በእስራኤል ያሉ ኢትዮጲያዊያን በፍርሀት ተውጠዋል
ጠ/ሚ/ር ቤንጃሚን ናታናሁ በድምሩ 25 ሺ አፍሪካዊ ስደተኞች ባስቸኳይ ወደመጡበት እንዲመለሱ አዘዋል!
(ልዩ ሪፖርታዥ)
Ethiopia Zare (እሁድ ሰኔ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. june 10, 2012)፦ እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በአገሪቱ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ እየተባባሰ በመጣው ዘረኝነትና የኀይል ርምጃ ሳቢያ በከፍተኛ ፍርሀት ውስጥ መውደቃቸውን የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ የዜና አውታራት እየዘገቡ ነው።
ኢትዮጵያዊይኑ አይሁዶች ቀደም ሲል በቆዳቸው ቀለም ሳቢያ የሚደርስባቸውን መድሎ በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ እንደነበር ቢታወቅም ያሁኑ ስጋታቸው ግን በጥቁር አፍሪካዊ ስደተኞች ላይ እየተወሰደ ያለው ህገ-ወጥ የኀይል እርምጃ እነሱንም ሊምራቸው ባለመቻሉ እንደሆነ ነው የተመለከተው።
ከእስራኤል እንደወጡ የተለያዩ የዜና ዘገባዎች ከሆነ በቅርቡ በቴል-አቪቭ የተደረገውን ስደተኞችን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ የአገሪቱ ጠ/ሚ/ር ቤንጃሚን ናታናሁ በድምሩ 25 ሺ አፍሪካዊ ስደተኞች ባስቸኳይ ወደመጡበት እንዲመለሱ አዘዋል። ይህም በስደተኞች በተገነባችው አገረ እስራኤል በተለይም በቴል-አቪቭና በእየሩሳሌም ነዋሪዎች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን የፀረ-አፍሪካዊ ስደተኞች እንቅስቃሴን ተከትሎ የወጣ የፖለቲካ ውሳኔ ነው በሚል እየተወገዘ ይገኛል።
በተለይም ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በሁለቱ ከተሞች የሚኖሩ ነጭ እስራኤላዊያን፣ ‹ስደተኞች ናቸው› በሚል ባሰቧቸው ጥቁር አፍሪካዊያን ላይ የኀይል እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ሱዳን ትሪቡንን ጨምሮ እየሩሳሌም ፖስትና አሪዞና ጄዊሽ ፖስት ሰፊ ትንታኔ አቅርበዋል። በዚሁ ህገ ወጥ የሀይል እርምጃ ሳቢያ ባለፈው ሰኞ ኤርትራዊያን ስደተኞች ይኖሩበታል የተባለን አንድ አፓርትመንት በእሳት እስከማጋየት የዘለቁት የአካባቢው ነዋሪዎች በህንጻው ግድግዳ ላይ "ስደተኞች ውጡ!" የሚል ጽሁፍ ጽፈው እንደነበርም ተመስክሯል።
በቴል-አቪቭና በእየሩሳሌም የሚኖሩ በዜግነት እስራኤላዊ የሆኑ እትዮጵያዊ አይሁዶችም ጥቁር በመሆናቸው ብቻ ‹ስደተኞች ናቸው› በሚል የተሳሳተ ግምት ድብደባና እንግልት እየተፈጸመባቸው መሆኑ ሲጠቆም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 10 የሚሆኑ ኢትዮ እስራኤላዊያን ሰለባ ሆነው መደብደባቸው ነው የተገለጸው። ለምሳሌ በደቡባዊ ቴል-አቪቭ ነዋሪ የሆነው ሀናንያ ዋንዳ የተባለው ኢትዮ እስራኤላዊ፣ ተሰባስበው በመጡ ነጭ እስራኤላዊያን የተወገረው ‹ሱዳናዊ ስደተኛ ነው› በሚል የተሳሳተ ግምት ሳቢያ ነበር።
"ዋንዳ ጓደኛዬ ነው። በነጮቹ ዓይን ሁላችንም ጥቁሮች አንድ ሆነን ነው የምንታያቸው። ዛሬ በጓደኛዬ ላይ የደረሰው በእኔ ጥቁር በሆንኩት እስራኤላዊ አይሁድ ፣ ወይም በማናቸውም የቤተሰቤም ሆነ የማህበረሰቤ አባላት ላይ ሊፈጸም የሚችል ነው።" ሲል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኤልያስ ኢንብራም ለጋዜጠኞቹ ገልጿል።
ኤልያስ አያይዞ ሲገልጽም ፦ "እኔ የህግ ዲግሪ አለኝ። ማስተርሴንም ሰርቻለሁ። በአገሪቱ ጦር ሰራዊት ውስጥም ያገለገልኩ ነኝ። ከተደበደቡት ጓደኞቼ መሀል አንዱ ለፒ ኤች ዲ የታጨ ነው። እኛ እስራኤላዊያን ብንሆንም ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት የሚያስተናግደን እንደ እስራኤላዊ አይሁድ ሳይሆን ለተደረገልን ሁሉ ምስጋና ስናቀርብ መኖር እንዳለብን አድርጎ ነው። አሁን ግን ሁኔታው ተባብሷል። በጣምም እየፈራን ነው። ምክንያቱም በነጮቹ ዓይን ከሁሉም ነገር በፊት ጥቁሮች መሆናችን እየታየ ነውና። " ብሏል።
ለዚህ በእስራኤላዊያን ነጮች ዘንድ እየገዘፈ ለመጣው የዘረኝነት ስሜት መባባስ ደግሞ የአገሪቷ ፖለቲከኞችም እየተወቀሱበት ይገኛሉ። ጠንካራ ዲስኩር የሚያሰሙት ጠ/ሚ/ሩ ኔታናሁ ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ ባለፈው ሰኞ አሪ ኢልዳድ የተባሉት የምክር ቤት አባል፦"የእስራኤል ጦር ኀይል አባላት ወደ አገሪቱ ድንበር ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን ተኩሰው መጣል ይገባቸዋል" ሲሉ በአደባባይ ተናግረዋል።
የአገሪቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ር የሆኑት ኢሊ ይሻይ ደግሞ ስደተኞቹን በሽታ በማዛመትና ሴቶችን በመድፈር ወንጀል በጅምላው ከሰዋቸዋል። በተመሳሳይ መልኩም የሊኩድ ፓርቲን ወክለው የምክር ቤት አባል የሆኑት ሚሪ ሬጌቭ የተባሉት ፖለቲከኛ ደግሞ ስደተኞቹን "ካንሰር ናቸው" የሚል ተራ ስድብ እስከማውረድ ደርሰዋል።
ኢትዮጵያዊያኑ አይሁዶች ግን በተሳሳተ ግምት እየደረሰባቸው ባለው ጥቃት ከመሸበራቸውም ባሻገር በጥቁሮች ላይ እየተፈጸመ ያለው ዘረኝነት እያበሳጫቸው መሆኑን እየገለፁ ነው።
" እኛ ኢትዮ እሳራኤላዊያን በሁኔታው ፍጹም ተረብሸናል። መንግስት ግን ጆሮ ሊሰጠን ፍቃደኛ አልሆነም።" የሚሉት የምክር ቤት አባል የሆኑት ኢትዮ እስራኤላዊቷ ቫሎም ሞላ፣ "አይሁዶች ግብጽ ውስጥ ባሮች ነበርን። በሌሎች አገራትም በሀይማኖታችንና በባህላችን ምክንያት ስለመሰቃየታችን እናወሳለን። አሁን ግን በሌሎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት እያደረስን ነው።" ሲሉ ኮንነዋል።
ጋዲ ያቫርካን የተባሉት የአንድ የመብት ተሟጋች ድርጅት ዳይሬክተርም፦ "እኛ ኢትዮ እስራኤላዊያን ዘረኝነትን በመቃወም በጎዳና ላይ ለተቃውሞ ሰልፍ እንወጣ የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። አሁን ታዲያ ይሄው የመብት ረገጣ በሌሎች ላይ ሲፈጸም እንዴት በዝምታ ማየት እንችላለን?" ሲሉ ሞግተዋል።
አሊዛ የተባለች በሂብሩ ዩንቨርስቲ የሶሲዮሎጂ ተማሪ የሆነች ኢትዮ እስራኤላዊት ደግሞ ፦ "በፊት በፊት ነጭ እስራኤላዊ የሆኑ ጓደኞቼ ከአፍሪካ የሚመጡ ስደተኞችን በተመለከተ ምን እንደሚሰማኝ ሲጠይቁኝ እናደድ ነበር። ጥቁር በመሆኔ ብቻ ስለ ጥቁር ስደተኞች የተለየ ስሜት ሊኖረኝ እንደሚገባ ለምን ያስባሉ? እያልኩም እበሳጭ ነበር። እኔ አይሁድና እስራኤላዊ ነኝ። የመጣሁትም ገና ጨቅላ ህጻን እያለሁ ስለነበር ከአፍሪካ ይልቅ የአይሁድ ታሪክ ነው የሚመለከተኝ ብዬ አስባለሁ። ከምስራቅ አውሮፓ የሆኑ አይሁዶች፣ ከአፍሪካ ሞስሊሞችና ክርስቲያኖች ይልቅ ይዛመዱኛል ባይም ነበርኩ።
" አሁን ግን ጥቁር በመሆኔ ብቻ በገዛ አገሬ ለመኖር እየፈራሁ ነው።" ብላለች። አሊዛ ከፍተኛ ፍርሀት ውስጥ የወደቀችው በተለይም ባለፈው ሰኞ ኤርትራዊያን የሚኖሩበት አፓርትመንት በጥቃት ፈጻሚዎች እንዲቃጠል ከተደረገ ወዲህ መሆኑን ነው የገለጸችው።
የመብት ተሟጋቹና በእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ያለ በስደተኞች ጉዳይ ዙሪያ የሚሰራ ኮሚቴ አባል የሆነው ኤልያስ ኢንብራም ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ አይሁዶች በቆዳቸው ቀለም ምክንያት እየደረሰባቸው ያለውን ችግር ሲዘረዝር የሚከተለውን አጣቅሷል፦
"አውቶቢስ ውስጥ ሰዎች ዞር እያሉ የሚያናግሩኝ በእንግሊዘኛ ነው። በጥቁርነቴ ስደተኛ አርገው ነው የሚያስቡኝ። በገበያ አዳራሾችና በቲያትር ቤቶች ያለብን የደህንነት ፍተሻ ከነጮቹ የተለየ ነው። ፈታሾቹ የሚያዩኝ በጥርጣሬ ነው። ሌላው ቀርቶ ታክሲ ማስቆም እንኳን አዳጋች እየሆነ መጥቷል" ብሏል።
የተለያዩ የዜና አውታሮች ለህዝብ ካቀረቧቸው ዘገባዎች መረዳት እንደሚቻለው ከሆነ ኢትዮ እስራኤላዊያን አይሁዶችን ፍርሀትና ብስጭት ውስጥ የከተታቸው ‹ስደተኞች ናችሁ› በሚል የተሳሳተ ግምት የሚደርስባቸው ጥቃት ብቻ አይደለም። በአጠቃላዩ በቆዳ ቀለም ላይ በተመሰረተ ጥላቻ ጥቁር አፍሪካዊያን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ አሳዝኗቸዋል። አስቆጥቷቸዋል።
ይህ በአገሪቱ ዋና ዋና ፖለቲከኞች እየተራገበና በአገሬው ነጭ ነዋሪዎች እየተወሰደ ያለው የበደል እርምጃ ሰለባ ካደረጋቸው ጥቁር አፍሪካዊያን መሀል በተለይም የሱዳንና የኤርትራ ተወላጅ ስደተኞች ይበዛሉ። ይህ ደግሞ ብዙዎች ኢትዮ እስራኤላዊያንን አሸማቋል። ጥቂት የማይባሉት ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ወደ እስራኤል የዘለቁት በሱዳን በኩል እንደነበር ሲታወስ ከነዚህም መሀል ዚቫ መኮንን ደጉ አንዱ ነው።
"ሱዳኖች እኛን እንዴት በመልካም መስተንግዶ እንደሸኙን ሳስታውስና አሁን እዚህ ምን እየደረሰባቸው እንደሆነ ሳይ ሀፍረት ይሰማኛል። ውሀ እያቀረቡና በቆይታችን ሳንቸገር ሰርቶ ማደር እንድንችል ይረዱን ነበር። " ይላል ይህ በቁጭት የተመላው ኢትዮ እስራኤላዊ።
የዚቫ መኮንን ደጉ ትዝብት ይህ ብቻ አልነበረም። " ቁም ነገሩ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከ30 ዓመት በፊት ወደ እስራኤል ለመምጣት ባደረግነው የሽግግር ቆይታ ወቅት በሱዳኖች የተረዳን መሆናችን ብቻ አይደለም። መላዋ አገራችን እስራኤልም እኮ መፈጠር የቻለችው ሁላችንም ባንድ ወቅት ስደተኞች በመሆናችን ነበር። አሁንም ታዲያ በሌላ አገር መጠጊያ ባላገኙ አይሁዶች ላይ የደረሰውን ማስታወስ በተገባን ነበር።" ብሏል በሀዘን።
‹በአገሪቱ ለተስፋፋው የወንጀል ተግባር ዓይነተኛ ምንጮቹ አፍሪካዊያን ስደተኞች ናቸው› የሚለውን በነዋሪዎቹ መሀል የሚስተጋባውን ስሜት ተከትለው የእስራኤል ፖለቲከኞች አክራሪ አቋም እየወሰዱ ከመሆኑም በላይ የነዋሪዎቹን ስሜት ለመጥለፍ ሲሉ የሚያሰሟቸው ፅንፈኛ ዲስኩሮች በጥቁር አፍሪካዊያኑ ላይ እየተወሰዱ ያሉትን ህገ ወጥ ጥቃቶች እያባባሱት መሆኑ ነው የታመነበት።
ከሰብዓዊ መብቶችና ከህግ አንጻር የአገሪቱ ነጭ ነዋሪዎች የተያያዙትን አስከፊ አካሄድ ለማስቆም መንግስት ይህ ነው የሚባል ጥረት ካለማድረጉም በላይ በጠ/ሚ/ሩ በቤንጃሚን ኔታናሁ አጋፋሪነት በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ጨምሮ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኮትዴቯርና ከጋና የመጡ 25ሺ ስደተኞች ባስቸኳይ ተገደው እንዲመለሱ ተወሰኗል። ባኳያውም የመንግስት ሀይሎች ህገ ወጥ ስደተኞችን እስከ 3ዓመት ድረስ ማሰር እንዲችሉ የሚፈቅድ አዲስ ህግ አርቅቀዋል። ይህ ህግ በስደተኞች ፣ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በአንዳንድ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ውግዘት ገጥሞታል።



