. አካለ ስንኩል ሳይቀር ተደብድበዋል

. ጭካኔው ከአልሸባብ የከፋ ነው ተባለ

(ልዩ ዘገባ - ኢትዮጵያ ዛሬ)

Ethiopia Zare (እሁድ መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም. April 1, 2012)፦ በድጋሚ ወደ ሱማሊያ የዘመተው የኢትዮጵያ ሰራዊት የሱማሊያ የሽግግር መንግስትን ከመደገፍ ሚሊሻዎች ጋር በመሆን ከአልሸባብ ባስለቀቃቸው የሀገሪቱ ከተሞች ውስጥ ሰፊ የመብት ረገጣ እየፈጸመ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣው መግለጫ ላይ አመለከተ።

 

በተለይም ከሁለት የሚሊሺያ ቡድኖች ጋር በመሆን ባለፈው ዲሴምበር 31 ቀን 2011 ዓ.ም ከአልሸባብ እጅ ነጥቆ በተቆጣጠራት በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው የሂራን ክልል ዋና ከተማ በሆነችው በበለተወይን እና ባለፈው ፌብሪዋሪ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በተቆጣጠራት በባይደዋ ከተማ ውስጥ እየተፈጸመ ያለው የመብት ረገጣ ከፍተኛ በመሆኑ ነዋሪው ህዝብ ከአልሸባብም በከፋ አገዛዝ ስር ወድቀናል በሚል እያማረረ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።

 

“የበለተወይንና የባይደዋ ነዋሪዎች ከአልሸባብ መባረር ጋር ለደህንነታቸው የሚሰጉበትና የሚረገጡበት ዘመን እንዳከተመ ቆጥረውት ነበር። ይሁንና በአልሸባብ እግር የተተኩት የኢትዮጵያ ጦርና ከጎኑ የቆሙት የሽግግር መንግስቱ ደጋፊ ሚሊሻዎች እየወሰዱ ያለው እርምጃ ያረጋገጠው ግን አንድ አፋኝና ጨቋኝ አገዛዝ ሲሄድ በሌላ አፋኝና ጨቋኝ አገዛዝ መተካቱን ነው።” ሲሉ ሌስሌ ሌፍኮ የተባሉ የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ገልጸዋል።

 

በስፋት ተይዟል የተባለውን የሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ የመግደል እርምጃ በአብዛኛው የሚፈጸመው ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ከተሰለፉት ሚሊሻዎች በተለይም በአንዱ ቡድን መሆኑ ቢጠቀስም የኢትዮጵያ ሰራዊትም በቀጥታ የመብት ረገጣው አካል ሆኖ መቀጠሉም ተመልክቷል።

 

ከተሞቹ በኢትዮጵያ ጦርና በሚሊሻዎቹ ቁጥጥር ስር ቢቆዩም እንኳን የአልሸባብ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ማድረሳቸውን የቀጠሉ ሲሆን በተለይም ባለፈው ጃንዋሪ 24 ቀን የኢትዮጵያ ጦር ዋና ካምፑ ባደረገው የመንግስት በነበረ ህንጻ ላይ የአልሸባብ አጥፍቶ ጠፊ በቦምብ የተሞላ መኪና በሩ ላይ  በማፈንዳት ጉዳት አድርሶ እንደነበር በወቅቱ በኢት ጵያ ዛሬ መዘገቡ ይታወሳል።

 

ይህንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ ጦርና አጋሮቹ ሚሊሻዎች በርካታ ሰዎችን ያሰሩ ሲሆን ከእነዚህ ከየቤታቸው እየተጎተቱ ከታሰሩ ሰዎች አንዱ የሆነው አብድረህማን መሀመድ ኑር አብዱል የተባለ መምህር ድብደባ ከተፈጸመበት በኋላ ተገድሎ ወንዝ ውስጥ መጣሉን የአይን ምስክሮች ለሰበአዊ መብት ተሟጋቹ አረጋግጠዋል።

 

ህገ ወጥ እስርን በተመለከተም የተባበሩት መንግስታት ታዛቢዎችን ጨምሮ የተለያዩ ታማኝ ምንጮች ያመላከቱት ጉዳይ ሲሆን የሂዩማን ራይትስ ዎች ካነጋገራቸው ምስክሮች መሀል አምስት ሰዎች በኢትዮጵያ ወታደሮች ስለደረሰባቸው እንግልት አስረድተዋል። በተለይም ሶስቱ እስረኞች በኢትዮጵያ ወታደሮች ክፉኛ መደብደባቸውን መስክረዋል።

 

በበለተወይን አንድ የሚሊሻ ቡድን በቤት ለቤት አሰሳው የያዘውን አንድ ሰው ለኢትዮጵያ ወታደሮች አሳልፎ የሰጠ ሲሆን  ኢትዮጵያዊያኑ ዋና መቀመጫቸው አድርገው እየተጠቀሙበት ባለው በሂራን ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ ውስጥ ለበርካታ ቀናት ከዛፍ ጋር አስረው ድብደባ ሲፈጽሙበት መቆየታቸውንና በእስር ቆይታውም ምግብ እንዳይቀምስ መከልከላቸውን ታማኝ ምንጮቹን ጠቅሶ ሂዩማን ራይትስ ዎች ይፋ አድርጓል።

 

በባይደዋም አልሸባብ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች ተከትሎ የጅምላ እስር የሚካሄድ ሲሆን በተለይም ወጣት ወንዶችና ታዳጊዎች ይህንን የመሰለው አሰሳ ኢላማ በመሆናቸው አካባቢውን ለቀው ለመሸሽ በገደዳቸውም ታውቋል።

 

ለዚህ እንደ ጥሩ አስረጅ የተጠቀሰ ሰው ማርች 2 ቀን ባይደዋ ካለ እንድ የፖሊስ ጣቢያ ውጭ ፍንዳታ ከተሰማ በኋላ የኢትዮጵያ ወታደሮችና አጋሮቹ ሚሊሻዎች 8 ታዳጊ ወጣቶችን ጨምሮ 42 ሰዎችን ማሰራቸውን ነበር። በወቅቱ በስፍራው የነበሩት የቀድሞው የትምህርት ሚኒስተር እና አሁን የደቡብ ሶማሊያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር መሀመድ አሊ አህመድ በአካለ ስንኩልነታቸው ምክንያት መሸሽ አልቻሉም። እኚህን ሰው የያዟቸው 5 የኢትዮጵያ ወታደሮች ድብደባ የፈጸሙባቸው ሲሆን በኤ.ኬ-47 ጠመንጃዎቻቸው ሰደፍም ጭንቅላታቸው፣ አፋቸውና ጆሯቸው ላይ ደብድበው ደም በደም እንዳደረጓቸው ተመስክሯል።

 

የኢትዮጵያ ጦር በቀዳሚው የሶማሊያ ዘመቻው ወቅት የፈጸማቸው መሰል የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ህዝቡን በማማረሩ አልሸባብን ለማጠናከር እንደረዳና የኢትዮጵያ ጦርም ባልተሳካ ቆይታ እንዲመለስ እንዳስገደደው የሚታወስ ነው።

 

በተያያዘ ዜናም የአልሸባብ ታጣቂዎች በማናቸውም መልኩ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ግንኙነት በመሰረተ ነዋሪ ላይ እርምጃ እንወስዳለን ባሉት መሰረት በርካታ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ሲዘገብ ከእነዚህም መሀል አንድ የንግድ ሰው የሆነ ኢትዮጵያዊ ባለፈው ፌብሪዋሪ 25 ቀን ምሽት ላይ በታጣቂዎች ጥይት መሞቱ ታውቋል።

 

ይህ የባይደዋ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በአስተርጓሚነት ከማገዙም በተጨማሪ የንግድ ቤቱን (ላውንደሪ) ቀድሞ በመክፈቱ ነው የተገደለው ተብሏል። ግለሰቡ አንድ ታጣቂ በከፈተው ተኩስ ጭንቅላቱ ላይ በ3 ጥይት ተደብድቦ መሞቱ ሲገለጽ ሀላፊነቱንም አልሸባብ ወስዷል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ