2ቱ ጀርመናዊያን ታጋቾች ተለቀቁ
"ያቆየኋቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች መንገድ ዘግተውብኝ ነው" - አርዱፍ
Ethiopia Zare (ረቡዕ የካቲት 28 ቀን 2004 ዓ.ም. March 7 , 2012)፦ የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ላለፉት 7 ሳምንታት ያህል አግቶ ያቆያቸውን ሁለት ጀርመናዊያን ጎብኚዎች ለአካባቢው ሽማግሌዎችና በኢትዮጲያ ለጀርመን ኤምባሲ ተወካዮች አሳልፎ እንደሰጠ ትላንት ማክሰኞ የካቲት 27 ቀን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ጀርመናዊያኑ የታገቱት ባለፈው ጥር 9 (ጃንዋሪ 18) ቀን በአማጺያኑና በመንግስት ወታደሮች መሀል ውጊያ በተካሄደበት ወቅት መሆኑ ሲታወስ በወቅቱ አምስት ሌሎች ጎብኚዎች መገደላቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ መንግስት ጥቃቱ የተፈጸመው 22 ጎብኚዎችን ባካተተው ቡድን ላይ አማጺያኑ ተኩስ በመክፈታቸው ነው በሚል በወቅቱ የከሰሰ ቢሆንም አማጺው ቡድን ግን የተኩሱ መንሳኤ ጎብኚዎቹን ያጀቡት የኢትዮጲያ ወታደሮች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጋዮቼ ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ በተደረገ ውጊያ ነው ከማለቱም በላይ አምስቱ ቱሪስቶች የተገደሉትም ከመንግስት ወታደሮች በተተኮሱ ጥይቶች ነው ሲል መወንጀሉ ይታወቃል። እንደ አርዱፍ ገለጻ ከሆነ በወቅቱ በተደረገው ውጊይ 16 በህወሀት የሚመሩ የመንግስት ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን 2 አማጺያን ደግሞ በመንግስት ሀይሎች ተይዘው ተወስደዋል።
“ቱሪስቶቹን በሰላም እንዳንመልስ የኢትዮጲያ መንግስት የፈጠረብንን መሰናክል ተቋቁመን፡ ትላንት ማርች 5 (የካቲት 26) ምሽት ላይ የጀርመን አምባሳደር ምክትል በሆኑት በሚ/ር ማይክል ባዮንታይኖ የሚመሩ የኤምባሲው ተወካዮች በተገኙበት፤ በደራሳ አብደላ አልዩ ለተላኩት የአካባቢው ሽማግሌዎች አስረክበናቸዋል።“ የሚለው አርዱፍ ታጋቾቹ ላለፉት ሶስት ሳምንታት እንክብካቤ እየተደረገላቸው የቆዩት እዚያው በአፋር ክልል መሆኑንም አስታውቋል።
እንደ አርዱፍ መግለጫ ከሆነ ታጋቾቹን ቀደም ብሎ ለመልቀቅ የተደረገው ጥረት የመንግስት ወታደሮች አካባቢውን ዘግተው ለእንቅስቃሴ አዳጋች በማድረጋቸው ምክንያት ነበር ሳይሳካ የቀረው።
አርዱፍ ሁለቱን በስም ያልጠቀሳቸውን ታጋቾች ለደረሰባቸው እንግልት ይቅርታ ጠይቆ በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ያለውን ልባዊ ምኞት በመግለጫው ላይ ገልጿል።
የሁለቱን ታጋቾች መለቀቅ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለጊዜው የሰጡት አስተያየት ያለመኖሩን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዘገበ ሲሆን የጀርመን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ስለታጋቾቹ መለቀቅ ማረጋገጫ መስጠት አልችልም ማለቱን ሮይተርስ ይፋ አድርጓል።
"ለታጋቾቹ ደህንነት እና ለጉዳዩ ዕልባት ለመሻት ስንል ለጊዜው ተጨማሪ አስተያየት መስጠት አንፈልግም" በማለት የጀርመን የውጪ ጉዳይ መ/ቤት ለጊዜው ዝምታን መምረጡ ተጠቁሟል።
ባለፈው ወር አርዱፍ ታጋቾቹን ለመልቀቅ ያለወን በጎ ፍቃድ ጠቅሶ ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ሀይል የሚከፍተው ማናቸውም አይነት የሀይል እርምጃ ግን የቱሪስቶቹን ደህንነት አደጋ ላይ ይጥለዋል በሚል ማስጠንቀቁ ይታወቃል። ትላንት ባወጣው መግለጫው ላይም ከጃንዋሪው ውጊያ ወዲህ በአማጺያኑና በመንግስት ወታደሮች መሀል በተለያዩ ጊዚያት ወታደራዊ ግጭቶች መፈጸማቸውን ይፋ አድርጓል።
አርዱፍ ካሁን ቀደምም (በ2007 ዓ/ም) አምስት አውሮፓዊያን ጎብኚዎችንና ስምንት ኢትዮጵያዊያንን አግቶ የነበረ ሲሆን አውሮፓዊያኑን ከአስራ ሁለት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያዊያኑን ደግሞ ለሁለት ወራት ያህል አቆይቶ መልቀቁ ይታወሳል።



