የቀድሞ የዩኒቲ ኮሌጅ ባለቤት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠየቁ
“ነገሮች እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ዝም ብለን በመመልከታችን ይቅርታ ልጠይቅ እፈልጋለሁ” ዶ/ር ፍስሓ እሸቱ
Ethiopia Zare (ረቡዕ የካቲት 28 ቀን 2004 ዓ.ም. March 7, 2012)፦ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ባለቤት የነበሩት ዶ/ር ፍስሐ እሸቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ይህ ሁሉ በደል ሲደርስ ዝም ብለው መመልከታቸው አግባብ እንዳልነበረ ገልጸው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠየቁ።
“ነገሮችን ዝም ብለን እያየን እዚህ ደረጃ ላይ እሲኪደርሱ መመልከታችን፤ አያገባንም ብለን መቀመጣችን፤ እኔ በበኩሌ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በጣም በጣም በጣም ቅር የሚለኝ ነገር ነው። ለዚያም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ።” በማለት ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ የይቅርታ መልእክታቸውን በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ገልጸዋል።
ዶ/ር ፍሰሃ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገዛዝ ምንም አይነት ስራ የማያሰራና ህዝቡን ያለአግባብ እየጨቆነ ያለ አገዛዝ መሆኑን ገልጸው ለሀገሪቱ መጻኢ ሂደት ጠቃሚ ሊሆን የሚችል የሽግግር ምክር ቤት (ካውንስል) መቋቋም አለበት በማለት በሰሜን አሜሪካ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት በአሁኑ ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ በኢሳት ራዲዮ ቀርበው የኢትዮጵያ ህዝብ ዝም ብለን ስንመለከት የቆየን ዜጎች “ይቅርታ መጠየቅና ለወደፊቱ ራሳችንን ማጽዳትና ከራሳችን ጋር የምንታረቅበት ጊዜ የደረሰ ይመስለኛል” ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያዊያን የሽግግር ካውንስል የሚል ተቋም በማቋቋም ላይ ያሉት ዶ/ር ፍሰሃ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅን ለባለሀብቱ ሸክ ሙሐመድ አላሙዲ ከሸጡ በሗላ በውጭ ሀገር እንውስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበርና በመጭው በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት ችግር ቢከሰት ተደራጅቶ የሚጠብቅ ከሁሉም ወገን የተውጣጣ ሀይል ሊኖር ይገባል በሚል ሀገር አቀፍ ተቋም በመመስረት ላይ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን ይህንን አላማቸውን ለማሳካት አንድ ሳንቲም እስክትቀራቸው ለመስራት ቆርጠው መነሳታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚህ አይነት ሁኔታ ሀገርንና ህዝብን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ መለመድ ያለበት ታላቅ ጉዳይ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል። በሀገራችን ያለውን አስከፊ አገዛዝ ለማንበርከክ ከሸፍጥ ነጻ የሆነ ልባዊ ይቅርታ የሚጠይቁ ወገኖች ሊበረታቱና ሊበዙ ይገባል በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት ነዋሪነታቸው በካናዳ የሆነ የፖለቲካ ተንታኝ በፍራቻ የተተበተቡና በእንዲህ አይነት ወቀሳ ውስጥ ያሉ ዜጎች በአደባባይ ይቅርታ ጠይቀው ወደስራ መግባታቸው እጅግ ሊታገዝ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል። (ዶ/ር ፍስሓ እሸቱ የሰጡትን ቃለምልልስ ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)



