የየመኑ አብደላ ሳላህ ወደ አዲስ አበባ ሸሽተዋል ተባለ
“ወደ የመን የሚመለሱ አይመስለኝም” ዲና ሙፍቲ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ የካቲት 17 ቀን 2004 ዓ.ም. February 25, 2012)፦ በህዝባዊ የተቃውሞ ማእበል ከስልጣናቸው የተወገዱት የየመኑ ፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ሳላህ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ወደ የመን ተመልሰው እንደማይሄዱም እየተገለጸ ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት ዲና ሙፍቲ ሳላህ ወደ አዲስ አባባ የመጡት ከትላንት በስቲያ ሀሙስ መሆኑን ገልጸው “ወደ የመን ይሄዳሉ ብዬ ግን አላስብም።” ሲሉ በይፋ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከወራት በፊት በተደረገውና በአሜሪካ መንግስት ገፋፊነት አሊ አብደላ ሳላህ ፕሬዚዳንት የሚለውን ስም ብቻ ይዘው ሙሉ ስልጣኑን ግን ለምክትላቸው ማስረከባቸው ሲታወስ ባለፈው ማክሰኞ በተደረገው ምርጫ ምክትላቸው አቤድ ራቦ መንሱር ሀዲ ፕሬዝዳንት ተብለው ተመርጠዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ዛሬ ቅዳሜ ፌብሪዋሪ 25 ቀን ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳላህ መጭው ህይወታቸው አጠያያቂ ሲሆን ወዳጃቸው አሜሪካ በስደተኛነት እንደማትቀበላቸው እና ሌላ ወዳጅ አገር ግን ሳታፈላልግላቸው እንደማትቀር አንዳንድ አለማቀፍ የዜና አውታራት ዘግበው እንደነበር ይታወቃል።
ከእነዚህ ያስጠጓቸዋል ተብለው ከሚገመቱ ሀገራት መሀል የሳውዲት አረቢያና የኢትዮጵያ ስም በአንዳንድ ወገኖች ተናፍሶ የነበረ ሲሆን የአሁኑ የአዲስ አበባ ጉዟቸውና የዲና ሙፍቲ “ወደ የመን የሚመለሱ ሰይመስለኝም” የሚለው ገለጻ ምናልባትም ጉዟቸው ለዘላቂ ህይወታቸው መቆያ ሊሆን ይችላል የሚል ግምትን አስከትሏል።
አሊ አብደላ ሳላህ ወደ ኢትዮጵያ ያመሩት ባለፈው ጁን ወር ላይ የግድያ ሙከራ በተደረገባቸው ወቅት ከደረሰባቸው ጉዳት ጋር በተያያዘ ለሶስት ሳምንት ያህል ህክምና ሲደረግላቸው ከቆዩበት ዩ.ኤስ. አሜሪካ ሲሆን በቀድሞው ምክትላቸው ፕሬዝዳንታዊ ቃለ መሀላ ስነ ስርአት ላይ እገኛለሁ ብለው እንደነበር ይታወቃል።



