቋል።
ይሁንና ወዳጆቹ አግባብተውት ዳግም ቲዩቡ እንዲቀጠል ቢፈቅድም እንኳን የጉሮሮረው ቀዳዳ በመደፈኑ የምግብ ማቀበያ ቱቦውን በቀጥታ በሆዱ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቤተሰቦቹ በሁኔታው ላይ ከተማከሩ በሗላ የመጨረሻ የህይወት ቀናቱን ከስቃይ ነጻ ሆኖ እንዲያሳልፍና “በሰላም ልረፍ” በማለት ታላቁ የስነ ጽሁፍ ሰው የጠየቀውን ጥያቄ ለመቀበል በመገደዳቸው የመጨረሻዎቹን 3ቀናት ጋሸ ስብሃት ያለምግብ ቆይቶ ማረፉን ለመረዳት ችለናል።
የህክምና ወጭውን በመሸፈን ያስታመሙት ወንድሙ ዶ/ር ተወልደ ገ/እግዚአብሔር መሆናቸውንም የዝግጅት ክፍላችን አረጋግጧል።
ስብሃት ይሰራበት የነበረው ፊልም ከግማሽ በላይ ቀረጻው በመጠናቀቁ ምናልባት አዘጋጆቹ መላ ፈጥረው ለእይታ ያበቁት ይሆናል በሚል ወዳጆቹ ተስፋ አድርገዋል።
ደራሲ፣ ጋዜጠኛ፣ የትወና ባለሙያና፣ መካሪ በመሆን የሚታወቀው ስብሃት ገ/እግዚአብሔር በታሪካዊዋ አደዋ ከተማ በ1928 ዓ.ም የተወለደ ሲሆን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ትምህርቱን ከመከታተሉም በላይ ልቦለድና ታሪክ ቀመስ ልቦለዶችን በአማርኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች በማሳተም በአንባቢያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ አንጋፋ የስነ ጽሁፍ ሰው መሆኑ ይታወቃል።
ስብሃት ገ/እግዚአብሔር በሀገሪቱ ይታተሙ በነበሩና በአሁኑ ሰዓትም በሚታተሙ ጋዜጦች ላይ የተለያዩ ጽሁፎችን ያበረከተ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያን ሄራልድ እና በአዲስ ዘመን ጋዜጦች ላይ ለረዥም ጊዜ በጋዜጠኝነትና በአምደኝነት የሰራ መሆኑ ተመልክቷል።
ደራሲ ስብሃት ከፍተኛ አድናቆትን ካተረፉለት ስራዎቹ መሀከል ትኩሳት፣ ሌቱም አይነጋልኝ፣ አምስት ስድስት ሰባት፣ ሰባተኛው መላክ፣ የተሰኙት መጽሀፎቹ የሚጠቀሱ ሲሆን በተለይ እግረ መንገድ በሚል ርእስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የሚያወጣቸው ጽሁፎቹ በአንባቢያን ዘንድ ተወዳጅ እንደነበሩ የሚዘነጋ አይደለም።
የቅርብ ጓደኛውና የመነን መጽሔት ባልደረባው የነበረው በዓሉ ግርማ ደራሲው በሚል ርእስ ስር በጻፈው መጽሐፉ በጋሽ ስብሃት ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን እንደነበር ሲታወቅ እስከ እልፈቱ ድረስ ከጎኑ ያልተለየው ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ደግሞ ‘ማስታወሻ’ በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፉ የጋስ ስብአትን ስብእናና የአስተሳሰቡን ከፍታ ልክ አስፈትሾበታል።
ለጋሼ ስብሃት ቤተሰቦች፣ የቅርብ ወዳጆች፣ ለመላ የስራዎቹ አድናቂዎችና የስነጽሁፍ አፍቃሪዎች መጽናናትን ይሰጣችሁ ዘንድ የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ከልብ ይመኛል።