የኢትዮጵያና የኤርትራ ውጥረት ተባብሷል
አቶ መለስ ለውስጥ ችግራቸው ሁሉ ኤርትራን ተጠያቂ እያደረጉ ነው
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዚያ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. April 25, 2012)፦ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ባለፈው ማክሰኞ በተወካዮች ምክር ቤት ፪፭ኛ ጉባኤ ላይ " በሰሜን ምእራብ ኢትዮጵያያ በትግራይ ክልል ውስጥ በወርቅ ማውጣት ስራ ላይ የተሰማሩ አንድ መቶ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶትን የኤርትራ መንግስት አፍኖ ወስዷቸዋል" ሲሉ መክሰሳተውን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት " ይህ የተለመደ የፈጠራ ውንጀላ ነው።" ሲል አስተባብሏል።
አቶ መለስ በም/ቤቱ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ በሰጡት ገለጻ ላይ የኤርትራ መንግስት ወጣቶቹን አፍኖ የወሰደው በቅርቡ ቢሆንም ባለፈው ጃንዋሪ ፩፯ ቀን በአገሪቱ ሰሜን ምስራቅ በኩል ለተገደሉት 5 ቱሪስቶትና ለታፈኑት 2 ጀርመናዊያንም ተጠያቂው እራሱ በመሆኑ "ኢትዮጵያ በአጸፋው በሁለቱም አቅጣጫዎች ተመጣጣኝ እርምጃ ወስዳለች" ብለዋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ በሰሜን ምስራቅ በኩል ተወሰደ የሚሉት የአጸፋ እርምጃ ባለፈው ማርች ፩፭ ቀን የኢትዮጵያ ወታደሮች ከኤርትራ ድንበር ፩፰ ኪሎ ሜትር ያህል ዘልቀን ገብተን አማጺያን የሚጠቀሙባቸውን 3 ወታደራዊ ቤዞች አጥቅተናል በሚል የገለጹት መሆኑ ነው። ይሁንና በትግራይ ክልል ታፍነው ተወስደውብናል ያሏቸውን ዜጎት በተመለከተ መች እንደተወሰዱም ሆነ የአጸፋ እርምጃቸውን ምንነት አስመልክቶ ጠ/ሚ/ሩ የገለጹት ነገር የለም።
የመንግስት የኮሚኒኬሽን ሚ/ር የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን ግን ለብሉምበርግ ኒውስ በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ "በትግራይ የተፈጸመው አይነት ጠለፋ በየጊዜው የሚካሄድ ነው" ብለዋል።
መንግስት ለጠለፋው በአጸፋ ወስጄያለሁ ስላለው እርምዳ የተሰጠ ማብራሪያ ባይኖርም ኤርትራ ውስጥ ያሉ ቤዞችን አጠቃሁ ማለቱን ተከትሎ "በሰሜን ምእራብ አቅጣጫም በባድሜ አካባቢ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደናል።" ሲሉ አንድ በስም ያልተጠቀሱ ባልስልጣን በወቅቱ ለሮይተርስ ገልጸው እንደነበር በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ መዘገባችን አይዘነጋም። ይሁንና ሮይተርስ ይህንኑ በዘገበ በማግስቱ አንድ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር ሹመኛ ሪፖርቱን ማስተባበላቸው ሲታወስ አሁን ከወር በኋላ ጠ/ሚ/ሩ በተባለው አካባቢ እርምጃ ወስደናል ማለታቸው ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።
የኤርትራ መንግስት ሁለቱንም ክሶች ከማስተባበሉም በላይ በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት ግርማ አስመሮም "ይህ ሁሉን ችግር በኤርትራ ላይ የመላከኩ የተለመደው የኢትዮጵያ መንግስት መሰረት የለሽ ውንጀላ ነው" ሲሉ ኮንነዋል።
"አሁንም አሁንም ውሸትን በመደጋገም እውነት ማስመሰል ይቻላል ብለው ያስባሉ። ኤርትራ ግን ለራሷ ጥቅም ስትል የተረጋጋች ፤ አንድነቷን የጠበቀችና የምታድግ ኢትዮጵያን ነው የምትፈልገው። ሱዳንንም እንደዚሁ። እነዚህ አገራት ትልልቅ ገበያዎች ናቸውና።" ሲሉ አምባሳደር ግርማ አስመሮም መግለጻተውን ብሉምበርግ ኒውስ ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያ መሳሪያ ያነሱ ተቃዋሚዎችዋን ሁሉ የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች እያለች መወንጀሉን ስራዬ ብላ የያዘች ቢሆንም የአገሪቱን ሁኔታ የሚከታተለው የአሜሪካ መንግስት ግን የክሷን እውነታነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ጥርጣሬ አለው። ኤፕሪል ፪፬ ቀን ፪፻፯ ዓ.ም. ከአዲስ አበባው የአሜሪካ ኤምባሲ የተላለፈና በዊኪሊክስ አማካኝነት ለህዝብ ይፋ የወጣ አንድ ኬብል እንዳጋለጠው ከሆነ በተለይም የኦብነግ እና የኦነግ እንቅስቃሴ እያየለ መምጣቱን ገልጾ የመንግስት ምላሽ ግን ጠንካራና አንዳንዴም በፍጹም ጭካኔ የተሞላ መሆኑን ይኮንኗል።
"ልማትና እርዳታን በክልሎች በማድረስ ተገቢ ምላሽ ነው መስጠት ያለባችሁ የሚለው ምክራችን ሰሚ አጥቷል። በዚህ መልኩ መንግስት የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ምክር አልሰማ ብሎ በዘረጋው የከሰረ ፖሊሲ ምክንያት በሁለቱ ክልሎች (ኡጋዴን እና በኦሮሚያ) ውጥረቱ ከተባባሰ የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን በኤርትራ ላይ የሚያሳብብበት ሁኔታ ከፍ እያለ የመሄዱ እድል ሰፊ ነው" ሲል ኤምባሲው ስጋቱን ጠቁሞ ነበር።



