በብራስልስ የአውሮፓ ኮሚሽን የተቃውሞ ሰልፍ ተጠራ
-
የኢትዮጵያ መንግሥት በዜጎቹ ላይ እያደረሰ ያለውን የመብት ረገጣ እና እስራት በአስቸኳይ ያቁም!!
-
በኃይማኖቶች ላይ ጣልቃ መግባቱን እና ዜጎችን ማፈናቀሉን ያቁም!!
Ethiopia Zare (ሐሙስ ግንቦት 2 ቀን 2004 ዓ.ም. May 10, 2012)፦”መብታችን ይከበር!” በሚል በኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተጀመረውን እንቅስቃሴ በመደገፍና ”የኢህአዴግ መንግሥት በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን የመብት ረገጣ፣ እስራት፣ በኃይማኖቶች ላይ ጣልቃ መግባቱንና ዜጎችን ማፈናቀሉን ያቁም!” በሚል መሪ መፈክር የፊታችን ሜይ 16 ቀን 2012 በብራስልስ የአውሮፓ ኮሚሽን ሕንፃ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ተጠራ።
የተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ በላከው መግለጫ፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት አገሪቱ የምትገኝበት ሁኔታ የዲሞክራሲ እምርታ ይቅርና ጭላንጭሉንም አይታለች ለማለት የሚያስደፍር አይደለም ሲል ገልጿል።
መግለጫው አክሎም፤ ”ከፓርቲ አንባገነንነት አልፎ የግለሰቦች ወይም የጥቂት ቡድኖች አንባገነናዊነት እውን የሆነባት አገር ከሆነች ውሎ አድሯል። መንግሥት ራሱ ያጸደቀውን ሕገ-መንግሥት ሳይቀር በመጣስ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ላይ እያደረገ ያለውን ግፍ አጠናክሮ ቀጥሎበታል። በዚያው መጠን የህዝብ እሮሮ፣ ስቃይና መከራ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መጥቷል። በኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየመነመነ መጥቶ እርቃኑን የቀረው ሥርዓት አሁንም ለህዝቦች ፍላጎት ጆሮ በመስጠትና የአገሪቱን አጠቃላይ ደህንነት ከግምት በማስገባት ድርጊቱን ከማሻሻል ይልቅ አፈናውን አጠናክሮ ቀጥሏል።” በማለት በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ ይገልጻል።
በዚህም ምክንያት ገዥው ፓርቲ የሥልጣኔ ተቀናቃኝ ናቸው ያላቸውን ዜጎች በእስር ቤቶቹ በማጎር እያሰቃያቸው እንዳለ፤ የግል ሚዲያዎችን እያዳከመና ጋዜጦችን ከሕትመት ውጭ በማድረግ ጋዜጠኞችን ለእስርና ለስደት እየዳረጋቸው እንደሆነ፤ የህዝብ መገናኛ ብዙኀንን ለሥርዓት ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ብቻ እያደረጋቸው መሆኑን መግለጫው ያትታል።
ይኸው መግለጫ አክሎ፤ ዜጎች ተወልደው ካደጉበትና ከሚኖሩበት ቀዬ መሬታቸው ለውጭ ዜጎችና ለሥርዓቱ ታማኝ አገልጋዮች እየተቸበቸበ መገኘቱን ገልጿል። ለምሳሌም በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ኢትዮጵያዊያን ይህ ነው ለማይባል ስቃይና እንግልት መዳረጋቸውን ጠቅሷል።
ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ የኖረውን ህዝባችንን በእምነቶቹ ጣልቃ በመግባት እርስ በርሱ እንዲተላለቅ የሚያደርጉ ስራዎች ከምንግዜውም በላይ ተጠናክረው ቀጥለዋል ያለው መግለጫ፤ ”በሙስሊሙ ህብረተሰብ እምነት ጣልቃ በመግባትና “አህባሽ” የተባለ የአምልኮ አስተሳስብ በህዝቡ ላይ በሀይል ለመጫን እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ይህን የተቃወሙ ሙስሊሞች ለእስራት ብቻ ሳይሆን በአገዛዝ ሥርዓቱ ታጣቂዎች በግፍ ደማቸው እየፈሰሰ ይገኛል” ሲል ገልጿል።
መግለጫው የአገርና የእምነት ቅርሶች ህልውናቸው እንዲያከስም እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ፤ በታሪካዊነቱና በጥንታዊነቱ ታዋቂ የሆነው የዋልድባ ገዳም የዚህ አገርን እና ህዝብን በማጥፋት ሥራ ላይ የተሰማራ መንግሥት ሰለባ ሆኗል ሲል ድርጊቱን ኮንኗል።
ገዥው መንግሥት ”ፀረ-ሽብርተኝነት” ብሎ በሰየመው ሕግ ዜጎችን እያስፈራራና እያሸማቀቀ እንደሆነ፣ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን እንደሽብርተኛ በመቁጠር በመወንጀል፣ በመክሰስ፣ ለእስራታ በመዳረግ፣ ገሚሶቹንም ከአስር ዓመት በላይ እስራት ፈርዶባቸው በእስር ላይ መገኘታቸውን መግለጫው አትቷል።
መግለጫው በሀገሪቱና በህዝቧ ላይ የኢህአዴግ መንግሥት እያደረሰ ያለውን በደሎች ሰፋ አድርጎ በማተት፤ ”ይህን እያየና እየሰማ አርፎ የሚቀመጥ ህሊና ሊኖረን አይችልም” ሲል ይገልጻል። በመሆኑም በኢህአዴግ መሪነት በአገራችን እና በህዝባችን ላይ እየተደረገ ያለውን የመብት ጥሰት፣ አገርን እና ህዝብን የማጥፋት ዘመቻው ሊያበቃ ይገባዋል። ግፉንም ሰላም ወዳድ ለሆነው የአለም ህዝብና መንግሥታት ማሳወቅ ይገባናል። በዚህም መሰረት የአገዛዝ ሥርዓቱ መልካም እየሰራ እየመሰላቸው በገንዘብም ሆነ በዲፕሎማሲ ድጋፍ ለሚያደርጉለት መንግሥታት አገሪቱ የምትገኝበትን አሳሳቢ ሁኔታ ለማስረዳት ሜይ 16 ቀን 2012 ከቀኑ 13፡00 ሰዓት ጀምሮ በብራስልስ ቤልጀም በሚገኘው የአውሮፓ ኮሚሽን ህንፃ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ መዘጋጀቱን ገልጿል።
መግለጫው በመጨረሻም፤ ሰልፉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሥርዓቱ ካዘጋጀለት የኃይማኖት፣ የጉሣና የዘር መከፋፈያ ወጥመድ ውስጥ ሳይገባ በአንድነት በመነሳት አገሩንና ራሱን እንዲታደግ ጥሪ የሚቀርብበት፤ ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህና ለሕግ የበላይነት የሚደረገውን ትግል በመደገፍም አጋርነታችንን የምንገልጽበት ይሆናል ብሏል። በሁሉም ቦታና በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በሁሉም የእምነት ተቋማትና ምዕመናን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ ድርጊትና ጣልቃገብነት እንዲያቆም ድምጻችንን የምናሰማበትም ነው በማለት አክሎ ገልጿል።
በዚሁ ሰልፍ ላይ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። (ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)



