ከአዲስ አበባ የመጡት የኦርቶዶክስ አባቶች የሽምግልና ቃላቸውን ማፍረሳቸው ተገለጸ
“የሽምግልና ጉባኤው ላደረገው ጥረት ሊመሰገን ይገባል” ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መልከ ጸዲቅ
“ቤተ ክርስቲያኗ ለ4 ተከፍላለች” ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ
“በህገ መንፈሳዊ መሰረት በፓትርያርክ ላይ ሌላ አይሾምም ከተሾመም ለመጀመሪያው ይጸናል” መላከገነት ገዛኸኝ
Ethiopia Zare (ሰኞ የካቲት 19 ቀን 2004 ዓ.ም. February 26, 2012)፦ በብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስና በአዲስ አበባ ተቀማጭነቱን ያደረገው በአቡነ ጳውሎስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ መሀከል ከሳምንት በላይ የፈጀው በአሜሪካዋ ግዛት አሪዞና ድርድር ለለቀጣይ ውይይት ለሀምሌ የተቀጠረ ቢሆንም የአዲስ አበባ ተደራዳሪዎች የሽምግልና ቃላቸውን ማፍረሳቸው ተዘገበ።
ከዋሽንግተን ዲሲ እግራቸው ሳይለቅ ሽምግልና ቃላቸውን በተለይ ህዝቡን ተስፋ ላለማስቆረጥ በሁለቱም ሲኖዶሶች መሀከል ህዝብን የሚለያይና የሽምግልና ሂደቱን ከሚያስተጓጉል ተግባር እንዲቆጠቡ የተላለፈውን የጋራ ውሳኔ አፍርሰው በውጭ ሀገር የሚገኘውን ቅዱስ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን የሚነቅፍ ንግግር በዋሽንግተኑ ማድረጋቸው ታውቋል። በአቡነ ገሪማ የተመራው የአዲስ አበባ ሲኖዶስ መልእክተኞች የተናገሩት አፍራሽ ትምህርትና ንግግር በምስልና በድምጽ መረጃወች መገኘቱ ተገልጿል።
ይሄው በአዲስ አበባ አባቶች የተሰጠው የተዛባ መልእክት ሽማግሌዎቹንና ህጋዊውን ሲኖዶስ እንዳሳዘነ በተለይ በውጭ የሚገኙ አባቶች ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።
በሽምግልናው ወቅት በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ ህዝባዊ እርቅ ተደርጎ በውጭ ሀገር የሚገኙ ምእመናንና ህዝብ በሰላም ሀገሩ የሚገባበትና የሚወጣበት ሁኔታ እንዲመቻችና በቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና መሻሩን እንተማመን በሚል ጽኑ አቋሙን አስተላልፏል። በሌላ ወገን ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶሰ ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ በሀገር ቤት ተመልሰው የአንድ ደብር የበላይ ጠባቂ ሆነው በጡረታ መልክ ህክምናና አስፈላጊው ነገር ተሟልቶላቸው እንዲገቡ የሚል የመደራደሪያ ሀሳብ ይዞ የቀረበው የአዲስ አበባ አባቶች ይዘውት የመጡት ሀሳብ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ህግ መሰረት በጠቅላላ የጵጵስናና በተለይ የፓትርያርክነት ስልጣን ምንም አይነት የጡረታ መብት የሌለው በቅድስና እስከ እለተ ሞት የሚሰጥ ታላቅ ስልጣን መሆኑን በቤተ ክርስቲያኗ ህግና ደንብን በድጋሚ የሚጥስ መሆኑን አባቶች ሲያብራሩ ተመልክቷል።
በውጭ ሀገር የሚገኘው ሲኖዶስ ለሽምግልና የተሳተፉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መልከጻዲቅ፣ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ እና መላከገነት ገዛኸኝ የድርድሩን መንፈስ በዋሽንግተን ዲሲ አውከውትና ለወደፊት ቀጣይ ነው የተባለውን የሰላም እርቅ በከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ ጥለው የሄዱትን በአቡነ ገሪማ የሚመራውን ቡድን በሚመለከት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ የገለጹ ሲሆን በተለይ ሊቀ ካህናት እንግዳ ቤተ ክርስቲያኗ ለአራት የተከፈለች በሆኗንን አብራርተዋል።
በውጭ ሀገር ያለው ሲኖዶስ፣ በሀገር ቤት መቀመጫውን ያደረገው ሲኖዶስ እና ገለልተኛ ነን በሚሉ ወገኖች መሀከል ያሉ ልዩነቶችና በአራተኛ ደረጃ በፖለቲካ ምክንያትም ቢሆን በኤርትራ የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ ያብራሩት ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ በተለይ ኤርትራ ከ50 ዓመት በላይ በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት በነበረች ጊዜ እንኳን ቤተ ክርስቲያኗ በነበረው ፖለቲካ ሳትናወጥ አንድ እንደነበረች አስታውሰው እንደምሳሌነትም በካቶሊክ አንድ ፓፓ ብቻ በመላ አለም የሚገኙ ካቶሊካዊያንን እንደሚያገለግሉ አጣቅሰዋል።
በውጭ ሀገር ያለው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጸሀፊ የሆኑት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መልከጻዲቅም በስደት የሚገኘው ህዝብ በሰላም ሀገሩ የሚገባበት ሁኔታ እንዲመቻች እንደሚመኙ ገልጸው ከሀገር ቤት የመጡት አባቶች የሽምግልና ሂደቱን የሚያደናቅፍ ተግባር ቢፈጽሙም ለሽምግልናው ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገውን የሽማግሌዎች ጉባኤ በእጅጉ እንደሚያመሰግኑ አስታውቀዋል።
በውጭ ላለው ሲኖዶስ ተደራዳሪዎች አንዱ የሆኑትና በተለይ የቀኖና ህጉን ፍንትው በማድረግ ያስቀመጡት መላከ ገነት ገዛኸኝ ደግሞ “ህግ መንፈሳዊ በሚያዘውና በሚፈቅደው መሰረት ፓትርያርክ እያለ ፓትርያርክ አይሾምም ከተሾመም ደግሞ ለቀደመው፣ ቀድሞ ለተሾመው ትጽና ይላል።” ብለዋል በማስከተልም “… አንድ ቅዱስ ፓትሪያርክ ከታመመ ምን መደረግ እንዳለበት ህግ መንፈሳዊ አንቀጽ 4 ቁጥር 69 ምን ምን መደረግ እንዳለበት ይናገራል” ሲሉ በተለይ ፕትርያርኩ ከመሰደዳቸው በፊት የነበረውን ሁናቴ በማስታወስ ህጉን የተከተለ እንዳልነበር አብራርተዋል።
አባቶቹ በተለይ በህዝብ ዘንድ አንዳንድ ሰዎች ፓትርየርኩ መሰደድ የለባቸውም ይላሉ ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።
ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና አዲሱ አበበ እና አበበ በለው በውጭ ሀገር ለሚገኙት አባቶች ያቀረቡትን ጥያቄዎችና መልሶችን ሙሉ ቃል ለማዳመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!



