የኢትዮጵያ ወታደሮች በባድሜ በኩል ድጋሚ ጥቃት ሰነዘሩ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ መጋቢት 9 ቀን 2004 ዓ.ም. March 17, 2012)፦ የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ ድንበሬን ጥሳ ለፈጸመችበት ጥቃት ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድባት ይገባል በማለት ለጸጥታው ምክር ቤት ክስ ባቀረበች በማግስቱ የኢትዮጵያ ወታደሮች ዛሬ አዲስ ጥቃት መሰንዘራቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ዛሬ መጋቢት 9 ቀን ጠዋት ሲሆን ያስከተለው ጉዳት ልክ ግን አልተብራራም። አንድ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደገለጹት ከሆነ የዛሬው የኢትዮጵያ ወታደሮች ጥቃት የተፈጸመው በሰሜናዊ ክፍል በባድሜ አቅራቢያ ሲሆን ወታደሮቹ ተልእኳቸውን በተሳካ ሁኔታ ፈጽመዋል ብለዋል።
ባለፈው ሀሙስ በኤርትራ ደቡባዊ ምስራቅ አቅጣጫ 16-18 ኪሎ ሜትር ዘልቄ ገብቼ በሶስት ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በማድረስ የኤርትራ ተላላኪዎችን ማሰልጠኛ፣ ማቀጃና መዘጋጃ ቦታዎችን አውድሜያለሁ ሲል የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ መግለጹ ሲታወስ ያሁኑ ጥቃት ግን በተለይ ማን ላይ ያነጣተጠረ እንደነበር ባለስልጣኑ አላብራሩም።
ከ2 ቀናት በፊት የተወሰደውን እርምጃ የኤርትራ መንግስት በጽኑ አውግዞ “ኢትዮጵያ ይህንን መሰል ድፍረት ልትፈጽምብኝ የቻለችው አሜሪካንን ድጋፍ በመመካቷ ነው።” ሲል መወንጀሉ ይታወሳል።
የተለያዩ የኤርትራ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ጦር ባለፈው ሀሙስ እርምጃ ለመውሰድ የወሰነው በሀገር ውስጥ በየአቅጣጫው በተነሳበት ውስጣዊ ተቃውሞ ምክንያት የህዝቡን ስሜት አቅጣጫ ለማስቀየር ነው ከማለታቸውም በላይ ያለፈውን ጦርነት ተከትሎ ለኤርትራ የተፈረደላትን ባድሜ ላለማስረከብ ማዘናጊያ አዲስ ምእራፍ ለመፍጠር ነው ሲሉም መኮነናቸው አይዘነጋም።
የዛሬውን አዲሱን ጥቃት በተመለከተ ለጋዜጠኞች የገለጹት በስም ያልተጠቀሱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ለወታደራዊ እርምጃው ዝርዝር ሁኔታ ከሰዓታት በሗላ መግለጫ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።



