በሙስሊሞች ጉዳይ ውጥረቱ እንዳየለ ነው
የፌደራል ጉዳዮች ሚ/ር አዲስ መግለጫ አወጣ
Ethiopia Zare (አርብ ሚያዚያ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. May 4, 2012)፦ "መንግስት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ውክልና የሌለውን የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔን በመጠቀም 'አህባሽ' የተባለውን አስተምህሮ በግድጅ ሊጭንብን እየሞከረ ነው " በሚል በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንደቀጠለ ሲሆን መንግስት ዓላማውን ለማስፈጸም የሀይል እርምጃን መምረጡም ውጥረቱን ይበልጥ እያባባሰው መጥቷል።
በቅርቡ በአርሲ ዞን በምትገኘው በአሳሳ ከተማ ውስጥ ሰዑድ አማን የተባሉትን ኢማም ለማሰር ወደ ሚያስተምሩበት መስጊድ ያመሩት የመንግስት ሀይሎች ህጋዊውን የፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ እንዲያሳዩ ቢጠየቁም ለማቅረብ ባለመቻላቸው ምክንያት በተፈጠረ ተቃውሞ ንጹሀን ዜጎች መገደላቸው ይፋ ሆኗል።
መንግስት ኢማሙን ለማሰር የፈለገው 'ሽብርተኝነትን ይሰብካሉ' በሚል ሰበብ ቢሆንም በመስጊዱ የነበሩት አማኞች ግን ያለህጋዊ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ኢማማችንን አሳልፈን አንሰጥም በማለት በመቃወማቸው የመንግስት ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው ቢያንስ 7 ሰዎች ሲገድሉ በርካቶችን ማቁሰላቸው ነው የተመሰከረው። ይህንኑ ሁነት በተመለከተ የዓይን ምስክርነታቸውን ለጋዜጠኞች ከሰጡ በርካታ ሰዎች መሀል አንዱ የሆኑት የአካባቢው የሞስሊሞች ማህበረሰብ መሪ ሀጂ አብድረሀማን ሳዲቅ 'ኦን እስላም' ለተባለ ድረ ገጽ በሰጡት ምስክርነት ላይ "ኢማም ሰዑድን ለማሰር የመንግስት ሀይሎች መስጊዱን መክበባቸው ያስቆጣቸው አማኞች አሳልፈን አንሰጥም በማለታቸው ነበር ተኩሱ የተከፈተው" ብለዋል።
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ሽመልስ ከማል ግን "የመንግስት ሀይሎች ለመተኮስ የተገደዱት ኢማሙ ከታሰሩ በኋላ ተከታዮቻቸው ከፖሊስ ጣቢያው በሀይል ሊያስፈቷቸው በመሞከራቸው ነው።" ሲሉ ለብሉምበርግ ኒውስ ከመግለጻቸውም በላይ የሟቾቹንም ቁጥር ወደ 4 ዝቅ አድርገውታል። ይሁንና የተለያዩ የአካባቢ ምንጮችን ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች ግን ቢያንስ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ሲያሳውቁ 180 የሚሆኑ ሙስሊሞች ደግሞ ለእስር ተዳርገውል ብለዋል።
ሽመልስ ከማል የእስረኞቹን ቁጥር በተመለከተ 24 ብቻ ናቸው ሲሉ የኦሮሚያ ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ኮማንደር አበበ ለገሰ ደግሞ "ፍርድ ቤቶቻችን በሳምንት ሰባት ቀናት ለ24 ሰዓት ስለሚሰሩ እስረኞቹንም በዕለተ ቅዳሜ ፍ/ቤት አቅርበናቸዋል" የሚል አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል። የአካባቢው ተወላጆች ይህን የኮማንደሩን አስገራሚ ቃል ያጣጣሉት ሲሆን የክልሉ ሹማምንትም ለተፈጸመው ግድያ ሀላፊ መሆናቸውን በሚያመላክት መልኩ ለሰለባዎቹ ቤተሰቦች "በጸጥታ የምታልፉት ከሆነ የደም ካሳ እንከፍላችኋለን" ማለታቸው ተዘግቧል።
መንግስት የተለየ ሀሳብ የነበራቸውን የመጅሊስ አባላት አባርሮ ራሱ በሾማቸው ሰዎች እየተጠቀመ ልዩ ድጋፍ የሚያደርግለትን የአህባሽ አስተምህሮ በማይቀበሉ ሙስሊሞች ላይ ከማስፈራራት አልፎ ተግባራዊ ጫና እያደረገ ነው በሚል በሰፊው እየተወነጀለ ነው። ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊም ባለፈው ኤፕሪል 17 ቀን በፓርላማ ባቀረቡት ንግግራቸው ላይ "ጥቂት ሳላፊስት አክራሪዎችን የያዘ የአልቃይዳ ሴል አርሲ ውስጥ ተይዟል።" በሚል አድበስብሰው ማለፋቸው 'የምንላችሁን ካልተከተላችሁ በሽብርተኝነት እንፈርጃችኋለን' የሚል ማስጠንቀቂያ ለመስጠት የተጠቀሙበት ስልት ነው የሚሉ አስተያየቶች ሲደመጡ ሰንብተዋል።
በተመሳሳይ መልኩም በትላንትናው ዕለት በፌደራል ጉዳዮች አማካኝነት የወጣው አዲስ መግለጫ በመብት ጥያቄዎች ዙሪያ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ህገመንግስትዊ ስርአቱን ለመናድ የሚደረጉ አንቅስቃሴዎች በማስመሰል "መንግስት ትዕግስቱ አልቋል" በሚል የሀይል እርምጃ ለመውሰድ መሰናዳቱን አመላክቷል።
የሙስሊሞቹን ጥያቄ "በሀይማኖት ሽፋን ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው" በሚል የሚኮንነው ይህ መግለጫ የዘመኑን ሶሻል ሚዲያዎች በመጠቀምና በሽብርተኝነት ከፈረጅናቸው ሀይሎች ጋር በማበር ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ከማለቱም በላይ ከዚህ በኋላ መንግስት በዝምታ እንደማይመለከተው በመጠቆም እስከማስፈራራት ዘልቋል።



