ጥሪው ለህጋዊው ሲኖዶስ፣ ለገለልተኞችም ሆነ ለአባ ጳውሎሰ ተከታዮች ተላልፏል

የተገኙት የህጋዊው ሲኖዶስ አባቶች ብቻ ነበሩ

(የተቃውሞ ሰልፉን ቪድዮ ለመመልከት ይህንን  ይጫኑ )

Ethiopia Zare (ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2004 ዓ.ም. March 26, 2012)፦ ዋልድባ በመባል የሚታወቀውንና ለዘመናት  የመነኮሳት መመነኛ በመሆኑ ከታሪካዊዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ገዳማት በዋናነት ተጠቃሽ የሆነው ገዳም የስኳር ፋብሪካ ለመስራት በሚል ሰበብ የተያዘውን የእርሻ ቁፋሮ በመቃወም በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ።

 

ዛሬ ከጠዋቱ 9 ሰዓት ላይ የጀመረው ይሄው ሰላማአዊ ሰልፍ ‘ዋልድባን የሚያጠፋ ይጠፋል’ ‘ዋልድባ የአምላክ እንጂ የንግድ አይደለም’ የሚሉና የመነኮሳትን አጽም በቡልዶዘር መቆፈር አግባብ አለመሆኑን በሚገልጹ በርካታ ልዩ ልዩ መፈክሮች የታጀበ ሲሆን ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ምእመናንና የታሪክ መጥፋት ያሳሰባቸው ኢትዮጵያዊያን መገኘታቸውን ለማወቅ ችለናል።

 

ይህ በቤተክርስቲያኗ ላይ የሚፈጸም አስከፊ ድርጊት የሁላችንም ነው ባሉ የቤተ ክርስቲያኗ ወጣት ምእመናን የተጠራው ሰልፍ ተቀማጭነቱ በአሜሪካን ሀገር የሆነውና ህጋዊው ሲኖዶስ፣ ገለልተኛ ነን ለሚሉ ወገኖችና በአባ ጳውሎስ የሚተዳደሩ ቤተክርስቲያናት እንዲገኙ ጥሪ መተላለፉ የተዘገበ ሲሆን በስፍራው ጉዳዩ ያሳሰባቸው ምእመናን የተገኙ ሲሆን ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ግን የህጋዊው ሲኖዶስ አባቶች እና የቀድሞ የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ብቻ መገኘታቸውን ዘጋቢያችን ከዋሽንግተን ዲሲ አረጋግጧል።

 

በስፍራው አቡነ ፊሊጶስ እና በዋልድባ የመነኮሱት አባ ገብረማሪያም ለሰልፈኞቹ ምክር የለገሱ ሲሆን ከኤምባሲው በኩል ምንም አይነት ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ለማወቅ ተችሏል።

 

በተለየ አባቶች በንገግራቸው “መከራው በዛብን፤ 20 ዓመት አውርተንና ተሰልፈን ብቻ መመለስ የለብንም ርምጃ መውሰድ አለብን፤ ምን እስክንሆን ነው የምንጠብቀው” በማለት ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ በቁጭት ሲናገሩ ተደምጠዋል።

 

የመነኮሳት አጽም መቆፈሩንና ገዳሙ አደጋ ላይ መውደቁን በተለይ ይፋ ያደረጉት የዋልድባ ገዳም መነኩሴ የሆኑት አባት በስልክ ከሀገር ቤት በዋ ንግተን ዲሲ ሰልፍ ለወጣው ህዝብ ስለሁኔታው አስረድተዋል።

 

በዋልድባ ገዳም አካባቢ በተደረገው የመንገድ ስራ በርካታ የመነኮሳት አጽም ተቆፍሮ የወጣ ሲሆን የመንግስት አካላት 27ቱን አጽም ማግኘታቸውን ማመናቸው ተመልክቷል።

 

በተያያዘም ሰልፈኞቹ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ በማምራት ከሁለት ወራት የዘለቀ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

 

ያሳለፍነውን የገና በዓል ለማክበር በአንድ ቤት ውስጥ ተሰባስበው የተገኙ ክርስቲያኖች በሳዑዲ አረቢያ ፖሊሶች ተይዘው ስቃይ ሲደርስባቸው መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን በተለይ በሴቶቹ ኢትዮጵያዊያት ላይ ዘግናኝ ድርጊቶች ሲፈጸምባቸው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ