ልዑል ኤርሚያስ የኬንታኪ ስቴትን ዋና ከተማ የክብር ቁልፍ ተረከቡ
ልዑል ኤርሚያስ ሣህለሥላሴ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አህጉር የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረትና የልማት አጠቃቀም ጉድለት አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ መሰረታዊ ችግር መሆኑን በማሳሰብ፤ ኬንታኪና አለም አቀፍ የልማት ተቋማት ድጋፋቸውን እንዲያጠናከሩ ጥሪ አቀረቡ።
ልዑል ኤርሚያስ ሣህለ-ሥላሴ ኃይለ- ሥላሴ ይህንን የልማት ጥሪ ያቀረቡት በየአመቱ የኬንታኪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Kentucky State University) የአፍሪካ ጥናት ዲፓርትሜንት በሚያዘጋጀው ኮንፍረንስ በተደርገላቸው ግብዣ ላይ በመገኘት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርና ይህንኑ አስምልክተው ባቀረብት ጥናታዊ ጽሁፍ ወቅት ነበር።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የአፄ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት እኒሁ ሉዑል በወቅቱ የዘውድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሲሆኑ፤ በተለያዩ በተለየም አህጉረ አፍሪካን በሚመለከቱ ልማትና ማህበራዊ ነክ ጉዳዮች ላይ፤ እንዲሁም የሃገሮች የድንበር ግጭቶችና ማህበራዊ ቀውሶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ መፍትሄ በመሻት ላይ በሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት በአባልነትና በመሪነት ጭምር በመሳተፍ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ ናቸው፤ በዚሁ ተግባራቸው ከተለያዩ ዕውቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅናና ሽልማቶችን ተቀብለዋል፤ በተለያዩ ጊዚያትም በዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ በመጋበዝ አሜሪካ ለታዳጊ ሀገሮች የምትሰጠው ሰብዓዊ እርዳታና ልማታዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበክረው ከማሳሰብ አልተቆጠቡም።
የአፍሪካ የልማት እንቅስቃሴ በህብረተሰቡና በአየር ንብረቷ ላይ ሊኖረው የሚቸለውን ተጽ ዕኖ በማስምልከት ለቀረቡ ጥያቄዎች መፍትሄ ለመሻት በተጠራው በዚህ ኮንፍረንስ፤ ልዑልነታቸው ያቀርቡት ጽሁፍ የዕለቱን ተሳታፊዎች ቀልብ በእጅጉ የሳበ ነበር። 80% (ሰማኒያ በመቶ) የሚሆነው የታዳጊ ሀገሮች የጤና ጉድለት ምንጭ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረትና ለልማት የሚውል የውሃ አጠቃቀም ችግር መሆኑን በመረጃ በመደገፍ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ይህ መሰረታዊ ችግር ሳይፈታ ስለ አህጉሪቷ እድገት ማውራት ፋይዳ እንደሌለው አበክረው አስገንዘዋል፤ በዚህ አኳያ መፍተሄ ይሆናል በማለት ያቀዱትንና በአነስተኛ ወጪና ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት በሚያስችል ዘመናዊ ቴክኒዎሎጅ በመታገዝ የጀመሩትን የመጠጥና ልማት ውሃ አጠቃቀም ፕሮጀክት አላማና ግብ ለተሳታፊዎቹ አስተዋውቀውል።
በኬንታኪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የተደረገውን ይህን ኮንፍረንስ በሰብሳቢነት ከመሩት አንዱ የዩኒቨርስቲው የሙያ ማጥኛ ኮሌጅ ዲን (Dean of College of Professional Studies) የሆኑት ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሠር ጋሻው ላቀ ነበሩ። ልዑልነታችው በዚህ አመታዊ ኮንፍርንስ በክብር እንግዳነትና ተናጋሪነት እንዲጋበዙ የተደረጉባቸውን አብይት ምክንያቶች ፕሮፌሰሩ ሲገልጹ፤ በተለይ ለትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያና ለመላ አፍሪካ ያላቸውን ራዕይ እውን ለማድረግ የጀመሩት የልማት ድጋፍና ሰላም የማሰፈንን በጎ አላማ እንቅስቃሴ በዝግጅቱ አስተባባሪዎች አድናቆትን በማትረፉ እንደሆነ ጠቁመውል።
በርካታ የዓለም አቀፍ መሪዎችንና ዕውቅ ግለሰቦችን በማስተናገድ የምትታወቀው የኬንታኪ ስቴት (Kentucky State) መዲና የሆነችው ፍራንክፈርት (Frankfort) ልዑል ኤርሚያስ ሣህለ-ሥላሴ በዘውድ ምክር ቤት ሰብሳቢነታቸውና በግላቸው ጭምር እያደረጉ ያሉትን ሰብዓዊና ልማታዊ ተሳትፎ በማድነቅ የከተማዋን የክብር ቁልፍ አስረክባቸዋለች። የከተማዋ ምክር ቤትም ግንቦት 7 ቀን 2012 “የልዑል ኤርሚያስ ሣህለሥላሴ ኃይለሥላሴ ቀን” ተብሎ እንዲሰየም ውሳኔ አሳልፏል።