Ethiopia Zare(ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. May 12, 2012)፦ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ የአፍሪካ መሪዎች ሙስና ውስጥ የሚዘፈቁት በወጉ የተደራጁ የውጪ ኩባንያዎች የሚያደርሱትን ጫና ለመቋቋም ስለሚያዳግታቸው መሆኑን አመላከቱ። አቶ መለስ ይህን እምነታቸውን የገለጹት በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ለመምከር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ትላንት (ሐሙስ ግንቦት 2 ቀን) ከአንዲት የፎረሙ ተካፋይ ከሆነች ደቡብ አፍሪካዊት ለቀረበ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው።


ጎባኖ ማድናማራሶ የተባለችው ደቡብ አፍሪካዊት ባቀረበችው ጥያቄ በወጣትነታቸው በጎ አሳቢና ባለራዕይ የነበሩትን ጨምሮ የአፍሪካ መሪዎች ስልጣን ከጨበጡ በኋላ በንቅዘትና ሙስና የሚዘፈቁ መሆናቸውን አጣቅሳ 'የችግሩ ምንጭና መፍትሄው ምንድነው?' በሚል ነበር የሞገተችው።


ከፎረሙ አወያዮች አንዱ የሆኑት ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ባልተለመደ ሁኔታ የችግሩን መኖር አምነው "መሪዎች ወደ ብሄራዊ ቤተ መንግስት ሲገቡ ራዕይ ካለው መሪነት አንዳንዴ ወደ ተራ ሌብነት ሳይቀር የሚለውጣቸው ምንድን ነው?-"የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በአህጉሪቷ ካለው የዝርፊያ መጠንና ለዝርፊያውም መሪዎቹ ካላቸው ሚና መነሳቱን መርጠዋል።


እነደ ጠ/ሚ/ሩ ከሆነ አብዛኛው ምዝበራ የሚፈጸመው በወጉ የተደራጁ ኩባንያዎች በሚያቀርቧቸው የተለያዩ አይነት ድለላዎች ሳቢያ ነው። የአፍሪካ መሪዎች የተለያዩ የስራ ዕድሎችን የሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶች ወደ አገሮቻቸው እንዲመጡ እንደሚፈልጉ ያመላከቱት አቶ መለስ ችግሩ ግን አህጉሯ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ያላት ዝና መጥፎ በመሆኑ ኢነቨስተሮቹም በዚሁ ያላግባብ አስፈሪ መስላ በምትታየው አህጉር ውስጥ ደፍሮ ሀብት ለማፍሰስ የተለዩ አጓጊ ጥቅሞች ያስፈልጉናል በሚል የሚስገድዱ መሆናቸውን በምክንያትነት አቅርበዋል።


"እነዚህ ካምፓኒዎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ እንፈልጋለን። ይሁንና ያለውን ሪስክ አጋንነው የሚያስቡ ከሆነ የሚያገኙት ጥቅምም በዚያው ልክ ከፍ ያለ መሆን  ይኖርበታል። ስለዚህ በጣም የተለየ ጥቅም እንዲመቻችላቸው ካላደረግን በቀር እንዲመጡ ማድረጉ አስቸጋሪ ነው።" ያሉት አቶ መለስ ኢንቨስትመንቱን እስከፈለጉ ድረስ የኩባንያዎቹን ጥያቄዎች ከመቀበል ውጪ ያሏቸው መደራደሪያ ካርዶች ውስን መሆናቸውን ጠቁመዋል።


"አንዳንዴ (ለኢንቨስተሮቹ) ሁኔታዎችን የምናመቻችላቸው ሳይከፈለን ነው። ሌላ ጊዜ ደግሞ 'የቤተሰብህ ማሳ ሲዘረፍ ለምን አብረህ አትዘርፍም?' እንላለን" የሚል ግልጽ ገለጻ የተጠቀሙት አቶ መለስ ይህን ሁለተኛውን አይነት ሙስና ከሁሉም የከፋው ነው ብለውታል።


አቶ መለስ የአፍሪካ መሪዎች በሙስና መዘፈቃቸውን በተለይም ከውጪ ኢንቨስተሮች ጋር የሚደረጉ ዓይን ያወጡ ግብይቶችን በተመለከተ በአደባባይ ማመናቸው ብዙዎችን ያስገረመ ሲሆን በተለይም ከ100ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ እያፈናቀሉ የአገሪቷን ለም መሬቶች ከነጻ ባልተሻለ ዋጋ ለኢንቨስተሮች እየቸበቸቡ ባለበት በዚህ ወቅት ሁኔታውን መካድ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ቢደርሱ ይሆናል የሚል ግምት ያሳደሩ አሉ።


በተለይም በጋምቤላና በቤንሻንጉል ንጹሀን የአካባቢው ነዋሪዎች በመንግስት ታጣቂዎች አስገዳጅነት እየተፈናቀሉ ለም መሬቶቻቸው ግን ለባለሀብቶች ሲቸበቸቡ መቆየታቸው ሲታወስ ይህ ሁኔታም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተመለከተው። በዚህ የመቶ አመት የሊዝ ችብቸባ ባለሀብቶች ለአንድ ሄክታር መሬት ሀያ የኢትዮጵያ ብር ብቻ እንዲከፍሉ መደረጉና ይህም በጊዜው የአገሪቱ ገበያ ከግማሽ ሊትር ዘይት በላይ የመግዛት አቅም የሌለው መሆኑ መዘገቡ ይታወሳል።


አቶ መለስ በፎረሙ ላይ ያሰሙትን ገለጻ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አንድ የፖለቲካ ታዛቢ ". . .ለምሳሌ በአገሪቱ በእርሻም ሆነ በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ የቻይናና የህንድ ድርጅቶችን ብንመለከት አብዛኛውን ሰራተኞቻቸውን ከአገራቸው ነው የሚያስመጡት። ስለዚህ የራሳቸውን የአቶ መለስን ትንታኔ ብንከተል እንኳን የእኛ አገሩ ሙስና ለአገሬው የስራ ዕድል ለመፍጠር ሳይሆን 'የቤተሰብህ ማሳ ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ' ከሚለው ብሂላቸው ጋር ነው የሚስማማው" ብለውናል።


ባሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ አቶ መለስን ጨምሮ የናይጄሪያ ፤ የናሚቢያ ፤ የጋቦንና የአንጎላ መሪዎች አወያዮች ሲሆኑ የናይጄሪያው ፕ/ት ጉድላክ ጆናታን የአፍሪካ መሪዎች የህዝቡን ፍላጎት ገሸሽ አድርገው የስልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም የአገራቸውን ህገ መንግስት እስከመቀየር የሚዘልቁበትን ሁኔታ ኮንነው ይልቅስ እራሳቸውን ከመንግስት በላይ፤ ፍላጎታቸውንም ከህዝብ ፍላጎት በላይ አድርጎ ማየቱን ማቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ