Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2004 ዓ.ም. May 26, 2012)፦ ተወዳጁ የኢሳት ጋዜጠኛ ንጉሴ ጋማ በደረሰበት ድንገተኛ ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ግንቦት 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ንጉሴ ጋማ በነጻው ፕሬስ ቀዳማይ ዓመታት ውስጥ በተለይም "ጧፍ" ትባል የነበረችው ተወዳጅ ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት፣ በኋላም "አዋሽ" ጋዜጣን በማኔጂንግ ኢዲተርነት ይመራ የነበረ ዕውቅ ጋዜጠኛ ሲሆን በወቅቱ ከፕሬስ ስራው ጋር በተገናኘ እስርና እንግልት የደረሰበት አይታክቴ ጋዜጠኛ ነበር።

 

ጋዜጠኛ ንጉሴ የመንግስት ለውጥ ተደርጎ "ነጻ ፕሬስ ተፈቅዷል" ከመባሉ በፊትም ቢሆን በየካቲት መጽሄት ፣ በአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ በማህበራዊና ኪነጥበባዊ ህይወት ዙሪያ በርካታ መጣጥፎች እና አጫጭር ልብወለድ ጽሁፎችን የሚያቀርብ ብዕረኛ እንደነበር የስራ ባልደረቦቹ ያስታውሳሉ።

 

በትምህርቱ በአካውንቲንግ ከንግድ ስራ ኮሌጅ በዲፕሎማ ፣ እንዲሁም በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ ፅሁፍ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በቢኤ ዲግሪ የተመረቀ ሲሆን በስራው ዓለምም ከነጻው ፕሬስ ጋዜጠኝነቱ በፊት በመምህርነት ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ በውሀና ፍሳሽ አገልግሎትና ሴፍ ዘ ቺልድረን በተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግሏል።

 

ጋዜጠኛ ንጉሴ ለስነ ፅሁፍ ልዩ ፍቅር ያለው ፣ በስፋት ያነበበና በተመስጦ የሚያስብ ሰው እንደነበር የሚያስታውሱት የቀድሞ ባልደረቦቹ በባህሪውም በእርጋታ የተሞላ፣ በጣም ደግ እና የሰው ችግር ማየት የማይችል ሩሁሩህ ሰው ነበር ይሉታል።

 

ንጉሴ ጋማ በነጻው ፕሬስ ህይወቱ እየፈለፈለ ለህዝብ ከሚያቀርባቸው ወቅታዊ ዜናዎች ባሻገር የጊዜውን ፖለቲካ አስከፊ ገጽታና የአመራር ብልሹነት እየተነተነ በማቅረቡ ከተደጋጋሚ ማስፈራሪያዎች አልፎ ለእስር እና እንግልት የተዳረገ ደፋር ብዕረኛ ነበር። በስደት ወደ ለንደን ካቀና በኋላም ቢሆን "ደወል" የምትሰኝ መፅሄትና "አቢሲኒያ" የተባለች ጋዜጣ አቋቁሞ በሙያው የዘለቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሴ ጋማ በተለያዩ ድረ ገጽችና ሚዲያዎች ላይም ፅሁፎቹን እያቀረበ ለፍትህ ለዲሞክራሲና ለዜጎች እኩልነት መከበር በተባ ብዕሩ ከመታገል ያልተቆጠበ አገሩን አፍቃሪ ሙያተኛ ነበር። በኋላም የተወዳጇ የህዝብ ልሳን የኢሳት ባልደረባ ሆኖ እስከ ዕልፈተ ቀኑ ድረስ ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል።

 

ንጉሴ ጋማ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆን ለሁለት የልጅ ልጆች መታደሉም ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል በተወዳጁ ጋዜጠኛ በንጉሴ ጋማ ሞት የተሰማውን ልባዊ ሀዘን እየገለጸ ለሚወዳቸው ቤተሰቦቹ፣ ለኢሳት ባልደረቦቹና ለአድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ