Ethiopia Zare  ማክሰኞ መጋቢት 19ቀን 2004 ዓ.ም. March 27, 2012)፦ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የእርሻ መሬቶችን ለባለ ሀብቶች በሊዝ የመሸጡን ሂደት አቋርጣለሁ ባለ በሳምንቱ የፈጠነ ሽያጭ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ይፋ አደረገ።

 

በተለይም በሱዳን አዋሳኝ በሆኑት በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልሎች አንድ ሄክታር መሬት በአመት በ1ዶላር ከ15 ሣንቲም ሂሳብ እየተቸበቸበ ነዋሪዎቹ ግን መላ ህይወታቸውን ከኖሩበት ቀዬ በግዳጅ ሲፈናቀሉ መቆየታቸው ከፍተኛ ውግዘት ካስከተለ በሗላ ነበር መንግስት ሂደቱን አቋርጨ እስካሁን ለባለሀብቶች የተሸጡት መሬቶች ምን ያህል እየተሰራባቸው እንደሆነ እገመግማለሁ ሲል ያስታወቀው።

 

ይሁንና ይህ መግለጫ በተሰጠ በሳምንቱ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልሎች ተጨማሪ 100ሺህ ሄክታር መሬት ለኢንቨስተሮች ለመስጠት መፍቀዱንና በመጭዎቹ ጊዜያት ባዶ መሬቱን ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ግንባታዎችን አሟልቶ ለመሸጥ መሰናዳቱን በግብርና  ሚኒስትር የእርሻ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ቢሮ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኢሳያስ ከበደ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ አረጋግጠዋል።

 

‘በአዲሱ እቅድ መሰረት መንግስት መሬቱን መንጥሮና የመስኖ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክና ንጹህ ውሃን የመሳሰሉ ነገሮችን አሟልቶ የመሬቱን ዋጋና ተጨማሪ ወጭዎቹን ጨምሮ ለባለ ሀብቶች ይሸጠዋል።’ ሲሉ አቶ ኢሳያስ ለብሉምበርግ ኒውስ አብራርተዋል።

 

ተቀማጭነቱ ለንደን የሆነው የውጭ ሀገራት ኢንስቲቲዩት እንደሚገልጸው በአለማችን ካሉት 5 ከፍተኛ የምግብ እርዳታ ተቀባዮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት 4 ዓመታት ብቻ ሳዊዲ ስታርን ጨምሮ ለተለያዩ ኢንቨስተሮች 400ሺህ ሄክታር መሬት በሊዝ ሸጣለች።

 

መንግስት በአጠቃላይ ለመሸጥ አቀዶ የያዘው 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሲሆን በጋንቤላ ከክልሉ 42% ያህሉን መሬት በሊዝ ለመሸጥ እቅድ የተያዘ ሲሆነ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ 1/5ኛው መሬት ለሊዝ ተዘጋጅቷል። ይህ ማለት ደግሞ ከ100ሺህ ሄክታር በላይ የተሸጠ ሲሆን 981 ሺህ ሄክታር ያህሉ ደግሞ በቅርቡ ለሽያጭ ይቀረባል።

 

የሽያጩ ዋጋ እንደሚያመለክተው ከሆነ ካራቶሪ ለተባለው የህንድ ኩባንያ ለአንድ ሄክታር 1፣15 ዶላር በአመት የተሸጠ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ ሲሰላ አንድ ሄክታር መሬት ወደ 20 ብር ገደማ በዓመት ተሽጧል ማለት ነው።

 

ሳውዲ ስታር የተባለው የሼህ ሙሀመድ አሊ አላሙዲ ካምፓኒ የሩዝ እርሻውን ለማስፋፋት ተጨማሪ 290ሺህ መሬት በጋምቤላ አካባቢ ለመግዛት እንደሚፈልግ በይፋ አስታውቋል።

 

“የመሬት ሽያጩን ሂደት ማስፋፋቱ መንግስት ‘የልማት እቅዴ’ በሚለው በዚሁ ፕሮግራሙ ምክንያት የደረሱትን የሰብአዊ መብት ረገጣዎች በተመለከተ ተጠያቂ የሚሆንበትን ጊዜ ያፋጥነዋል።” ሲሉ የኦክላንድ ኢኒስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።

 

“የዓለም አቀፍ ለጋሽ አገራትም ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጡትን እርዳታ እንዲያቆሙ እየተደረገ ያለውን ግፊት ይህ ውሳኔ ያፋጥነዋል።” ሲሉ ተሟጋቹ አክለው ገልጸዋል።    

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ