ጥርጣሬው እስካሁን አልቆመም

Ethiopia Zare (እሁድ ሚያዚያ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. April 29, 2012)፦ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ ከህዝብ ዕይታ ተሰውረው መቆየታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ታመዋል በሚል በኤርትራዊያን ዘንድ በስፋት መነጋገሪያ ሆነው ቢቆዩም በትላንትናው ዕለት በኤርትራ ቴሌቪዚን ቀርበው "ያስወሩብኝ ጠላቶቼ ናቸው" ሲሉ አስተባብለዋል።

 

 

የመንግስታቸው ተቃዋሚ የሆኑ ድረ ገጾች ፕሬዘዳንቱ በጉበት በሽታ በጽኑ መታመማቸውን በስፋት እየዘገቡት ሲቆዩ አንዳንዶቹም በህይወት መኖራቸውን ሳይቀር ጥያቄ ወስጥ ጥለውት ነበር። በተለይም 'አሴና" የተሰኘው ድረ ገጽ ምንጮችን ጠቅሶ የኢሳያስን መታመም ዘግቦ ኤርትራ ባሁኑ ወቅት በጥድፍያ በተቋቋመ 'የአመራር ጉባዔ' ስር እየተዳደረች ስለመሆኗም አመልክቷል።

 

ይህን 'የበላይ ጉባዔ' ጄ/ል ስብሀት ኤፍሬም በበላይነት እንደሚያዙትና ብ/ጄ/ል አብርሀ ካሳ ምክትላቸው መደረጋቸው በድረ ገጹ ዘገባ የተመለከተ ሲሆን ሜ/ጄ/ል ኡመር ጠዊል እና ሜ/ጄ/ል ፊሊጶስ ወ/ዮሀንስም በአዲሱ የበላይ ኮሚቴ ውስጥ መኖራቸው ነበር የተመለከተው።

 

አቶ ኢሳያስ ኤርትራ ነጻነቷን ካወጀችበት ቀን ጀምሮ አገሪቷን በብቸኝነት ሲመሩ ከመቆየታቸውም በላይ ችግር ቢደርስባቸው ኃላፊነቱን ተረክቦ አመራር የሚሰጥ ሰው በምክትልነት አላስቀመጡም።

 

ይሄንኑ በተመለከተ ‘ኢሳያስ ከሞቱ ማን ሊተካቸው ይችላል በሚል ጥያቄ ዙሪያ ኤርትራዊያን በየድረ ገጾቹ ሲወያዩ የከረሙ ሲሆን አንዳንዶቹም አምባገነኑ መሪ ለስልጣናቸው ምክትልም ሆነ ስርአት ያለው ሽግግር ሊካሄድ የሚቻልበትን መሰረት ሳይጥሉ መቅረታቸውን አጥብቀው ሲኮንኑ ሰንብተዋል።

 

“በአለም ላይ ምክትል መሪ የሌላት ሀገር ኤርትራ ብቻ ነች። እንደ አልቃይዳ ያሉ ሽብርተኛ ድርጅቶች እንኳን ምክትል መሪ አላቸው።” ሲል አንድ ኤርትራዊ ቁጭቱን የጻፈ ሲሆን ሌሎች መሰሎቹም ስርአት ያለው ሽግግር ማስፈጸም የሚችል ህገ መንግስታዊ መዋቅር ያለመኖሩንና ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ ዲሞክራሲያዊ ተቃማት ያለመገንባታቸው ሊያስከትል በሚችለው ችግር ዙሪያ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ሰንብተዋል።

 

የኤርትራ መንግስት ግን የፕሬዝዳንቱን ጤንነት በተመለከተ የተዛመተውን ወሬ የሲ.አይ፣ኤ ዘመቻና የአገሪቷን መረጋጋት የማይፈልጉ ተቃዋሚዎች ስራ ነው በሚል ከማስተባበሉም በላይ በኤርትራ ቴሌቪዥን አማካኛነት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ የሚያሳይ ፊልም አሳይቷል።

 

ይሁንና ይህ በኤርትራ ቲቪ ተላልፎ የነበረው ምስል ከፋይል የወጣ የቆየ ቅጅ ነው ሲሉ አንዳንድ ታዛቢዎች ተችተውት የነበረ ሲሆን ኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት አሊ አብዶም ከጥቂት ቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ “ኢሳያስ በመልካም ጤንነት ላይ ነው ያለው። እኔ በየቀኑ ነው የማገኘው። ይህንን ታሟል የሚል ወሬ ለማስተባበል ሲባል ግን በቴሌቭዥን የሚቀርብበት ምክንያት የለም ማለታቸው ይታወሳል።

 

ያም ሆኖ ግን የተዛመተው ወሬ ደጋፊዎቻቸውን ጭንቀት ውስጥ ከከተተና ተቃዋሚዎቻቸውም ስለሚከተለው ሁኔታ በስፋት የሚነጋገሩበትን እድል ከሰጠ በኋላ ግን ፕሬዝዳንቱ በሀገራቸው ቴሌቭዥን ቀርበው ጤንነታቸውን ለማረጋገጥ ተገደዋል።

 

አቶ ኢሳያስ “እኔ ጤነኛ ነኝ። ይልቅስ ታሟል ያሉኝ ሰዎች ናቸው በሽተኞቹ።” በማለት ነበር የተነዛውን ወሬ ለማጣጣል የሞከሩት።

 

የኢሳያስን በጠና መታመም ሲያጣቅሱ ከኖሩ ተቃዋሚዎቻቸው አንዳንዱ “ከከፍተኛ ህክምና በኋላ በማገገሙ ነው ለእይታ የበቃው እንጅ በእርግጥ ታሟል።” የሚል እምነታቸውን ያስነበቡ ሲሆን አንድ የኤርትራዊ ብሎግ ደግሞ በቲቪ የቀረቡት ኢሳያስ ሳይሆኑ በአስመራ የሚገኘው አምሳያቸው ነው እስከማለት ደርሷል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ